ሆሴዕ 2:1-23
ሆሴዕ 2:1-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወንድማችሁን ሕዝቤ፥ እኅታችሁንም፦ ሥህልት በሉአቸው። እናታችሁ ሚስቴ አይደለችምና፥ እኔም ባልዋ አይደለሁምና እናታችሁን ተዋቀሱአት። ዝሙቷን ከፊቷ፥ ምንዝርናዋንም ከጡቶችዋ መካከል አስወግዳለሁ። ዕራቁትዋንም እንድትቆም አደርጋታለሁ፤ እንደ ሕፃንነትዋ ወራት፥ እንደ ተወለደችባት እንደ መጀመሪያዪቱም ቀን አደርጋታለሁ። እንደ ምድረ በዳም አደርጋታለሁ፤ ውኃም እንደሌላት ምድር አደርጋታለሁ፤ በውኃም ጥም እገድላታለሁ። የዝሙት ልጆች ናቸውና ልጆችዋን ይቅር አልላቸውም። እናታቸው አመንዝራለችና፤ የወለደቻቸውም፥ “እንጀራዬንና ውኃዬን፥ ቀሚሴንና መደረቢያዬን፥ ዘይቴንና የሚገባኝን ሁሉ የሚሰጡኝ ወዳጆችን እከተላቸው ዘንድ እሄዳለሁ” ብላለችና አሳፈረቻቸው። ስለዚህ እነሆ ጎዳናዋን በእሾህ አጥረዋለሁ፤ መንገድዋንም እዘጋዋለሁ፤ ማለፊያም ታጣለች። ወዳጆችዋንም ትከተላለች፤ ነገር ግን አትደርስባቸውም፤ ትፈልጋቸውማለች፤ ነገር ግን አታገኛቸውም፤ እርስዋም፥ “ከዛሬ ይልቅ የዚያን ጊዜ ይሻለኝ ነበርና ተመልሼ ወደ ቀደመው ባሌ እሄዳለሁ” ትላለች። እርስዋም እህልንና ወይንን ዘይትንም የሰጠኋት፥ ብርንና ወርቅን ያበዛሁላት እኔ እንደ ሆንሁ አላወቀችም። እርስዋ ግን ወርቁንና ብሩን ለጣዖት አደረገች። ስለዚህ እህሌን በጊዜው፥ ወይኔንም በወራቱ እወስዳለሁ፤ ኀፍረቷንም እንዳትሸፍን ልብሴንና መጎናጸፊያዬን እገፍፋታለሁ። አሁንም በወዳጆችዋ ፊት ነውርዋን እገልጣለሁ፤ ከእጄም ማንም አያድናትም። ደስታዋንም ሁሉ፥ በዓላቶችዋንም፥ መባቻዎችዋንም፥ ሰንበቶችዋንም፥ ሥርዐቶችዋንም ሁሉ አስቀራለሁ። እርስዋም፥ “ወዳጆች የሰጡኝ ዋጋዬ ይህ ነው” ያለችውን ሁሉ ወይንዋንና በለስዋን አጠፋለሁ፤ ምስክርም ይሆኑ ዘንድ አኖራቸዋለሁ፤ የምድረ በዳም አራዊትና የሰማይ ወፎች፥ የምድር ተንቀሳቃሾችም ይበሉታል። እኔን ረስታ ወዳጆችዋን እየተከተለች፥ በጕትቾችዋና በጌጥዋም እያጌጠች ለበኣሊም የሠዋችበትን ወራት እበቀልባታለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር። ስለዚህ እነሆ አቅበዘብዛታለሁ፤ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ፤ ለልብዋም እናገራለሁ። ከዚያም የተገኘውን ገንዘብዋን እሰጣታለሁ፤ ምክርዋንም በአኮር ሸለቆ እገልጣለሁ፤ እንደ ሕፃንነትዋ ወራት፥ ከግብፅም እንደ ወጣችበት ቀን ትዘምራለች። በዚያ ቀን ባሌ ብለሽ ትጠሪኛለሽ እንጂ ዳግመኛ በዓሊም ብለሽ አትጠሪኝም፥ ይላል እግዚአብሔር፤ የበዓሊምን ስሞች ከአፍዋ አሰወግዳቸዋለሁና፥ ስማቸውም ከእንግዲህ ወዲህ አይታሰብም። በዚያም ቀን ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች፥ ከመሬትም ተንቀሳቃሾች ጋር ቃል ኪዳን አደርግላቸዋለሁ። ቀስትንና ሰይፍን፥ ጦርንም ከምድሩ እሰብራለሁ፤ ተዘልለሽም ትቀመጫለሽ። ለዘለዓለምም ለእኔ እንድትሆኚ አጭሻለሁ፤ በጽድቅና በፍርድ በምሕረትና በይቅርታ አጭሻለሁ። ለእኔም እንድትሆኚ በመታመን አጭሻለሁ፤ አንቺም እግዚአብሔርን ታውቂአለሽ። በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ለሰማይ እመልሳለሁ፤ ሰማይም ለምድር ይመልሳል፤ ምድርም ለእህል፥ ለወይንና ለዘይት ትመልሳለች፤ እነርሱም ለኢይዝራኤል ይመልሳሉ። በምድርም ላይ ለእኔ እዘራታለሁ፤ ይቅርታ የሌላትን ይቅር እላታለሁ፤ ያልተወደደች የነበረችውን እወድዳታለሁ፤ ሕዝቤም ያልሆነውን፥ “አንተ ሕዝቤ ነህ” እለዋለሁ፤ እርሱም፥ “አንተ ጌታዬና አምላኬ ነህ” ይለኛል።
ሆሴዕ 2:1-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ወንድሞቻችሁን ‘ሕዝቤ’፣ እኅቶቻችሁንም ‘ተወዳጆቼ’ ብላችሁ ጥሯቸው። “እናታችሁን ምከሯት፤ ምከሯት፤ እርሷ ሚስቴ አይደለችም፤ እኔም ባሏ አይደለሁምና። ከፊቷ የዘማዊነት አስተያየትን፣ ከጡቶቿም መካከል ምንዝርናዋን ታስወግድ። አለዚያ ገፍፌ ዕርቃኗን አስቀራታለሁ፤ እንደ ተወለደችበትም ቀን አደርጋታለሁ፤ እንደ ምድረ በዳ፣ እንደ ደረቅም ምድር አደርጋታለሁ፤ በውሃ ጥምም እገድላታለሁ። ለልጆቿ አልራራላቸውም፤ የምንዝርና ልጆች ናቸውና። እናታቸው አመንዝራ ናት፤ በውርደትም ፀንሳቸዋለች፤ እርሷም፣ ‘እንጀራዬንና ውሃዬን ይሰጡኛል፤ ሱፌንና የሐር ልብሴን፣ ዘይቴንና መጠጤን ይሰጡኛል፤ ስለዚህ ውሽሞቼን ተከትዬ እሄዳለሁ’ አለች። በዚህ ምክንያት መንገዷን በእሾኽ እዘጋለሁ፤ መውጫ መንገድ እንዳታገኝም ዙሪያዋን በግንብ ዐጥራለሁ። ውሽሞቿን ተከትላ ትሄዳለች፤ ነገር ግን አትደርስባቸውም፤ ትፈልጋቸዋለች፤ ሆኖም አታገኛቸውም። ከዚያም እንዲህ ትላለች፤ ‘ወደ ቀድሞ ባሌ እመለሳለሁ፤ የፊተኛው ኑሮዬ ከአሁኑ ይሻለኛልና።’ እርሷም እህል፣ ዘይትና አዲስ የወይን ጠጅ የሰጠኋት፣ ለበኣል አምልኮ ያደረጉትን፣ ብርንና ወርቅን ያበዛሁላት፣ እኔ እንደ ሆንሁ አላወቀችም። “ስለዚህ እህሌን በመከር ጊዜ፣ አዲሱም የወይን ጠጅ በደረሰ ጊዜ እወስዳለሁ፤ ዕርቃኗንም እንዳትሸፍንበት፣ ሱፍና የሐር ልብሴን መልሼ እወስድባታለሁ። አሁንም በውሽሞቿ ፊት፣ ነውሯን እገልጣለሁ፤ ከእጄም የሚያድናት የለም። የደስታ በዓሎቿን ሁሉ፣ የዓመት በዓላቷንና የወር መባቻዎቿን፣ ሰንበቶቿንና የተመረጡ በዓላቷን ሁሉ አስቀራለሁ። ከውሽሞቼ የተቀበልሁት ዋጋ ነው የምትለውን የወይን ተክሎቿንና የበለስ ዛፎቿን አጠፋለሁ፤ ጫካ አደርገዋለሁ፤ የዱር አራዊትም ይበሉታል። ለበኣል አማልክት ዕጣን ስላጠነችባቸው ቀናት እቀጣታለሁ፤ በጌጣጌጥና በቀለበቶች ራሷን አስጊጣለች፤ ውሽሞቿንም ተከትላ ሄዳለች፤ እኔን ግን ረስታለች” ይላል እግዚአብሔር። “ስለዚህ እነሆ፤ አባብላታለሁ፤ ወደ ምድረ በዳም እወስዳታለሁ፤ በፍቅር ቃል አነጋግራታለሁ። በዚያም የወይን ተክሏን እመልስላታለሁ፤ የአኮርንም ሸለቆ የተስፋ በር እንዲሆናት አደርጋለሁ። በዚያም ከግብጽ እንደ ወጣችበት ቀን፣ እንደ ልጅነቷም ጊዜ ትዘምራለች። “በዚያ ቀን፣ ‘ባሌ’ ብለሽ፣ ትጠሪኛለሽ” ይላል እግዚአብሔር። “ከእንግዲህም፣ ‘ጌታዬ’ ብለሽ አትጠሪኝም። የበኣል አማልክትን ስም ከአንደበቷ አስወግዳለሁ፤ ከእንግዲህም ስሞቻቸው አይነሡም። በዚያ ቀን ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች፣ በምድርም ላይ ከሚሳቡ ፍጥረታት ጋራ፣ ቃል ኪዳን አደርግላቸዋለሁ፤ ሁሉም ያለ ሥጋት እንዲኖሩ፣ ቀስትን፣ ሰይፍንና ጦርነትን፣ ከምድሪቱ አስወግዳለሁ። ለእኔ እንድትሆኚ ለዘላለም ዐጭሻለሁ፤ በጽድቅና በፍትሕ፣ በፍቅርና በርኅራኄም ዐጭሻለሁ። በታማኝነት ዐጭሻለሁ፤ አንቺም እግዚአብሔርን ታውቂያለሽ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በዚያ ቀን እኔ እመልሳለሁ፤ ለሰማያት እመልሳለሁ፤ እነርሱም ለምድር ምላሽ ይሰጣሉ፤ ምድርም ለእህል፣ ለአዲስ የወይን ጠጅና ለዘይት ምላሽ ትሰጣለች፤ እነርሱም ለኢይዝራኤል ምላሽ ይሰጣሉ። ስለ ራሴ ስል በምድሪቱ እተክላታለሁ፤ ‘ምሕረትን ያላገኘ’ ብዬ የጠራሁትንም እምረዋለሁ፤ ‘ሕዝቤ አይደላችሁም’ ተብለው የተጠሩትንም፣ ‘ሕዝቤ’ እላቸዋለሁ፤ እነርሱም፣ ‘አንተ አምላኬ ነህ’ ይላሉ።”
ሆሴዕ 2:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የእስራኤልም ልጆች ቍጥር እንደማይሰፈርና እንዳማይቈጠር እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናል፥ እንዲህም ይሆናል፥ እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም ተብሎ በተነገረበት በዚያ ስፍራ የሕያው አምላክ ልጆች ይባላሉ። የይሁዳ ልጆችና የእስራኤል ልጆች በአንድነት ይሰበሰባሉ፥ ለእነርሱም አንድ አለቃ ይሾማሉ፥ ከምድሪቱም ይወጣሉ፥ የኢይዝራኤል ቀን ታላቅ ይሆናልና። ወንድሞቻችሁን፦ ዓሚ፥ እኅቶቻችሁንም፦ ሩሃማ በሉአቸው። እናታችሁ ሚስቴ አይደለችምና፥ እኔም ባልዋ አይደለሁምና ተምዋገቱ፥ ከእናታችሁ ጋር ተምዋገቱ። ግልሙትናዋን ከፊትዋ፥ ምንዝርናዋንም ከጡቶችዋ መካከል ታስወግድ፥ ዕራቁትዋን እንዳልገፍፋት፥ እንደ ተወለደችበትም ቀን እንዳላደርጋት፥ እንደ ምድረ በዳና እንደ ደረቅ ምድር እንዳላደርጋት፥ በጥማትም እንዳልገድላት፥ የግልሙትናዋ ልጆች ናቸውና ልጆችዋን አልምርም። እናታቸው አመንዝራለች፥ የፀነሰቻቸውም፦ እንጀራዬንና ውኃዬን፥ ጥጤንና የተልባ እግሬን፥ ዘይቴንና መጠጤን ከሚሰጡኝ ከውሽሞቼ በኋላ እሄዳለሁ ብላ አስነወረቻቸው። ስለዚህ፥ እነሆ፥ መንገድሽን በእሾህ እዘጋለሁ፥ መንገድዋንም እንዳታገኝ ቅጥርን እቀጥርባታለሁ። ውሽሞችዋንም ትከተላለች፥ ነገር ግን አትደርስባቸውም፥ ትፈልጋቸውማለች፥ ነገር ግን አታገኛቸውም፥ እርስዋም፦ ከዛሬ ይልቅ የዚያን ጊዜ ይሻለኝ ነበርና ተመልሼ ወደ ቀደመው ባሌ እሄዳለሁ ትላለች። እርስዋም እህልንና ወይንን ጠጅ ዘይትንም የሰጠኋት፥ ለበኣልም የተሠራውን ብርና ወርቅ ያበዛሁላት እኔ እንደ ሆንሁ አላወቀችም። ስለዚህ እህሌን በጊዜዋ ወይን ጠጄንም በወረትዋ እወስዳለሁ፥ ዕራቁትነትዋንም እንዳትሸፍን ጥጤንና የተልባ እግሬን እገፍፋታለሁ። አሁንም ውሽሞችዋ እያዩ ነውርዋን እገልጣለሁ፥ ከእጄም ማንም አያድናትም። ደስታዋንም ሁሉ፥ በዓላቶችዋንም፥ መባቻዎችዋንም፥ ሰንበቶችዋንም፥ የተቀደሱትንም ጉባኤዎችን ሁሉ አስቀራለሁ። እርስዋም፦ ውሽሞቼ የሰጡኝ ዋጋዬ ይህ ነው ያለችውን ወይንዋንና በለስዋን አጠፋለሁ፥ ዱርም አደርገዋለሁ፥ የምድረ በዳም አራዊት ይበሉታል። እኔን ረስታ ውሽሞችዋን እየተከተለች፥ በጕትቾችዋና በጌጥዋም እያጌጠች ለበኣሊም ያጠነችበትን ወራት እበቀልባታለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። ስለዚህ፥ እነሆ፥ አባብላታለሁ፥ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ፥ ለልብዋም እናገራለሁ። ከዚያም የወይን ቦታዋን፥ የተስፋ በርም እንዲሆንላት የአኮርን ሸለቆ እሰጣታለሁ፥ በዚያም ከግብጽ ምድር እንደ ወጣችበት ቀን እንደ ሕፃንነትዋ ወራት ትዘምራለች። በዚያ ቀን ባሌ ብለሽ ትጠሪኛለሽ እንጂ ዳግመኛ በኣሌ ብለሽ አትጠሪኝም፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የበኣሊምን ስም ከአፍዋ አስወግደዋለሁና፥ በስማቸውም እንግዲህ አይታሰቡምና። በዚያም ቀን ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች ከመሬትም ተንቀሳቃሾች ጋር ቃል ኪዳን አደርግላቸዋለሁ፥ ቀስትንና ሰይፍን ሰልፍንም ከምድሩ እሰብራለሁ፥ ተከልለውም እንዲኖሩ አስተኛቸዋለሁ። ለዘላለምም ለእኔ እንድትሆኚ አጭሻለሁ፥ በጽድቅና በፍርድ በምሕረትና በርኅራኄ አጭሻለሁ። ለእኔም እንድትሆኚ በመታመን አጭሻለሁ፥ አንቺም እግዚአብሔርን ታውቂአለሽ። በዚያንም ቀን እመልሳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር ለሰማይ እመልሳለሁ፥ ሰማይም ለምድር ይመልሳል፥
ሆሴዕ 2:1-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ ወንድሞቻችሁ የሆኑትን እስራኤላውያንን “አሚ” እኅቶቻችሁንም “ሩሃማ” ብላችሁ ጥሩአቸው። ልጆቼ ሆይ! ከእንግዲህ ወዲያ እናታችሁ ሚስቴ ስላልሆነችና እኔም ባልዋ ስላልሆንኩ የዝሙት አመለካከትዋንና አመንዝራነትዋን እንድታስወግድ ውቀስዋት። ባትመለስ ግን እንደ ተወለደችበት ቀን እርቃንዋን አስቀራታለሁ፤ እንደ ደረቀ ባዶ ምድር አደርጋታለሁ፤ በውሃ ጥምም እገድላታለሁ። ከዘማዊት ሴት የተወለዱ ስለ ሆኑ ለልጆችዋም አልራራላቸውም። እናታቸው አመንዝራ ስለ ሆነች እነርሱን ባሳፋሪ መንገድ ፀንሳቸዋለች፤ እርስዋም ይህን ያደረገችው ምግቤንና ውሃዬን፥ የሱፍና የተልባ እግር ልብሴን፥ ዘይቴንና መጠጤን የሚሰጡኝ ስለ ሆነ ፍቅረኞቼን ተከትዬ እሄዳለሁ ብላ ነው። ስለዚህ መንገድዋን በእሾኽ እዘጋዋለሁ፤ መውጫ በር እንዳታገኝም ዙሪያውን በግንብ አጥራለሁ። ፍቅረኞችዋን ተከትላ ትሄዳለች፤ ነገር ግን ልትደርስባቸው አትችልም፤ ትፈልጋቸዋለች፤ ነገር ግን አታገኛቸውም፤ ከዚህ በኋላ “ከአሁኑ ኑሮዬ ይልቅ የዱሮው ይሻለኛል፤ ስለዚህ ወደ ቀድሞው ባሌ እሄዳለሁ” ትላለች። እርስዋ እህልን፥ የወይን ጠጅን፥ የወይራ ዘይትን የሰጠኋት፥ እኔ እንደ ሆንኩ ከቶ አልተገነዘበችም፤ እኔ ያበዛሁላትን ብርና ወርቅ “በዓል” ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት አቀረበች። እህሉን በመከር ጊዜ ወይኑንም በወቅቱ እወስድባታለሁ፤ ራቁትነትዋን የምትሸፍንባቸውን የሱፍና የተልባ እግር ልብሶቼንም እወስድባታለሁ። በፍቅረኞችዋም ፊት እርቃንዋን አስቀራታለሁ፤ ከእጄም የሚያድናት የለም። የምትደሰትባቸውን በዓላትዋን ሁሉ ሰንበትዋን፥ ዓመታዊና ወርኀዊ በዓላትዋን እሽራለሁ፤ የተለዩ በዓላትዋንም ሁሉ እንዳታከብር አደርጋታለሁ። ከፍቅረኛዎችዋም ያገኘቻቸውን የወይን ተክሎችና የበለስ ዛፎች እነቃቅላለሁ፤ የወይንና የፍራፍሬ እርሻዎችዋን ወደ ጫካነት እለውጣለሁ፤ የዱር አራዊትም ይበሉአቸዋል። “በዓል” ለሚባለው ጣዖት ለማጠንና ጌጣጌጥዋን አድርጋ ፍቅረኛዎችዋን በመከተል እኔን በመተዋ እቀጣታለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር። ስለዚህ እንደገና ወደ በረሓ እወስዳታለሁ፤ እዚያም በፍቅር ቃል አባብዬ እማርካታለሁ። የቀድሞውን የወይን ተክል እመልስላታለሁ፤ የመከራንም ሸለቆ የተስፋ በር እንዲሆናት አደርጋለሁ፤ እዚያም ከግብጽ ስትወጣ በወጣትነትዋ ወራት በነበራት ሁኔታ በደስታ ትዘምራለች። በዚያን ቀን “ባለቤቴ” ብላ እንጂ እንደ በዓል ጣዖት “ጌታዬ” ብላ አትጠራኝም። ከአንደበትዋ የ“በዓል” ጣዖቶችን ስም ለማስወግድ የእነርሱ ስም ዳግመኛ አይጠራም። በዚያን ጊዜ ስለ እናንተ ከአራዊት፥ ከሰማይ ወፎችና በደረታቸው በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረቶች ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ከምድሪቱም ላይ ቀስትን፥ ሰይፍንና ጦርነትን አስወግዳለሁ፤ እናንተንም በሰላም እንድታርፉ አደርጋለሁ። እስራኤል ሆይ! ለዘለዓለም እንደ ባለቤቴ አደርግሻለሁ፤ በጽድቅ፥ በፍትሕ፥ በዘለዓለማዊ ፍቅርና በምሕረት እንደ ባለቤቴ እንድትሆኚ አደርጋለሁ። ቃል ኪዳኔን በመጠበቅ እንደ ባለቤቴ አደርግሻለሁ፤ አንቺም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ታውቂያለሽ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በዚያን ቀን እኔ መልስ አሰጣለሁ፤ እኔ ለሰማያት መልስ እሰጣለሁ፤ ሰማያትም ለምድር መልስ ይሰጣሉ። ምድርም እህልን፥ ወይንንና የወይራ ዘይትን በማስገኘት ለኢይዝራኤል መልስ ትሰጣለች። ሕዝቤን በምድሪቱ ላይ እመሠርታለሁ፤ እንዲበለጽጉም አደርጋቸዋለሁ፤ ‘ምሕረት አይደረግላችሁም’ የተባሉትን ምሕረት አደርግላቸዋለሁ፤ ‘ሕዝቤ አይደላችሁም’ የተባሉትንም ‘ሕዝቤ ናችሁ’ እላቸዋለሁ፤ እነርሱም ‘አንተ አምላካችን ነህ’ ይሉኛል።”
ሆሴዕ 2:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የእስራኤልም ልጆች ቍጥር እንደማይሰፈርና እንዳማይቆጠር እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናል፤ እንዲሁም እነርሱ፦ “ሕዝቤ አይደላችሁም” በተባሉበት በዚያ ስፍራ፦ “የሕያው አምላክ ልጆች” ይባላሉ። የይሁዳ ልጆችና የእስራኤል ልጆች በአንድነት ይሰበሰባሉ፥ እነርሱም አንድ አለቃ በራሳቸው ላይ ይሾማሉ፤ የኢይዝራኤልም ቀን ታላቅ ይሆናልና ከምድሪቱ ይወጣሉ። ወንድሞቻችሁን፦ “ዓሚ”፥ እኅቶቻችሁንም፦ “ሩሃማ” በሉአቸው። እናታችሁ ሚስቴ አይደለችምና፥ እኔም ባሏ አይደለሁምና ተምዋገቱ፤ ከእናታችሁ ጋር ተምዋገቱ። ምንዝርናዋን ከፊትዋ፥ ዝሙትዋንም ከጡቶችዋ መካከል ታስወግድ፤ አለበለዚያ ዕራቁትዋን እንድትሆን እገፍፋታለሁ፥ እንደ ተወለደችበትም ቀን አደርጋታለሁ፥ እንደ ምድረ በዳና እንደ ደረቅ ምድር አደርጋታለሁ፥ በጥምም እገድላታለሁ። እንዲሁም የአመንዝራ ልጆች ናቸውና ለልጆችዋ አልራራም። እናታቸው አመንዝራለች፤ የፀነሰቻቸውም እርሷ አሳፋሪ ነገር አድርጋለች፤ ምክንያቱም፦ እንጀራዬንና ውኃዬን፥ ጥጤንና የተልባ እግሬን፥ ዘይቴንና መጠጤን ከሚሰጡኝ ከውሽሞቼ በኋላ እሄዳለሁ፥ ብላለችና። ስለዚህ፥ እነሆ፥ መንገድሽን በእሾህ እዘጋለሁ፤ መንገድዋንም እንዳታገኝ ቅጥርን እቀጥርባታለሁ። ውሽሞችዋንም ትከተላለች፥ ነገር ግን አትደርስባቸውም፤ ትፈልጋቸዋለችም፥ ነገር ግን አታገኛቸውም፤ እርሷም፦ ከዛሬ ይልቅ የዚያን ጊዜ ይሻለኝ ነበርና፥ ተመልሼ ወደ ቀደመው ባሌ እሄዳለሁ፥ ትላለች። እርሷም እህልንና ወይን ጠጅን ዘይትንም የሰጠኋት፥ ለበኣልም ያደረጉትን ብርና ወርቅ ያበዛሁላት እኔ እንደሆንኩ አላወቀችም። ስለዚህ እህሌን በጊዜው፥ ወይን ጠጄንም በወቅቱ ፈጽሞ እወስዳለሁ፥ ዕራቁትነትዋንም መሸፈኛ የነበረውን ጥጤንና የተልባ እግሬን እገፍፋታለሁ። እንዲሁም አሁን ውሽሞችዋ እያዩ ነውርዋን እገልጣለሁ፤ ከእጄም ማንም አያድናትም። ደስታዋንም ሁሉ፥ በዓላቶችዋንም፥ መባቻዎችዋንም፥ ሰንበቶችዋንም፥ የተቀደሱትንም ጉባኤዎችዋን ሁሉ አስቀራለሁ። እርሷም፦ “ውሽሞቼ ለእኔ የሰጡኝ ዋጋዬ ይህ ነው” ያለችውን ወይንዋንና በለስዋን አጠፋለሁ፤ ዱርም አደርገዋለሁ፥ የምድረ በዳም አራዊት ይበሉታል። በበኣሊም የበዓል ቀኖች ዕጣን ለእነርሱ በማጠንዋና ራስዋን በጉትቾችዋና በጌጥዋ በማስጌጥ ውሽሞችዋን ተከትላ እኔን በመርሳትዋ እቀጣታለሁ፥ ይላል ጌታ። ስለዚህ፥ እነሆ፥ አባብላታለሁ፥ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ፥ ለልብዋም እናገራለሁ። ከዚያም የወይን ቦታዎችዋን፥ የተስፋ በርም እንዲሆናት የአኮርን ሸለቆ እሰጣታለሁ፤ በዚያም ከግብጽ ምድር እንደ ወጣችበት ቀን እንደ ብላቴንነትዋ ወራት ትዘምራለች። “በዚያ ቀን፦ ‘ባሌ’ ብለሽ ትጠሪኛለሽ እንጂ ዳግመኛ፦ ‘በኣሌ’ ብለሽ አትጠሪኝም፥ ይላል ጌታ፤ የበኣሊምን ስም ከአፏ አስወግዳለሁና፥ ከእንግዲህም ወዲህ በስማቸው የሚያስታውሳቸው አይኖርም። በዚያም ቀን ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች በምድርም ላይ ከሚሳቡ ፍጥረቶች ጋር ቃል ኪዳን አደርግላቸዋለሁ፤ ቀስትንና ሰይፍን ጦርነትንም ከምድሪቱ አስወግዳለሁ፤ በደኅንነትም እንዲያርፉ አደርጋቸዋለሁ። ለዘለዓለምም ለእኔ እንድትሆኚ አጭሻለሁ፤ በጽድቅና በፍርድ፥ በምሕረትና በጽኑ ፍቅር ለእኔ አጭሻለሁ። ለእኔም እንድትሆኚ በታማኝነት አጭሻለሁ፤ አንቺም ጌታን ታውቂአለሽ። “እንዲህም ይሆናል፥ በዚያን ቀን እመልሳለሁ ይላል ጌታ፥ ለሰማይ እመልሳለሁ፥ ሰማይም ለምድር ይመልሳል፤