ዕብራውያን 7:11-28 - Compare All Versions
ዕብራውያን 7:11-28 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
ፍጹምነት የተገኘውና ሕጉ ለሕዝቡ የተሰጠው በሌዊ ክህነት መሠረት ቢሆን ኖሮ፣ እንደ አሮን ሳይሆን እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ያለው ሌላ ካህን መምጣቱ ለምን አስፈለገ? የክህነት ለውጥ ካለ ሕጉም ሊለወጥ ግድ ነውና። ይህ ሁሉ የተነገረለት እርሱ ከሌላ ነገድ ነው፤ ከዚያም ነገድ በመሠዊያ ያገለገለ ማንም የለም። ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደ መጣ ግልጽ ነውና፤ ሙሴ ስለ ካህናት ሲናገር ይህን ነገድ አስመልክቶ የተናገረው ምንም ነገር የለም። እንደ መልከ ጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን ቢነሣ ግን እኛ የተናገርነው ይበልጥ ግልጽ ይሆናል፤ እርሱ ካህን የሆነው በማይጠፋ የሕይወት ኀይል መሠረት እንጂ፣ እንደ ትውልዱ የሕግ ሥርዐት አይደለም፤ እንዲህ ተብሎ ተመስክሮለታል፤ “እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ።” የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና የማይጠቅም በመሆኑ ተሽሯል፤ ሕጉ ማንንም ፍጹም ሊያደርግ ስለማይችል፣ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት የተሻለ ተስፋ መጥቷል። ይህ ያለ መሐላ አልሆነም። ሌሎች ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤ እርሱ ግን ካህን የሆነው በመሐላ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሮለታል፤ “ጌታ ማለ፤ አሳቡንም አይለውጥም፤ ‘አንተ ለዘላለም ካህን ነህ።’ ” ከዚህ መሐላ የተነሣ፣ ኢየሱስ ለተሻለ ኪዳን ዋስ ሆኗል። በአገልግሎታቸው እንዳይቀጥሉ ሞት ስለ ከለከላቸው፣ የቀድሞዎቹ ካህናት ቍጥራቸው ብዙ ነበር፤ ኢየሱስ ግን ለዘላለም የሚኖር በመሆኑ፣ ክህነቱ የማይሻር ነው። ስለዚህ ስለ እነርሱ እየማለደ ሁልጊዜ በሕይወት ስለሚኖር፣ በርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። እንግዲህ ለእኛ የሚያስፈልገን፣ ቅዱስ፣ ነቀፋ የሌለበት፣ ንጹሕ፣ ከኀጢአተኞች የተለየና ከሰማያት በላይ የከበረ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ነው። እርሱም እንደ ሌሎቹ ሊቃነ ካህናት መጀመሪያ ስለ ራሱ ኀጢአት፣ ከዚያም ስለ ሕዝቡ ኀጢአት በየቀኑ መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልገውም፤ ራሱን በሰጠ ጊዜ፣ ስለ ኀጢአታቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት አቅርቧልና። ሕጉ ደካማ የሆኑትን ሰዎች ሊቃነ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣው መሐላ ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ሾሟል።
ዕብራውያን 7:11-28 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
እንግዲህ ለሕዝቡ ሕግ የተሰጠው በሌዊ ክህነት መሠረት ነው፤ በዚህ በሌዋውያን ክህነት ፍጹምነት ቢገኝ ኖሮ የአሮን የክህነት ሹመት ሳይሆን የመልከ ጼዴቅ የክህነት ሹመት ያለው ሌላ ካህን መምጣት ባላስፈለገም ነበር፤ የክህነት ሐረጉ ሲለወጥ ሕጉም አብሮ መለወጥ አለበት። ይህ ሁሉ የተነገረለት ካህን ከሌላ ነገድ ነው፤ ከዚህ ነገድ ማንም ወደ መሠዊያው ቀርቦ ያገለገለ የለም። ጌታችን ከይሁዳ ነገድ መሆኑ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ሙሴ ስለ ካህናት ሲናገር የይሁዳን ነገድ አስመልክቶ የተናገረው ምንም ነገር የለም። ይህ ነገር በጣም ግልጥ ሆኖ የሚገኘው እንደ መልከጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን በሚነሣበት ጊዜ ነው፤ እሱ የክህነት ሹመትን የተቀበለው ለሕይወቱ ፍጻሜ የሌለው በመሆኑ ነው እንጂ ከዘር በመጣ ሥርዓትና ሕግ አይደለም። “እንደ መልከጼዴቅ የክህነት ሹመት አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ” ተብሎ ተመስክሮለታል። የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና የማይጠቅም ስለ ሆነ ተሽሮአል በሙሴ ሕግ ምንም ነገር ፍጹም ሊሆን አልቻለም፤ አሁን ግን ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት የተሻለ ተስፋ ተሰጥቶናል። ከዚህም በቀር ይህ ክህነት ያለ እግዚአብሔር መሐላ አልሆነም፤ እነዚያ ከዚህ በፊት ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤ ኢየሱስ ግን ካህን የሆነው በእግዚአብሔር መሐላ ነው፤ ይህም፦ “እግዚአብሔር ‘አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ’ ብሎ ምሎአል፤ አይለውጥም” ተብሎ በተነገረለት መሠረት ነው። በዚህ መሐላ ምክንያት ኢየሱስ ለተሻለው ቃል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። በሞት ምክንያት አንድ ካህን ሳይለወጥ በሥራው ላይ ለዘለዓለም መኖር ስለማይችል የቀድሞዎቹ ካህናት ቊጥራቸው ብዙ ነበር፤ ኢየሱስ ግን ለዘለዓለም የሚኖር በመሆኑ ክህነቱ የማይለወጥ ነው። ስለዚህ እነርሱን ለማማለድ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ ስለሚኖር በእርሱ አማካይነት ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ሁሉ በፍጹም ሊያድናቸው ይችላል። እንዲህ ያለው ቅዱስ፥ ነቀፋ የሌለበት፥ ንጹሕ፥ ከኃጢአተኞች የተለየ፥ ከሰማይ በላይ ከፍ ያለ የካህናት አለቃ ያስፈልገናል። እርሱ እንደ ሌሎቹ የካህናት አለቆች በመጀመሪያ ስለ ራሱ ኃጢአት፥ በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት በየቀኑ መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልገውም፤ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ባቀረበ ጊዜ ይህን ነገር በማያዳግም ሁኔታ ፈጽሞታል። ሕግ የካህናት አለቆች አድርጎ የሚሾማቸው ደካሞች ሰዎችን ነው፤ ከሕግ በኋላ የመጣው የመሐላ ቃል ግን ለዘለዓለም ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔርን ልጅ ሾሞአል።
ዕብራውያን 7:11-28 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
እንግዲህ ሕዝቡ በሌዊ ክህነት የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና በዚያ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ቢሆን፥ እንደ አሮን ሹመት የማይቈጠር፥ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ግን የሆነ ሌላ ካህን ሊነሣ ወደ ፊት ስለምን ያስፈልጋል? ክህነታቸው ታልፍ ዘንድ አላትና፤ ክህነታቸው ካለፈችም ኦሪታቸው ታልፋለች። ይህ ነገር የተነገረለት እርሱ በሌላ ወገን ተካፍሎአልና፥ ከዚያም መሠዊያውን ያገለገለ ማንም የለም። ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደ ወጣ የተገለጠ ነውና፤ ስለዚህም ነገድ ሙሴ ምንም እንኳን ስለ ክህነት አልተናገረም። ይልቁንም ይህ እጅግ ያስረዳል፤ በመልከ ጼዴቅ ክህነት አምሳል ሌላ ካህን ይነሣል ብሎአልና። ይኸውም በማያልፍ ሕይወት ኀይል እንጂ ለሥጋና ለደም በተሠራ ሕግ አይደለም። “እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት የዘለዓለም ካህን አንተ ነህ” ብሎ ይመሰክራልና። ስለዚህም የምትደክም፥ የማትጠቅምም ስለ ሆነች የቀደመችው ትእዛዝ ተሽራለች። ኦሪት ምንም ግዳጅ አልፈጸመችምና፤ ነገር ግን በእርስዋ ፋንታ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ከእርስዋ የሚሻል ተስፋ ገብቶአል። እርሱ ያለ መሐላ አልሆነም፤ ያለ መሐላ የተሾሙ ካህናት አሉና። በመሐላ የሾመውን ግን፥ “እግዚአብሔር ማለ፥ አይጸጸትምም፤ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት የዘለዓለም ካህን ነህ” አለው። ኢየሱስ ይህን ያህል በምትበልጥና ከፍ ባለች ሹመት ተሾመ። ለእነዚያስ ብዙዎች ካህናት ነበሩአቸው፤ ሞት ይሽራቸው፥ እንዲኖሩም አያሰናበታቸውም ነበርና። እርሱ ግን ለዘለዓለም ይኖራል፤ ክህነቱ አይሻርምና። ዘወትር በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሊያድናቸው ይቻለዋል፤ ለዘለዓለምም ሕያው ነውና ያስታርቃቸዋል። ቅዱስና ያለ ተንኰል፥ ነውርም የሌለበት፥ ከኀጢአተኞችም የተለየ፥ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባናል። እርሱም እንደ እነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኀጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኀጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና። ኦሪትስ የሚሞት ሰውን ሊቀ ካህናት አድርጋ ትሾማለች፤ ከኦሪት በኋላ የመጣው የእግዚአብሔር የመሐላ ቃሉ ግን ዘለዓለም የማይለወጥ ፍጹም ወልድን ካህን አድርጎ ሾመልን።
ዕብራውያን 7:11-28 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
እንግዲህ ህዝቡ በሌዊ ክህነት የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና በዚያ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ቢሆን፥ እንደ አሮን ሹመት የማይቍኦጠር፥ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ግን የሆነ ሌላ ካህን ሊነሳ ወደፊት ስለ ምን ያስፈልጋል? ክህነቱ ሲለወጥ፥ ሕጉ ደግሞ ሊለወጥ የግድ ነውና። ይህ ነገር የተነገረለት እርሱ በሌላ ወገን ተካፍሎአልና፥ ከዚያም መሠዊያውን ያገለገለ ማንም የለም፤ ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደወጣ የተገለጠ ነውና፥ ስለዚህም ነገድ ሙሴ ምንም እንኳ ስለ ክህነት አልተናገረም። በማያልፍም ሕይወት ኃይል እንጂ በሥጋ ትእዛዝ ሕግ ሳይሆን ሌላ ካህን በመልከ ጼዴቅ ምሳሌ ቢነሳ፥ ይህ እጅግ አብልጦ የሚገለጥ ነው። አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ይመሰክራልና። ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፥ ስለዚህም የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትእዛዝ ተሽራለች፥ ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋ ገብቶአል። እነርሱም ያለ መሐላ ካህናት ሆነዋልና፤ እርሱ ግን፦ ጌታ፦ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ አይጸጸትም ብሎ በተናገረለት ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና ያለ መሐላ ካህን እንዳልሆነ መጠን፥ እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና፤ እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና። ሕጉ ድካም ያላቸውን ሰዎች ሊቀ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣ የመሐላው ቃል ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ይሾማል።
ዕብራውያን 7:11-28 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
እንግዲህ በሌዊ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ከሆነ፥ ሕዝቡ በዚያ ላይ የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና፤ ወደ ፊት እንደ አሮን ሹመት የሚቆጠር ሳይሆን፥ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት የሆነ ሌላ ካህን ሊነሣ ስለምን ያስፈልጋል? ምክንያቱም ክህነቱ ሲለወጥ፥ ሕጉ ደግሞ ሊለወጥ ግድ ይላልና ነው። ይህ ነገር የተነገረለት እርሱ ከሌላ ነገድ ነው፤ ከዚያም ማንም ወደ መሠዊያው ቀርቦ ያገለገለ የለም። ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደ ወጣ የታወቀ ነው፤ ከዚያ ነገድ ጋር በተገናኘ ስለ ካህናት ሙሴ ምንም አልተናገረም። ይህ ይበልጥ እንደ መልከጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን በሚነሣበት ጊዜ ግልጽ ይሆናል፤ እሱ የክህነት ሹመትን የተቀበለው በማያልፍም ሕይወት ኃይል እንጂ በሥጋ ትእዛዝ ሕግ አይደለም። ስለ እርሱ “እንደ መልከጼዴቅ የክህነት ሹመት አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ” ተብሎ ተመስክሮለታል። ስለዚህም ደካማና የማትጠቅም ስለ ሆነች፥ የቀደመችው ትእዛዝ ተሽራለች፤ ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፤ ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋ ተዋውቀናል። ከዚህም በቀር ይህ ክህነት ያለ መሐላ አልሆነም፤ እነዚያ ከዚህ በፊት ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤ እርሱ ግን ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና፤ “ጌታ ሐሳቡን አይቀይርም ‘አንተ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ፤’ ብሎ ምሏል፥፥” በዚህ መሐላ ምክንያት ኢየሱስ ለተሻለው ቃል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። በሞት ምክንያት በክህነት ሥራ ላይ ለመቆየት ስላልቻሉ፥ የቀድሞዎቹ ካህናት ቊጥራቸው ብዙ ነበር፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ለዚህም ነው፥ እነርሱን ሊያማልድ ዘወትር ይኖራልና፥ በእርሱ አማካይነት ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ሁሉ ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። እንዲህ ያለው ቅዱስ፥ ነቀፋ የሌለበት፥ ንጹሕ፥ ከኃጢአተኞች የተለየ፥ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ ሊቀ ካህናት ሊኖረን ይገባል፤ እርሱ እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት፥ አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት፥ ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ማቅረብ አያስፈልገውም፤ ይህን ራሱን ባቀረበ ጊዜ አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎታል። ሕጉ ሰዎችን ድካም እያላቸው ሊቀ ካህናት አድርጎ ይሾማል፤ ከሕግ በኋላ የመጣ የመሐላው ቃል ግን፥ ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ሾመልን።