ዕብራውያን 6:1-12
ዕብራውያን 6:1-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስለዚህም የክርስቶስን የነገሩን መጀመሪያ ትተን ወደ ፍጻሜው እንሂድ፤ እንግዲህ ደግሞ ሌላ መሠረት እንዳትሹ ዕወቁ፤ ይኸውም ከሞት ሥራ ለመመለስ፥ በእግዚአብሔርም ለማመን፥ ጥምቀትን፥ በአንብሮተ እድ መሾምን፥ የሙታንን ትንሣኤና የዘለዓለም ፍርድን ለመማር ነው። እግዚአብሔርም ቢፈቅድ ይህን ባደረግን ነበር። ነገር ግን አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን፥ ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን፥ ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን፥ መልካሙን የእግዚአብሔርን ቃል፥ የሚመጣውንም የዓለምን ኀይል የቀመሱትን፥ በኋላም የካዱትን እንደ ገና ለንስሓ እነርሱን ማደስ አይቻልም፤ ራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና፥ ያዋርዱትማልና። ምድርም በእርስዋ የሚወርደውን ዝናም ከጠጣች፥ ያንጊዜ ስለ እርሱ ያረሱላትን መላካም ቡቃያ ታበቅላለች፤ ከእግዚአብሔር ዘንድም በረከትን ታገኛለች። እሾህንና ኵርንችትን ብታወጣ ግን የተጣለች ናት፤ ለመርገምም የቀረበች ናት፤ ፍጻሜዋም ለመቃጠል ይሆናል። የተመረጣችሁ ወንድሞቻችን ሆይ፥ ምንም እንኳን እንዲህ ብንላችሁ ሕይወት ወዳለባት ትምህርት እንድትቀርቡ እንታመንባችኋለን። እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስለ አገለገላችሁ፥ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው ያደረጋችትሁን ሥራ፥ በስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዐመፀኛ አይደለምና። ነገር ግን ሁላችሁም በዚች ተስፋችሁ እንዲሁ ትጋታችሁን እስከ መጨረሻው ታሳዩ ዘንድ እንወዳለን። ዳተኞች እንዳትሆኑ በሃይማኖትና በትዕግሥት ተስፋቸውን የወረሱትን ሰዎች ምሰሉአቸው።
ዕብራውያን 6:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ ስለ ክርስቶስ የተሰጠውን የመጀመሪያ ትምህርት ትተን ወደ ብስለት እንሂድ፤ ከሞተ ሥራ ንስሓ ስለ መግባትና በእግዚአብሔር ስለ ማመን እንደ ገና መሠረትን አንጣል፤ እንዲሁም ስለ ጥምቀቶች፣ እጆችን ስለ መጫን፣ ስለ ሙታን ትንሣኤና ስለ ዘላለም ፍርድ ትምህርት እንደ ገና አንመሥርት። እግዚአብሔር ቢፈቅድ ይህን እናደርጋለን። አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን፣ ሰማያዊውን ስጦታ የቀመሱትን፣ ከመንፈስ ቅዱስ ተካፋዮች የሆኑትን፣ መልካሙን የእግዚአብሔር ቃልና የሚመጣውን ዓለም ኀይል የቀመሱትን፣ በኋላ ግን የካዱትን እንደ ገና ወደ ንስሓ መመለስ አይቻልም፤ ምክንያቱም እነርሱ ለገዛ ጥፋታቸው የእግዚአብሔርን ልጅ እንደ ገና ይሰቅሉታል፤ ያዋርዱታልም። ዘወትር በርሷ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣና ለሚያርሷትም ፍሬ የምትሰጥ መሬት ከእግዚአብሔር በረከትን ትቀበላለች። ነገር ግን እሾኽና አሜከላ የምታበቅል መሬት ዋጋ ቢስ ትሆናለች፤ መረገሚያዋም ተቃርቧል፤ መጨረሻዋም በእሳት መቃጠል ነው። ወዳጆች ሆይ፤ ምንም እንኳ እንደዚህ ብንናገርም፣ ከድነታችሁ ጋራ የተያያዘ ታላቅ ነገር እንዳላችሁ ርግጠኞች ነን። እግዚአብሔር ዐመፀኛ አይደለም፤ እርሱ ሥራችሁን እንዲሁም በፊትም ሆነ አሁን ቅዱሳንን በመርዳት ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም። የተሰጠው ተስፋ እስኪፈጸም ድረስ እያንዳንዳችሁ እንዲህ ያለውን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን። በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንድትሆኑ አንፈልግም።
ዕብራውያን 6:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለዚህ የክርስቶስን ነገር መጀመሪያ የሚናገረውን ቃል ትተን ወደ ፍጻሜ እንሂድ፤ መሠረትን ደግመን አንመሥርት፥ እርሱም ከሞተ ሥራ ንስሐና በእግዚአብሔር እምነት፥ ስለ ጥምቀቶችና እጆችንም ስለ መጫን ስለ ሙታንም ትንሣኤ ስለ ዘላለም ፍርድም ትምህርት ነው። እግዚአብሔርም ቢፈቅድ ይህን እናደርጋለን። አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱትን በኋላም የካዱትን እንደገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻል ነው፤ ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና ያዋርዱትማልና። ብዙ ጊዜ በእርስዋ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣ መሬት፥ ለሚያርሱአትም ደግሞ የምትጠቅምን አትክልት የምታበቅል፥ ከእግዚአብሔር በረከትን ታገኛለችና፤ እሾህና ኵርንችትን ግን ብታወጣ፥ የተጣለች ናት ለመረገምም ትቀርባለች፥ መጨረሻዋም መቃጠል ነው። ስለ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ምንም እንኳ እንዲሁ ብንናገር፥ አብልጦ የሚሻለውና ለመዳን የሚሆነው እንዲሆንላችሁ ተረድተናል። እግዚአብሔር፥ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፥ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና። በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ፥ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን።
ዕብራውያን 6:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንግዲህ ስለ ክርስቶስ የተሰጠውን የመጀመሪያ ትምህርት ትተን ፍጹም ወደህ ኦነው ትምህርት እንለፍ፤ ከሞተ ሥራ ንስሓ የመግባትንና በእግዚአብሔር የማመንን መሠረት እንደገና አንመሥርት፤ እንዲሁም የጥምቀትን፥ የእጅ መጫንን፥ ከሞት የመነሣትን፥ የዘለዓለም ፍርድን ትምህርት እንደገና አንመሥርት። እግዚአብሔር ቢፈቅድልን ይህን እናደርጋለን። እምነታቸውን የካዱትን ሰዎች ወደ ንስሓ መመለስ እንዴት ይቻላል? እነዚህ ሰዎች ከዚህ በፊት ብርሃን በርቶላቸው ነበር፤ ሰማያዊውንም ስጦታ ቀምሰው ነበር፤ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ተካፋዮች ሆነው ነበር፤ የእግዚአብሔርን መልካም ቃልና የሚመጣውን ዓለም ኀይል ቀምሰው ነበር፤ ከዚህ ሁሉ በኋላ እምነታቸውን ቢክዱ እነርሱ ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ እንደገና ስለሚሰቅሉትና በይፋ ስለሚያዋርዱት እነርሱን ወደ ንስሓ መመለስ አይቻልም። ብዙ ጊዜ በእርስዋ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣ ተክል ለተከለባትም ሰው ጥቅም የምትሰጥ መሬት ከእግዚአብሔር በረከትን ታገኛለች። እሾኽና አሜከላ ብታበቅል ግን ዋጋቢስ ትሆናለች፤ በቅርብ ጊዜም ትረገማለች፤ መጨረሻዋም በእሳት መቃጠል ነው። ተወዳጆች ሆይ! ይህን ብንናገርም እንኳ እናንተ መዳናችሁን በሚያመጣ የተሻለ አቋም ላይ ለመሆናችሁ እርግጠኞች ነን። እግዚአብሔር ቅን ፈራጅ ነው፤ ስለዚህ ሥራችሁንና በፊትም ሆነ አሁን ቅዱሳንን በመርዳት ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም። እናንተ ሁላችሁም በተስፋ የምትጠባበቁትን ነገር እስክትጨብጡ ድረስ ትጋታችሁን እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን፤ የምንመኘውም በእምነትና በትዕግሥት ጸንተው ተስፋ የተሰጣቸውን ነገር የሚወርሱትን ሰዎች እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንድትሆኑ አይደለም።
ዕብራውያን 6:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለዚህ የክርስቶስን የመጀመሪያ ትምህርት አልፈን ወደ ፍጻሜ እንሂድ፤ መሠረትን ደግመን አንመሥርት፤ እርሱም ከሞተ ሥራ ንስሓና በእግዚአብሔር እምነት፥ ስለ ጥምቀቶችና እጆችንም ስለ መጫን ስለ ሙታንም ትንሣኤ ስለ ዘላለም ፍርድም ነው። እግዚአብሔርም ቢፈቅድ ይህን እናደርጋለን። እንደዚህ ያሉ ሰዎች ወደ ንስሓ መመለስ እንዴት ይቻላል!? አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸው፥ ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱ፥ ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩ፥ መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና መጪውንም የዓለም ኃይል የቀመሱ፥ ከዚህ ሁሉ በኋላ ቢክዱ፥ እነርሱ ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ እንደገና ስለሚሰቅሉትና ስለሚያዋርዱት፥ አይቻልም። ብዙ ጊዜ በእርስዋ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣ መሬት፥ ለሚያርሱአትም ደግሞ የምትጠቅምን አትክልት የምታበቅል፥ ከእግዚአብሔር በረከትን ታገኛለችና፤ እሾህና ኩርንችትን ግን ብታወጣ፥ ጥቅም አይኖራትም፤ ለመረገምም ትቀርባለች፤ መጨረሻዋም መቃጠል ነው። ስለ እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ! ምንም እንኳ እንዲህ ብንናገር፥ አብልጦ የሚሻለውና ለመዳን የሚሆነው እንደሚሆንላችሁ እርግጠኝነት ይሰማናል። እግዚአብሔር፥ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፥ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዐመፀኛ አይደለምና። እናንተም ሁላችሁ በተስፋ የምትጠባበቁትን ነገር እስክትጨብጡ ድረስ ትጋታችሁን እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን፤ ያም በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንድትሆኑ አይደለም።