ዕብራውያን 7:18-25
ዕብራውያን 7:18-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስለዚህም የምትደክም፥ የማትጠቅምም ስለ ሆነች የቀደመችው ትእዛዝ ተሽራለች። ኦሪት ምንም ግዳጅ አልፈጸመችምና፤ ነገር ግን በእርስዋ ፋንታ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ከእርስዋ የሚሻል ተስፋ ገብቶአል። እርሱ ያለ መሐላ አልሆነም፤ ያለ መሐላ የተሾሙ ካህናት አሉና። በመሐላ የሾመውን ግን፥ “እግዚአብሔር ማለ፥ አይጸጸትምም፤ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት የዘለዓለም ካህን ነህ” አለው። ኢየሱስ ይህን ያህል በምትበልጥና ከፍ ባለች ሹመት ተሾመ። ለእነዚያስ ብዙዎች ካህናት ነበሩአቸው፤ ሞት ይሽራቸው፥ እንዲኖሩም አያሰናበታቸውም ነበርና። እርሱ ግን ለዘለዓለም ይኖራል፤ ክህነቱ አይሻርምና። ዘወትር በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሊያድናቸው ይቻለዋል፤ ለዘለዓለምም ሕያው ነውና ያስታርቃቸዋል።
ዕብራውያን 7:18-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና የማይጠቅም በመሆኑ ተሽሯል፤ ሕጉ ማንንም ፍጹም ሊያደርግ ስለማይችል፣ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት የተሻለ ተስፋ መጥቷል። ይህ ያለ መሐላ አልሆነም። ሌሎች ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤ እርሱ ግን ካህን የሆነው በመሐላ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሮለታል፤ “ጌታ ማለ፤ አሳቡንም አይለውጥም፤ ‘አንተ ለዘላለም ካህን ነህ።’ ” ከዚህ መሐላ የተነሣ፣ ኢየሱስ ለተሻለ ኪዳን ዋስ ሆኗል። በአገልግሎታቸው እንዳይቀጥሉ ሞት ስለ ከለከላቸው፣ የቀድሞዎቹ ካህናት ቍጥራቸው ብዙ ነበር፤ ኢየሱስ ግን ለዘላለም የሚኖር በመሆኑ፣ ክህነቱ የማይሻር ነው። ስለዚህ ስለ እነርሱ እየማለደ ሁልጊዜ በሕይወት ስለሚኖር፣ በርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።
ዕብራውያን 7:18-25 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፥ ስለዚህም የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትእዛዝ ተሽራለች፥ ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋ ገብቶአል። እነርሱም ያለ መሐላ ካህናት ሆነዋልና፤ እርሱ ግን፦ ጌታ፦ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ አይጸጸትም ብሎ በተናገረለት ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና ያለ መሐላ ካህን እንዳልሆነ መጠን፥ እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።
ዕብራውያን 7:18-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና የማይጠቅም ስለ ሆነ ተሽሮአል በሙሴ ሕግ ምንም ነገር ፍጹም ሊሆን አልቻለም፤ አሁን ግን ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት የተሻለ ተስፋ ተሰጥቶናል። ከዚህም በቀር ይህ ክህነት ያለ እግዚአብሔር መሐላ አልሆነም፤ እነዚያ ከዚህ በፊት ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤ ኢየሱስ ግን ካህን የሆነው በእግዚአብሔር መሐላ ነው፤ ይህም፦ “እግዚአብሔር ‘አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ’ ብሎ ምሎአል፤ አይለውጥም” ተብሎ በተነገረለት መሠረት ነው። በዚህ መሐላ ምክንያት ኢየሱስ ለተሻለው ቃል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። በሞት ምክንያት አንድ ካህን ሳይለወጥ በሥራው ላይ ለዘለዓለም መኖር ስለማይችል የቀድሞዎቹ ካህናት ቊጥራቸው ብዙ ነበር፤ ኢየሱስ ግን ለዘለዓለም የሚኖር በመሆኑ ክህነቱ የማይለወጥ ነው። ስለዚህ እነርሱን ለማማለድ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ ስለሚኖር በእርሱ አማካይነት ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ሁሉ በፍጹም ሊያድናቸው ይችላል።
ዕብራውያን 7:18-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለዚህም ደካማና የማትጠቅም ስለ ሆነች፥ የቀደመችው ትእዛዝ ተሽራለች፤ ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፤ ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋ ተዋውቀናል። ከዚህም በቀር ይህ ክህነት ያለ መሐላ አልሆነም፤ እነዚያ ከዚህ በፊት ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤ እርሱ ግን ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና፤ “ጌታ ሐሳቡን አይቀይርም ‘አንተ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ፤’ ብሎ ምሏል፥፥” በዚህ መሐላ ምክንያት ኢየሱስ ለተሻለው ቃል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። በሞት ምክንያት በክህነት ሥራ ላይ ለመቆየት ስላልቻሉ፥ የቀድሞዎቹ ካህናት ቊጥራቸው ብዙ ነበር፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ለዚህም ነው፥ እነርሱን ሊያማልድ ዘወትር ይኖራልና፥ በእርሱ አማካይነት ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ሁሉ ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።