ሆሴዕ 1:2-5
ሆሴዕ 1:2-5 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወደ ሆሴዕ የመጣ የእግዚአብሔር የቃሉ መጀመሪያ ይህ ነው፤ እግዚአብሔር ሆሴዕን፥ “ምድሪቱ ከእግዚአብሔር ርቃ ታመነዝራለችና ሂድ፤ ዘማዊቱን ሴትና የዘማዊቱን ልጆች ለአንተ ውሰድ” አለው። እርሱም ሄዶ የዴብላይምን ልጅ ጎሜርን አገባ፤ እርስዋም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅንም ወለደችለት። እግዚአብሔርም፥ “ከጥቂት ዘመን በኋላ የኢይዝራኤልን ደም በይሁዳ ቤት ላይ እበቀላለሁና፥ ከእስራኤልም ቤት መንግሥትን እሽራለሁና ስሙን ኢይዝራኤል ብለህ ጥራው፤ በዚያም ጊዜ እንዲህ ይሆናል፤ በኢይዝራኤል ሸለቆ ውስጥ የእስራኤልን ቀስት እሰብራለሁ” አለው።
ሆሴዕ 1:2-5 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር በሆሴዕ መናገር በጀመረ ጊዜ፣ እግዚአብሔር “ምድሪቱ ከእግዚአብሔር ተለይታ ታላቅ ምንዝርና እያደረገች ስለ ሆነ፣ ሄደህ አመንዝራ ሴት አግባ፤ የምንዝርና ልጆችንም ለራስህ ውሰድ” አለው። ስለዚህ እርሱ የዴቤላይምን ሴት ልጅ ጎሜርን አገባ፤ እርሷም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደችለት። እግዚአብሔርም ሆሴዕን እንዲህ አለው፤ “በኢይዝራኤል ስለ ተፈጸመው ግድያ የኢዩን ቤት በቅርቡ ስለምቀጣና የእስራኤልንም መንግሥት እንዲያከትም ስለማደርግ፣ ስሙን ኢይዝራኤል ብለህ ጥራው። በዚያም ቀን በኢይዝራኤል ሸለቆ፣ የእስራኤልን ቀስት እሰብራለሁ።”
ሆሴዕ 1:2-5 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔር መጀመሪያ በሆሴዕ በተናገረ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ሆሴዕን፦ ምድሪቱ ከእግዚአብሔር ርቃ ታላቅ ግልሙትና ታደርጋለችና ሂድ፥ ጋለሞታን ሴትና የግልሙትናን ልጆች ለአንተ ውሰድ አለው። እርሱም ሄዶ የዴቤላይምን ልጅ ጎሜርን አገባ፥ እርስዋም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደችለት። እግዚአብሔርም፦ ከጥቂት ዘመን በኋላ የኢይዝራኤልን ደም በኢዩ ቤት ላይ እበቀላለሁና፥ ከእስራኤልም ቤት መንግሥትን እሽራለሁና ስሙን ኢይዝራኤል ብለህ ጥራው፥ በዚያም ቀን በኢይዝራኤል ሸለቆ ውስጥ የእስራኤልን ቀስት እሰብራለሁ አለው።
ሆሴዕ 1:2-5 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር በሆሴዕ አማካይነት ለእስራኤል ሕዝብ ቃሉን ማስተላለፍ ሲጀምር ሆሴዕን እንዲህ አለው፦ “ሕዝቤ ከእኔ ተለይቶ አጸያፊ የሆነ የዝሙት ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል፤ እንግዲህ አንተም ሂድና ዘማዊት ሴት አግባ፤ ከእርስዋም የዝሙት ልጆችን ውለድ።” ስለዚህ ሆሴዕ ሄዶ የዲብላይምን ልጅ ጎሜርን አገባ፤ እርስዋም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደችለት። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሆሴዕን እንዲህ አለው፦ “ኢዩና ዘሮቹ በኢይዝራኤል በገደሉአቸው ሰዎች ምክንያት የኢዩን ቤተሰብ የምቀጣበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፤ የእስራኤልም መንግሥት እንዲያከትም አደርጋለሁ፤ በዚያን ጊዜ በኢይዝራኤል ሸለቆ የእስራኤልን ጦር እደመስሳለሁ፤ ስለዚህ የልጅህን ስም ‘ኢይዝራኤል’ ብለህ ጥራው።”
ሆሴዕ 1:2-5 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታ መጀመሪያ በሆሴዕ በተናገረ ጊዜ፥ ጌታ ሆሴዕን፦ “ምድሪቱ ከጌታ ርቃ ታላቅ ዝሙት አድርጋለችና ሂድ፤ አመንዝራን ሴት ውሰድና አግባ፤ የዝሙትም ልጆች ይኑሩህ፥” አለው። እርሱም ሄዶ የዴቤላይምን ልጅ ጎሜርን አገባ፤ እርሷም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደችለት። ጌታም እንዲህ አለው፦ “ከጥቂት ዘመን በኋላ የኢይዝራኤልን ደም በኢዩ ቤት ላይ እበቀላለሁና፥ ከእስራኤልም ቤት መንግሥትን እሽራለሁና ስሙን ኢይዝራኤል ብለህ ጥራው፤ በዚያም ቀን በኢይዝራኤል ሸለቆ ውስጥ የእስራኤልን ቀስት እሰብራለሁ።”