ሆሴዕ 13:1-16
ሆሴዕ 13:1-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኤፍሬም ሲናገር ሰዎች ተንቀጠቀጡ፤ በእስራኤልም የተከበረ ነበር፤ ነገር ግን በኣልን ስላመለከ በደለ፤ ሞተም። አሁንም ኀጢአትን መሥራት አበዙ፤ ብራቸውን አቅልጠው ለራሳቸው ጣዖት ሠሩ፣ በጥበብ የተሠሩ ምስሎችን አበጁ፤ ሁሉም የእጅ ጥበብ ባለሙያ ናቸው። ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ተብሏል፤ “ሰውን መሥዋዕት አድርገው ያቀርባሉ፤ የጥጃ ጣዖቶችንም ይስማሉ!” ስለዚህ እንደ ማለዳ ጉም፣ ፈጥኖ እንደሚጠፋ የጧት ጤዛ፣ ከዐውድማ እንደሚጠረግ እብቅ፣ በመስኮትም እንደሚወጣ ጢስ ይሆናሉ። “እኔ ግን ከግብጽ ምድር ያወጣሁህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አታውቅም፤ ከእኔም በቀር ሌላ አዳኝ የለም። በምድረ በዳ፣ በሐሩር ምድርም ተንከባከብሁህ። ካበላኋቸው በኋላ ጠገቡ፤ በጠገቡ ጊዜ ታበዩ፤ ከዚያም ረሱኝ። ስለዚህ እንደ አንበሳ እመጣባቸዋለሁ፤ እንደ ነብርም በመንገድ አደባባቸዋለሁ። ግልገሎቿን እንደ ተነጠቀች ድብ፣ እመታቸዋለሁ፤ እዘነጣጥላቸዋለሁ። እንደ አንበሳም ሰልቅጬ እውጣቸዋለሁ፤ የዱር አራዊትም ይገነጣጥላቸዋል። “እስራኤል ሆይ፤ በእኔ ላይ ስለ ተነሣህ፣ ረዳትህንም ስለ ተቃወምህ ትጠፋለህ። ‘ንጉሥንና አለቆችን ስጠኝ፤’ ብለህ እንደ ጠየቅኸው፣ ያድንህ ዘንድ ንጉሥህ የት አለ? በከተሞችህ ሁሉ የነበሩ ገዦችህስ የት አሉ? በቍጣዬ ንጉሥን ሰጠሁህ፤ በመዓቴም ሻርሁት። የኤፍሬም በደል ተከማችቷል፤ ኀጢአቱም በመዝገብ ተይዟል። በምጥ ላይ እንዳለች ሴት ጭንቅ ይመጣበታል፤ እርሱ ግን ጥበብ የሌለው ልጅ ነው፤ የሚወለድበት ጊዜ ሲደርስ፣ ከእናቱ ማሕፀን መውጣት የማይፈልግ ሕፃን ነው። “ከመቃብር ኀይል እታደጋቸዋለሁ፤ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ፤ ሞት ሆይ፤ መቅሠፍትህ የት አለ? መቃብር ሆይ፤ ማጥፋትህ የት አለ? “ከእንግዲህ ወዲህ አልራራለትም፤ በወንድሞቹ መካከል ቢበለጽግም እንኳ፣ የምሥራቅ ነፋስ ከምድረ በዳ እየነፈሰ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይመጣል፤ ምንጩ ይነጥፋል፤ የውሃ ጕድጓዱም ይደርቃል። የከበረው ሀብቱ ሁሉ፣ ከግምጃ ቤቱ ይበዘበዛል። የሰማርያ ሰዎች በደላቸውን ይሸከማሉ፤ በአምላካቸው ላይ ዐምፀዋልና። በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ሕፃኖቻቸውም በምድር ላይ ይፈጠፈጣሉ፤ የእርጉዝ ሴቶቻቸውም ሆድ ይቀደዳል።”
ሆሴዕ 13:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኤፍሬም በተናገረ ጊዜ ፍርሃት ነበረ፥ በእስራኤልም ዘንድ ታበየ፥ ነገር ግን በኣልን በማምለክ በበደለ ጊዜ ሞተ። አሁንም ኃጢአትን ይሠሩ ዘንድ ጨመሩ፥ በብራቸውም ለራሳቸው ቀልጦ የተሠራ ምስልን፥ እንደ ጥበባቸውም ጣዖታትን ሠርተዋል፥ ሁሉም የሠራተኛ ሥራ ናቸው። ስለ እነርሱም፦ የሚሠው ሰዎች እምቦሳውን ይሳሙ ይላሉ። ስለዚህም እንደ ማለዳ ደመና፥ በጥዋትም እንደሚያልፍ ጠል፥ በዐውሎ ነፍስም ከአውድማ እንደሚበተን እብቅ፥ ከመስኮትም እንደሚወጣ ጢስ ይሆናሉ። እኔ ግን ከግብጽ ምድር ጀምሬ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ አታውቅም፥ ከእኔም በቀር ሌላ መድኃኒት የለም። በምድረ በዳ፥ እጅግ በደረቀ ምድር አውቄህ ነበር። ከተሰማሩ በኋላ ጠገቡ፥ በጠገቡም ጊዜ ልባቸው ታበየ፥ ስለዚህ ረሱኝ። ስለዚህም እኔ እንደ አንበሳ ሆንሁባቸው፥ እንደ ነብርም በመንገድ አጠገብ አደባባቸዋለሁ፥ ልጅዋ እንደ ተነጠቀባት ድብ እገጥማቸዋለሁ፥ የልባቸውንም ስብ እቀድዳለሁ፥ በዚያም እንደ አንበሳ እበላቸዋለሁ፥ የምድረ በዳም አውሬ ይነጣጠቃቸዋል። እስራኤል ሆይ፥ በእኔ በረዳትህ ላይ በመነሣትህ ጥፋትህ ነው። በየከተማህ ሁሉ ያድንህ ዘንድ ንጉሥህ ወዴት አለ? ስለ እነርሱም፦ ንጉሥንና አለቆችን ስጠኝ ብለህ የተናገርኸው መሳፍንቶችህ ወዴት አሉ? በቁጣዬ ንጉሥን ሰጠሁህ፥ በመዓቴም ሻርሁት። የኤፍሬም በደል ታስሮአል፥ ኃጢአቱም ተከማችቶአል። ምጥ እንደ ያዛት ሴት ጭንቅ ይመጣበታል፥ በሚወለድበት ጊዜ በማኅፀን አፍ ቀጥ ብሎ አይወጣምና አእምሮ የሌለው ልጅ ነው። ከሲኦል እጅ እታደጋቸዋለሁ፥ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ፥ ሞት ሆይ፥ ቸነፈርህ ወዴት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ማጥፋትህ ወዴት አለ? ርኅራኄ ከዓይኔ ተሰወረች። በወንድሞቹ መካከል ፍሬያማ ቢሆን የምሥራቅ ነፋስ ይመጣል፥ የእግዚአብሔር ነፋስ ከምድረ በዳ ይመጣል፥ ምንጩንም ያደርቃል፥ ፈሳሹንም ያጠፋል፥ የተከበሩ ዕቃዎች ሁሉ ያሉበትን መዝገብ ይበዘብዛል። ሰማርያ በአምላክዋ ላይ ዐምፃለችና በደልዋን ትሸከማለች፥ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ሕፃኖቻቸውም ይፈጠፈጣሉ፥ እርጕዞቻቸውም ይቀደዳሉ።
ሆሴዕ 13:1-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የኤፍሬም ነገድ በእስራኤል ሕዝብ ላይ ከፍ ብሎ በነበረበት ዘመን ሲናገር የሚሰሙት ሁሉ ይንቀጠቀጡ ነበር፤ በኋላ ግን ባዓል ለተባለ ጣዖት በመስገድ ኃጢአት ስለ ሠራ በሞት ተቀጣ። አሁንም በጥበባቸው የቀለጡ ምስሎችና በብር የተሠሩ ጣዖቶችን በመሥራት በኃጢአት ላይ ኃጢአትን ይጨምራሉ፤ እነዚህ ሁሉ የሰው እጅ ሥራ ናቸው፤ ለእነዚህም የሰው እጅ ሥራዎች መሥዋዕት አቅርቡ ይላሉ፤ ሰዎችም በጥጃ መልክ የተሠሩ ጣዖቶችን ይሳለማሉ። በዚህም ምክንያት እነርሱ እንደ ማለዳ ጉም ተነው ይጠፋሉ፤ እንደ ጠዋት ጤዛም ይረግፋሉ፤ ከአውድማ ላይ በዐውሎ ነፋስ እንደሚጠረግ እብቅ ወይም በጢስ መውጫ ወጥቶ እንደሚያልቅ ጢስ ይሆናሉ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ አምላካችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የላችሁም፤ አዳኛችሁም እኔ ብቻ ነኝ። ድርቅ በበዛበት በረሓ እንክብካቤ ያደረግኹላችሁ እኔ ነኝ። ነገር ግን ወደ መልካሚቱ ምድር በገባችሁ ጊዜ እስክትጠግቡ በልታችሁ እጅግ ታበያችሁ፤ እኔንም ረሳችሁ። ከዚህ የተነሣ እንደ አንበሳና በመንገድ እንደሚያደባ ነብርም እሆንባችኋለሁ። ግልገሎችዋ የተወሰዱባት ድብ እንደምታደርግ እኔም አደጋ እጥልባችኋለሁ፤ እቦጫጭቃችሁማለሁ፤ እንደሚባላ አንበሳ እሆንባችኋለሁ፤ እንደሚበጣጥስ ክፉ አውሬም እበጣጥሳችኋለሁ። “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በእኔ በምረዳችሁ ላይ ስለ ተነሣችሁ አጠፋችኋለሁ፤ እናንተ ንጉሥና መሪዎች እንድሰጣችሁ ጠይቃችሁ ነበር፤ ታዲያ አሁን የሚያድናችሁ ንጉሥ፥ የሚከላከሉላችሁስ መሪዎች የት አሉ? በቊጣዬ ነገሥታትን ሰጥቻችሁ ነበር፤ ነገር ግን በከፍተኛ ቊጣዬ አጠፋኋቸው። “የእስራኤል ኃጢአትና በደል ተጽፎ ተከማችቶአል። እስራኤል በሕይወት የመኖር ተስፋ አለው፤ ነገር ግን የሚወለድበት ጊዜ ሲቃረብ ከእናቱ ማሕፀን ለመውጣት እንደማይፈልግ ሕፃን ሞኝ ሆኖአል። ከሲኦል ኀይል እታደጋቸዋለሁን? ከሞትስ አድናቸዋለሁን? ሞት ሆይ! መቅሠፍቶችህ የት አሉ? ሲኦል ሆይ! አጥፊነትህ የት አለ? እኔኮ አልራራላቸውም፤ በወንድሞቹ መካከል ፍሬያማ ቢሆንም የእግዚአብሔር ቅጣት የሆነው የምሥራቁ ነፋስ ከምድረ በዳ ተነሥቶ ይመጣል፤ ምንጩ ይቆማል፤ ወንዙም ይደርቃል። ነፋሱም የነበሩትን ውድ ዕቃዎች ሁሉ ገፎ ይወስድበታል። ሰማርያ በእኔ ላይ በማመፅዋ በሠራችው በደል ተጠያቂ ትሆናለች፤ ሕዝብዋም በጦርነት ይሞታሉ፤ ሕፃናት በምድር ላይ ይፈጠፈጣሉ፤ እርጉዞችም ሆዳቸው ይሰነጠቃል።”