ዕብራውያን 7:15-22
ዕብራውያን 7:15-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ይልቁንም ይህ እጅግ ያስረዳል፤ በመልከ ጼዴቅ ክህነት አምሳል ሌላ ካህን ይነሣል ብሎአልና። ይኸውም በማያልፍ ሕይወት ኀይል እንጂ ለሥጋና ለደም በተሠራ ሕግ አይደለም። “እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት የዘለዓለም ካህን አንተ ነህ” ብሎ ይመሰክራልና። ስለዚህም የምትደክም፥ የማትጠቅምም ስለ ሆነች የቀደመችው ትእዛዝ ተሽራለች። ኦሪት ምንም ግዳጅ አልፈጸመችምና፤ ነገር ግን በእርስዋ ፋንታ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ከእርስዋ የሚሻል ተስፋ ገብቶአል። እርሱ ያለ መሐላ አልሆነም፤ ያለ መሐላ የተሾሙ ካህናት አሉና። በመሐላ የሾመውን ግን፥ “እግዚአብሔር ማለ፥ አይጸጸትምም፤ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት የዘለዓለም ካህን ነህ” አለው። ኢየሱስ ይህን ያህል በምትበልጥና ከፍ ባለች ሹመት ተሾመ።
ዕብራውያን 7:15-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንደ መልከ ጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን ቢነሣ ግን እኛ የተናገርነው ይበልጥ ግልጽ ይሆናል፤ እርሱ ካህን የሆነው በማይጠፋ የሕይወት ኀይል መሠረት እንጂ፣ እንደ ትውልዱ የሕግ ሥርዐት አይደለም፤ እንዲህ ተብሎ ተመስክሮለታል፤ “እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ።” የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና የማይጠቅም በመሆኑ ተሽሯል፤ ሕጉ ማንንም ፍጹም ሊያደርግ ስለማይችል፣ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት የተሻለ ተስፋ መጥቷል። ይህ ያለ መሐላ አልሆነም። ሌሎች ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤ እርሱ ግን ካህን የሆነው በመሐላ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሮለታል፤ “ጌታ ማለ፤ አሳቡንም አይለውጥም፤ ‘አንተ ለዘላለም ካህን ነህ።’ ” ከዚህ መሐላ የተነሣ፣ ኢየሱስ ለተሻለ ኪዳን ዋስ ሆኗል።
ዕብራውያን 7:15-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በማያልፍም ሕይወት ኃይል እንጂ በሥጋ ትእዛዝ ሕግ ሳይሆን ሌላ ካህን በመልከ ጼዴቅ ምሳሌ ቢነሳ፥ ይህ እጅግ አብልጦ የሚገለጥ ነው። አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ይመሰክራልና። ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፥ ስለዚህም የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትእዛዝ ተሽራለች፥ ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋ ገብቶአል። እነርሱም ያለ መሐላ ካህናት ሆነዋልና፤ እርሱ ግን፦ ጌታ፦ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ አይጸጸትም ብሎ በተናገረለት ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና ያለ መሐላ ካህን እንዳልሆነ መጠን፥ እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል።
ዕብራውያን 7:15-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይህ ነገር በጣም ግልጥ ሆኖ የሚገኘው እንደ መልከጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን በሚነሣበት ጊዜ ነው፤ እሱ የክህነት ሹመትን የተቀበለው ለሕይወቱ ፍጻሜ የሌለው በመሆኑ ነው እንጂ ከዘር በመጣ ሥርዓትና ሕግ አይደለም። “እንደ መልከጼዴቅ የክህነት ሹመት አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ” ተብሎ ተመስክሮለታል። የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና የማይጠቅም ስለ ሆነ ተሽሮአል በሙሴ ሕግ ምንም ነገር ፍጹም ሊሆን አልቻለም፤ አሁን ግን ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት የተሻለ ተስፋ ተሰጥቶናል። ከዚህም በቀር ይህ ክህነት ያለ እግዚአብሔር መሐላ አልሆነም፤ እነዚያ ከዚህ በፊት ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤ ኢየሱስ ግን ካህን የሆነው በእግዚአብሔር መሐላ ነው፤ ይህም፦ “እግዚአብሔር ‘አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ’ ብሎ ምሎአል፤ አይለውጥም” ተብሎ በተነገረለት መሠረት ነው። በዚህ መሐላ ምክንያት ኢየሱስ ለተሻለው ቃል ኪዳን ዋስ ሆኖአል።
ዕብራውያን 7:15-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ይህ ይበልጥ እንደ መልከጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን በሚነሣበት ጊዜ ግልጽ ይሆናል፤ እሱ የክህነት ሹመትን የተቀበለው በማያልፍም ሕይወት ኃይል እንጂ በሥጋ ትእዛዝ ሕግ አይደለም። ስለ እርሱ “እንደ መልከጼዴቅ የክህነት ሹመት አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ” ተብሎ ተመስክሮለታል። ስለዚህም ደካማና የማትጠቅም ስለ ሆነች፥ የቀደመችው ትእዛዝ ተሽራለች፤ ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፤ ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋ ተዋውቀናል። ከዚህም በቀር ይህ ክህነት ያለ መሐላ አልሆነም፤ እነዚያ ከዚህ በፊት ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤ እርሱ ግን ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና፤ “ጌታ ሐሳቡን አይቀይርም ‘አንተ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ፤’ ብሎ ምሏል፥፥” በዚህ መሐላ ምክንያት ኢየሱስ ለተሻለው ቃል ኪዳን ዋስ ሆኖአል።