ሆሴዕ 10:1-13

ሆሴዕ 10:1-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እስ​ራ​ኤል ፍሬው የበ​ዛ​ለት የለ​መ​ለመ ወይን ነው፤ እንደ ፍሬው ብዛት መሠ​ዊ​ያ​ዉን አብ​ዝ​ቶ​አል፤ እንደ ምድ​ሩም ማማር መጠን ሐው​ል​ቶ​ችን ሠር​ተ​ዋል። ልባ​ቸው ተከ​ፈለ፤ አሁ​ንም ይጠ​ፋሉ፤ እርሱ መሠ​ዊ​ያ​ቸ​ውን ያፈ​ር​ሳል፤ ሐው​ል​ቶ​ቻ​ቸ​ው​ንም ያጠ​ፋል። አሁ​ንም፥ “ንጉሥ የለ​ንም፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን አል​ፈ​ራ​ን​ምና፤ ንጉ​ሥስ ምን ያደ​ር​ግ​ል​ናል?” ይላሉ። የማ​ይ​ረ​ባ​ውን የሐ​ሰት ቃል ይና​ገ​ራሉ፤ ቃል ኪዳ​ንም ያደ​ር​ጋሉ፤ ስለ​ዚህ መር​ዛም ሣር በእ​ርሻ ትልም ላይ እን​ደ​ሚ​በ​ቅል ፍርድ ይበ​ቅ​ል​ባ​ቸ​ዋል። የሰ​ማ​ርያ ሰዎች በቤ​ት​አ​ዌን እን​ቦሳ አጠ​ገብ ይኖ​ራሉ፤ ሕዝቡ ያለ​ቅ​ሱ​ለ​ታል፤ ክብ​ሩም ከእ​ርሱ ዘንድ ወጥ​ቶ​አ​ልና እን​ዳ​ዘ​ኑ​በት እን​ዲሁ በክ​ብሩ ደስ ይላ​ቸ​ዋል። ለን​ጉሡ ለኢ​ያ​ሪም እጅ መንሻ ይሆን ዘንድ አስ​ረው ወደ አሦር ይወ​ስ​ዱ​ታል፤ ኤፍ​ሬ​ምን እፍ​ረት ይይ​ዘ​ዋል፤ እስ​ራ​ኤ​ልም በም​ክሩ ያፍ​ራል። ሰማ​ርያ ንጉ​ሥ​ዋን እንደ ጥራጊ በውኃ ላይ ጣለ​ችው። የእ​ስ​ራ​ኤል ኀጢ​አት የሆ​ኑት የአ​ዎን የኮ​ረ​ብ​ታው መስ​ገ​ጃ​ዎች ይፈ​ር​ሳሉ፤ እሾ​ህና አሜ​ከ​ላም በመ​ሠ​ዊ​ያ​ዎ​ቻ​ቸው ላይ ይበ​ቅ​ላሉ፤ ተራ​ሮ​ች​ንም፥ “ክደ​ኑን፤ ኮረ​ብ​ቶ​ች​ንም፦ ውደ​ቁ​ብን” ይሉ​አ​ቸ​ዋል። እስ​ራ​ኤል ከጊ​ብዓ ዘመን ጀምሮ ኀጢ​አ​ትን ሠር​ቶ​አል፤ በዚ​ያም ጸን​ተ​ዋል፤ በጊ​ብዓ ላይ ጦር አይ​ደ​ር​ስ​ባ​ቸ​ው​ምን? መጥ​ቶም የዐ​መፅ ልጆ​ችን ገሠ​ጻ​ቸው፤ ስለ ሁለ​ቱም ኀጢ​አ​ቶ​ቻ​ቸው በገ​ሠ​ጻ​ቸው ጊዜ አሕ​ዛብ በላ​ያ​ቸው ይሰ​በ​ሰ​ቡ​ባ​ቸ​ዋል። ኤፍ​ሬ​ምም ቀን​በ​ርን እንደ ለመ​ደች ጊደር ነው፤ እኔ ግን በአ​ን​ገቱ ውበት እጫ​ን​በ​ታ​ለሁ፤ በኤ​ፍ​ሬም ላይ እጠ​ም​ድ​በ​ታ​ለሁ፤ ይሁ​ዳ​ንም እለ​ጕ​መ​ዋ​ለሁ፤ ያዕ​ቆ​ብም ለራሱ መን​ግ​ሥ​ትን ያስ​ተ​ካ​ክ​ላል። ለእ​ና​ንተ ጽድ​ቅን ዝሩ፤ የሕ​ይ​ወት ፍሬን ሰብ​ስቡ፤ የጥ​በ​ብ​ንም ብር​ሃን ለራ​ሳ​ችሁ አብሩ፤ የጽ​ድ​ቃ​ችሁ መከር እስ​ኪ​ደ​ርስ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ፈል​ጉት። ዐመ​ፅን ለምን ተከ​ላ​ችሁ? ኀጢ​አ​ት​ንስ ለምን አጨ​ዳ​ችሁ፤ የሐ​ሰ​ት​ንም ፍሬ በል​ታ​ች​ኋል፤ በሠ​ረ​ገ​ሎ​ች​ህና በሠ​ራ​ዊ​ትህ ብዛት ታም​ነ​ሃል።

ሆሴዕ 10:1-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እስራኤል የተንዠረገገ ወይን ነበር፤ ብዙ ፍሬም አፈራ፤ ፍሬው በበዛ መጠን፣ ብዙ መሠዊያዎችን ሠራ፤ ምድሩ በበለጸገ መጠን፣ የጣዖታት ማምለኪያ ዐምዶችን አስጌጠ። ልባቸው አታላይ ነው፤ ስለዚህም በደላቸውን ይሸከማሉ። እግዚአብሔር መሠዊያዎቻቸውን ያወድማል፤ የጣዖት ማምለኪያ ዐምዶቻቸውን ያፈራርሳል። እነርሱም፣ “እኛ ንጉሥ የለንም፤ እግዚአብሔርን አላከበርንምና፤ ንጉሥ ቢኖረንስ፣ ምን ሊያደርግልን ይችል ነበር?” ይላሉ። ከንቱ ተስፋ ይሰጣሉ፤ በሐሰት በመማል፣ ቃል ኪዳን ያደርጋሉ፤ ስለዚህም ፍርድ፣ በዕርሻ ውስጥ እንደሚገኝ መርዛማ ዐረም ይበቅላል። በሰማርያ የሚኖረው ሕዝብ፣ በቤትአዌን ስላለው የጥጃ ጣዖት ይፈራል፤ ሕዝቡም ያለቅስለታል፤ በክብሩ እጅግ ደስ ያላቸው ሁሉ፣ አመንዝራ ካህናትም እንደዚሁ ያለቅሱለታል፤ በምርኮ ከእነርሱ ተወስዷልና። ለታላቁ ንጉሥ እንደ እጅ መንሻ፣ ወደ አሦር ይወሰዳል፤ ኤፍሬም ይዋረዳል፤ እስራኤልም ስለ ጣዖቱ ያፍራል። ሰማርያና ንጉሧ፣ በውሃ ላይ እንዳለ ኵበት ተንሳፍፈው ይጠፋሉ። የእስራኤል ኀጢአት የሆነው፣ የአዌን ማምለኪያ ኰረብታ ይጠፋል፤ እሾኽና አሜከላ ይበቅልባቸዋል፤ መሠዊያዎቻቸውንም ይወርሳል፤ በዚያ ጊዜ ተራሮችን፣ “ውደቁብን!” ኰረብቶችንም፣ “ሸፍኑን!” ይላሉ። “እስራኤል ሆይ፤ ከጊብዓ ጊዜ ጀምሮ ኀጢአት ሠራችሁ፤ በዚያም ጸናችሁ፤ በጊብዓ የነበሩትን ክፉ አድራጊዎች፣ ጦርነት አልጨረሳቸውምን? በፈለግሁ ጊዜ እቀጣቸዋለሁ፤ ስለ ድርብ ኀጢአታችሁም ይቀጧቸው ዘንድ፣ በእነርሱ ላይ ይሰበሰባሉ፤ ኤፍሬም ማበራየት እንደምትወድድ፣ እንደ ተገራች ጊደር ነው፤ በተዋበ ጫንቃዋም ላይ፣ ቀንበርን አኖራለሁ፤ ኤፍሬምን እጠምዳለሁ፤ ይሁዳ ያርሳል፤ ያዕቆብም መሬቱን ያለሰልሳል። ለራሳችሁ ጽድቅን ዝሩ፤ የጽኑ ፍቅርን ፍሬ ዕጨዱ፤ ዕዳሪውንም መሬት ዕረሱ፤ እርሱም መጥቶ፣ ጽድቅን በላያችሁ እስኪያዘንብ ድረስ፣ እግዚአብሔርን የምትፈልጉበት ጊዜ ነውና። እናንተ ግን ክፋትን ዘራችሁ፤ ኀጢአትንም ዐጨዳችሁ፤ የሐሰትንም ፍሬ በላችሁ። በራሳችሁ ጕልበት፣ በተዋጊዎቻችሁም ብዛት ታምናችኋልና፣

ሆሴዕ 10:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እስራኤል ፍሬው የበዛለት የለመለመ ወይን ነው፥ እንደ ፍሬው ብዛት መሠዊያውን አብዝቶአል፥ እንደ ምድሩም ማማር መጠን ሐውልቶችን እያሳመሩ ሠርተዋል። ልባቸው ተከፈለ፥ አሁንም በደላቸውን ይሸከማሉ፥ እርሱ መሠዊያቸውን ያፈርሳል፥ ሐውልቶቻቸውን ያጠፋል። አሁንም፦ ንጉሥ የለንም፥ እግዚአብሔርን አልፈራንምና፥ ንጉሥስ ምን ያደርግልናል? ይላሉ። የማይረባውን ቃል ይናገራሉ፥ ቃል ኪዳን በገቡ ጊዜ በሐሰት ይምላሉ፥ ስለዚህ መርዛም ሣር በእርሻ ትልም ላይ እንደሚበቅል መቅሠፍት ይበቅልባቸዋል። የሰማርያ ሰዎች ስለ ቤትአዌን እምቦሳ ይፈራሉ፥ ክብሩም ከእርሱ ዘንድ ወጥቶአልና ሕዝቡ ያለቅሱለታል፥ የጣዖቱ ካህናትም በኀዘን ይንተባተባሉ። ለንጉሡ ለኢያሪም እጅ መንሻ ይሆን ዘንድ ወደ አሦር ይማረካል፥ ኤፍሬምን እፍረት ይይዘዋል፥ እስራኤልም በምክሩ ያፍራል። ሰማርያ ከንጉሥዋ ጋር በውኃ ላይ እንዳለ አረፋ ጠፍታለች። የእስራኤል ኃጢአት የሆኑት የአዌን የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፥ እሾህና አሜከላ በመሠዊያዎቻቸው ላይ ይበቅላል፥ ተራሮችንም፦ ክደኑን፥ ኮረብቶችንም፦ ውደቁብን ይሉአቸዋል። እስራኤል ሆይ፥ ከጊብዓ ዘመን ጀምረህ ኃጢአትን ሠርተሃል፥ በዚያ ጸንተዋል፥ በጊብዓ ላይ ሰልፍ አይደርስባቸውምን? በፈቀድሁም ጊዜ እገሥጻቸዋለሁ፥ ስለ ሁለቱም ኃጢአታቸው በታሰሩ ጊዜ አሕዛብ ይሰበሰቡባቸዋል። ኤፍሬም ማበራየት እንደ ለመደች ጊደር ነው፥ እኔ ግን በአንገቱ ውበት እጫንበታለሁ፥ በኤፍሬም ላይ እጠምድበታለሁ፥ ይሁዳም ያርሳል፥ ያዕቆብም አፈሩን ያለሰልሳል። እግዚአብሔር መጥቶ ጽድቅን እስኪያዘንብላችሁ ድረስ እርሱን የምትሹበት ዘመን ነውና ለእናንተ በጽድቅ ዝሩ፥ እንደ ምሕረቱም መጠን እጨዱ፥ ጥጋታችሁንም እረሱ። ክፋትን አርሳችኋል፥ ኃጢአትንም አጭዳችኋል፥ የሐሰትንም ፍሬ በልታችኋል፥ በኃያላንህ ብዛት፥ በመንገድህም ላይ ታምነሃልና።

ሆሴዕ 10:1-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

የእስራኤል ሕዝብ ብዙ ዘለላ እንደ ያዘ የወይን ተክል ናቸው፤ ፍሬ በበዛላቸው መጠን ብዙ የጣዖት መሠዊያዎችን ሠሩ፤ ምድራቸው ፍሬያማ ሆና በበለጸገችላቸው መጠን የጣዖት መስገጃ ዐምዶችን አስጊጠው ሠሩ። ልባቸው በተንኰል የተሞላ ነው፤ የበደላቸውንም ዋጋ ያገኛሉ፤ እግዚአብሔር መሠዊያዎቻቸውን ሁሉ ይሰባብራል፤ የጣዖት መስገጃ ዐምዶቻቸውንም ያፈራርሳል። ሕዝቡ “እግዚአብሔርን መፍራት ስለ ተውን ንጉሥ አጥተናል፤ ንጉሥ ቢኖረንስ ምን ያደርግልናል?” ይላሉ። በሐሰት መሐላ ቃል ኪዳን በመግባት ከንቱ ንግግር ይናገራሉ፤ ስለዚህ በእርሻ መሬት ውስጥ መርዘኛ አረም እንደሚበቅል በእነርሱም መካከል ክርክር ይስፋፋል። በሰማርያ ከተማ የሚኖሩ ሕዝቦች በቤትአዌን ስላለው በጥጃ ምስል በተሠራ ጣዖት በታላቅ ፍርሀት ይርበደበዳሉ፤ ክብሩ ስለ ተገፈፈ ሕዝቡ ያለቅሳሉ፤ የጣዖቱ ካህናትም እሪ ብለው ይጮኻሉ። ጣዖቱ ወደ አሦር በመወሰድ ለታላቁ ንጉሥ እጅ መንሻ ሆኖ ይቀርባል፤ እስራኤል ከተከተለው ክፉ ምክር የተነሣ ኀፍረትና ውርደት ይደርስበታል። የሰማርያ ንጉሥ የውሃ ላይ ዐረፋ ሆኖ ይቀራል። የእስራኤል ሕዝብ አዌን በተባለ ከተማ ጣዖት በማምለክ ኃጢአት የሚሠሩባቸው ከፍተኛ ቦታዎች ይፈራርሳሉ፤ በመሠዊያዎቻቸውም ላይ እሾኽና አሜከላ ይበቅሉባቸዋል፤ በዚያን ጊዜ ሕዝቡ ተራራዎችን “ደብቁን!” ኮረብቶችንም “ጋርዱን!” ይላሉ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ሕዝብ በጊብዓ ኃጢአት ከሠሩበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን ከማሳዘን አልተቈጠቡም፤ ስለዚህ በገባዖን ጦርነት ይነሣባቸዋል። እነዚህን ዐመፀኞች እቀጣቸዋለሁ፤ አሕዛብ ሁሉ ተሰብስበው በእነርሱ ላይ ይነሣሉ፤ ስለ ድርብ ኃጢአታቸውም ቅጣት ይደርስባቸዋል። “እስራኤል ማበራየት እንደምትወድ ጊደር ነበረች፤ ነገር ግን በተዋበ ጫንቃዋ ላይ ቀንበር እጭንበታለሁ፤ በዚህ ዐይነት ይሁዳ ያርሳል፤ የያዕቆብ ልጆች በሙሉ ተጠምደው መሬቱን ያለሰልሳሉ፤ እኔም ‘እንግዲህ ዕዳሪውን መሬት ዕረሱ፤ ጽድቅን ለራሳችሁ ዝሩ፤ የማይለዋወጥ ፍቅርን ሰብስቡ፤ እነሆ ወደ እኔ ወደ አምላካችሁ የምትመለሱበት ጊዜ አሁን ነው! እኔም መጥቼ ፍትሕን አሰፍንላችኋለሁ’ አልኩ። “እናንተ ግን በራሳችሁ ኀይልና በጀግኖቻችሁ ብዛት በመተማመናችሁ፥ ክፋትን ዘርታችሁ ግፍን ሰበሰባችሁ፤ ሐሰታችሁ ያስገኘውን ፍሬ በላችሁ።

ሆሴዕ 10:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እስራኤል ፍሬውን የሚሰጥ የተትረፈረፈ ወይን ነው፤ እንደ ፍሬው ብዛት መሠዊያዎችን አብዝቶአል፤ እንደ ምድሩም ብልጥግና መጠን ሐውልቶችን እያሳመሩ ሠርተዋል። ልባቸው ሐሰተኛ ነው፤ በደላቸውን አሁን ይሸከማሉ፤ ጌታ መሠዊያዎቻቸውን ይሰባብራል፥ ሐውልቶቻቸውን ያጠፋል። አሁንም፦ “ጌታን አልፈራንምና ንጉሥ የለንም፤ ንጉሥስ ለእኛ ምን ያደርግልናል?” ይላሉ። የማይረባውን ቃላት ተናገሩ፤ በሐሰት መሐላ ቃል ኪዳን አደረጉ፤ ስለዚህ መርዛም አረም በእርሻ ትልሞች ላይ እንደሚበቅል መቅሠፍት በቀለባቸው። የሰማርያ ሰዎች የቤትአዌንን እምቦሳ ፈሩ፤ ክብሩ ከእርሱ ተለይቶታልና ሕዝቡ ያለቅሱለታል፥ የጣዖቱ ካህናትም እሪ ብለው ይጮኹለታል። እርሱም ደግሞ ለታላቁ ንጉሥ እጅ መንሻ እንዲሆን ወደ አሦር ተማርኮ ይወሰዳል፤ ኤፍሬምን እፍረት ይይዘዋል፥ እስራኤልም በምክሩ ያፍራል። ሰማርያ ከንጉሥዋ ጋር በውኃ ላይ እንደሚሳፈፍ ስንጥር ትጠፋለች። የእስራኤል ኃጢአት የሆኑት የአዌን የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፤ እሾኽና አሜከላ በመሠዊያዎቻቸው ላይ ይበቅላል፤ እነርሱም ተራሮችን፦ “ሸፍኑን!” ኮረብቶችንም፦ “ውደቁብን!” ይሉአቸዋል። እስራኤል ሆይ! ከጊብዓ ዘመን ጀምረህ ኃጢአትን ሠርተሃል፤ በዚያ ጸንተዋል፤ በዓመፀኛ ልጆች ላይ በጊብዓ ጦርነት አይደርስባቸውምን? በፈቀድሁም ጊዜ እገሥጻቸዋለሁ፤ እጥፍ ስለ ሆነው በደላቸው በታሰሩ ጊዜ አሕዛብ በእነርሱ ላይ ይሰበሰቡባቸዋል። ኤፍሬም ማበራየት የምትወድ የተገራች ጊደር ነበር፥ እኔም በውብ አንገትዋ ላይ አልጫንኩባትም፤ በኤፍሬም ላይ እጠምድበታለሁ፥ ይሁዳም ያርሳል፥ ያዕቆብም ለራሱ አፈሩን ያለሰልሳል። ጌታ መጥቶ ጽድቅን እስኪያዘንብላችሁ ድረስ እርሱን የመሻት ዘመን ነውና ጽድቅን ለራሳችሁ ዝሩ፥ የጽኑ ፍቅርን ፍሬ ሰብስቡ፥ ያልታረሰ መሬታችሁን እረሱ። ክፋትን አርሳችኋል፥ ኃጢአትንም አጭዳችኋል፥ የሐሰትንም ፍሬ በልታችኋል፤ በኃያላንህ ብዛት፥ በመንገድህም ላይ ታምነሃልና።