ሆሴዕ 3:1-5
ሆሴዕ 3:1-5 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም፥ “የእስራኤል ልጆች ወደ ሌሎች አማልክት ቢመለሱና የዘቢብ ጥፍጥፍን ቢወድዱ እንኳን፥ እግዚአብሔር እንደሚወድዳቸው አንተም ክፋትና ዝሙት ያለባትን ሴት ውደድ” አለኝ። እኔም በዐሥራ አምስት ብርና በአንድ ቆሮስ መስፈሪያ ተኩል ገብስና በአንድ ፊቀን ወይን ተወዳጀኋት። “ከእኔ ጋር ብዙ ወራት ተቀመጪ፤ አታመንዝሪም፤ ሌላ ሰውንም አታግቢ፤ እኔም ከአንቺ ጋር እኖራለሁ” አልኋት። የእስራኤል ልጆች ያለ ንጉሥና ያለ አለቃ፥ ያለ መሥዋዕትና ያለ ምሥዋዕ፤ ያለ ካህንና ያለ ራእይ፤ ያለ ኤፉድና ያለ ተራፊም ብዙ ወራት ይቀመጣሉና፤ ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመልሰው አምላካቸውን እግዚአብሔርንና ንጉሣቸውን ዳዊትን ይፈልጋሉ፤ በኋለኛውም ዘመን እግዚአብሔርንና ቸርነቱን ያስቡታል።
ሆሴዕ 3:1-5 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “እርሷ በሌላ ሰው የምትወደድ አመንዝራ ብትሆንም፣ አሁንም ሂድና ሚስትህን ውደዳት፤ ወደ ሌሎች አማልክት ዘወር ቢሉና ለእነርሱም የተቀደሰውን የዘቢብ ጥፍጥፍ ቢወድዱም፣ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን እንደ ወደዳቸው አንተም እርሷን ውደዳት።” ስለዚህ በዐሥራ ዐምስት ሰቅል ጥሬ ብርና በአንድ ቆሮስ ተኩል መስፈሪያ ገብስ ገዛኋት። እኔም፣ “ከእኔ ጋራ ብዙ ቀን ተቀመጪ፤ አታመንዝሪ ወይም ሌላ ሰው አትውደጂ፤ እኔም ከአንቺ ጋራ እኖራለሁ” ብዬ ነገርኋት። እስራኤላውያን ለብዙ ዘመን ያለ ንጉሥና ያለ አለቃ፣ ያለ መሥዋዕትና ያለ ዐምደ ጣዖት፣ ያለ ኤፉድና ያለ ጣዖት ምስል ይኖራሉና። ከዚያ በኋላ እስራኤላውያን ተመልሰው አምላካቸውን እግዚአብሔርንና ንጉሣቸውን ዳዊትን ይፈልጋሉ፤ በመጨረሻውም ዘመን በመንቀጥቀጥ ወደ እግዚአብሔርና ወደ በረከቱ ይመጣሉ።
ሆሴዕ 3:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም፦ የእስራኤል ልጆች ወደ ሌሎች አማልክት ቢመለሱና የዘቢብ ጥፍጥፍን ቢወድዱ እንኳ፥ እግዚአብሔር እንደሚወድዳቸው አንተም ውሽማዋን የምትወድደውን አመንዝራይትን ሴት ውደድ አለኝ። እኔም በአሥራ አምስት ብርና በአንድ ቆሮስ መስፈሪያ ተኩል ገብስ ገዛኋት። ከእኔ ጋር ብዙ ወራት ተቀመጪ፥ አታመንዝሪም፥ ለሌላ ሰውም አትሁኚ፥ እኔም እንዲሁ እሆንልሻለሁ አልኋት። የእስራኤል ልጆች ያለ ንጉሥና ያለ አለቃ፥ ያለ መሥዋዕትና ያለ ዓምድ፥ ያለ ኤፉድና ያለ ተራፊም ብዙ ወራት ይቀመጣሉና፥ ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመልሰው አምላካቸውን እግዚአብሔርንና ንጉሣቸውን ዳዊትን ይፈልጋሉ፥ በኋለኛውም ዘመን ፈርተው ወደ እግዚአብሔርና ወደ በረከቱ ይመጣሉ።
ሆሴዕ 3:1-5 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “እስራኤላውያን ወደ ሌሎች አማልክት ሄደው የዘቢብ ጥፍጥፍ ማቅረብ ቢወዱ እንኳ ከዚሁ ጋር እግዚአብሔር ይወዳቸዋል፤ አንተም እንደዚሁ ፍቅረኛ ወደ አላት አመንዝራ ሴት ሄደህ ውደዳት።” ስለዚህ በዐሥራ አምስት ብርና በአንድ መቶ ኃምሳ ኪሎ ገብስ ገዛኋት፤ “ሳታመነዝሪና ሰውነትሽን ለማንኛውም ወንድ ሳትሰጪ እኔን እየጠበቅሽ ለብዙ ጊዜ መቈየት አለብሽ፤ እኔም ለአንቺ እንዲሁ አደርግልሻለሁ” ብዬ ነገርኳት። በዚሁ ዐይነት የእስራኤል ሕዝብ ያለ ንጉሥ ወይም ያለ መሪ፥ ያለ መሥዋዕት ወይም ያለ ሐውልት፥ ያለ ልብሰ ተክህኖ ወይም የጣዖት ምስል ለብዙ ዘመን ይኖራሉ፤ ከዚህ ጊዜ በኋላ እስራኤላውያን ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔርና ወደ ንጉሣቸው ወደ ዳዊት ይመለሳሉ፥ በኋለኛው ዘመን በፍርሃት ወደ እግዚአብሔር ይመጣሉ፤ በረከቱንም ይቀበላሉ።
ሆሴዕ 3:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም እንዲህ አለኝ፦ “የእስራኤል ልጆች ወደ ሌሎች አማልክት ቢመለሱና የዘቢብ ጥፍጥፍን ቢወድዱ እንኳ ጌታ እንደሚወድዳቸው እንዲሁ አንተም ዳግመኛ ሂድ፥ በውሽማዋ የምትወደደውን አመንዝራይትን ሴት ውደድ።” እኔም በዓሥራ አምስት ብርና በአንድ ቆሮስ መስፈሪያ ተኩል ገብስ ገዛኋት። ለእርሷም፦ “የእኔ ሆነሽ ለብዙ ወራት ተቀመጪ፥ አታመንዝሪም፥ ለሌላ ሰውም አትሁኚ፤ እኔም እንዲሁ እሆንልሻለሁ” አልኋት። የእስራኤል ልጆች ያለ ንጉሥና ያለ አለቃ፥ ያለ መሥዋዕትና ያለ ዓምድ፥ ያለ ኤፉድና ያለ ተራፊም ብዙ ወራት ይቀመጣሉና፤ ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመልሰው አምላካቸውን ጌታንና ንጉሣቸውን ዳዊትን ይፈልጋሉ፤ በኋለኛውም ዘመን ፈርተው ወደ ጌታና ወደ መልካምነቱ ይመጣሉ።