ዕብራውያን 5:11-14
ዕብራውያን 5:11-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፤ ጆሮዎቻችሁም ስለ ፈዘዙ በቃል ልንተረጕመው ጭንቅ ነው። መምህራን ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ ካመናችሁ ጀምሮ በትምህርት ላይ የቈያችሁ ስለ ሆነ፥ እስከ ዛሬም ገና የእግዚአብሔርን የቃሉን መጀመሪያ ትምህርት ሊያስተምሩአችሁ ትወዳላችሁ፤ ወተትንም ሊግቱአችሁ ትሻላችሁ፤ ጽኑ ምግብንም አይደለም። ወተትን የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለሆነ፥ የጽድቅን ቃል ሊያውቅ አይሻም። ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉዉን ለመለየት በሥራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።
ዕብራውያን 5:11-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ ጕዳይ የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፤ ነገር ግን ለመማር ዳተኛ ስለ ሆናችሁ ለማስረዳት አስቸጋሪ ነው። በዚህ ጊዜ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፣ ገና የእግዚአብሔርን ቃል የመጀመሪያ ትምህርት የሚያስተምራችሁ ሰው ያስፈልጋችኋል፤ የሚያስፈልጋችሁም ጠንካራ ምግብ ሳይሆን ወተት ነው። ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ፣ ከጽድቅ ትምህርት ጋራ ገና አልተዋወቀም። ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙን ከክፉው ለመለየት ራሳቸውን ላስለመዱ፣ ለበሰሉ ሰዎች ነው።
ዕብራውያን 5:11-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፥ ጆሮቻችሁም ስለ ፈዘዙ በቃል ልንተረጕመው ጭንቅ ነው። ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም። ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤ ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በስራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።
ዕብራውያን 5:11-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ ጉዳይ የምንናገረው ብዙ ነገር አለ፤ ነገር ግን የማስተዋል ችሎታችሁ አነስተኛ ስለ ሆነ ለማስረዳት አስቸጋሪ ነው። እስከ አሁን በነበረው ጊዜ እናንተ አስተማሪዎች መሆን በተገባችሁ ነበር፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል የመጀመሪያውን ትምህርት ሌላ ሰው እንደገና እንዲያስተምራችሁ ያስፈልጋል፤ በዚህ ዐይነት የሚያስፈልጋችሁ ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም። ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ መልካም ነገርን ከክፉ የመለየት ትምህርት አልተለማመደም። ጠንካራ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ግን መልካሙንና ክፉውን የመለየት ልምድ ያላቸው ትላልቅ ሰዎች ናቸው።
ዕብራውያን 5:11-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፤ ለማድመጥ በድንዛዜ ላይ ስለ ሆናችሁ፥ ለማስረዳት አስቸጋሪ ነው። እስከ አሁን በነበረው ጊዜ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ እንደገና የእግዚአብሔር ቃላት የመጀመሪያውን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ ሰው ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም። ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅም፤ ጠንካራ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ግን መልካሙንና ክፉውን የመለየት ልምድ ያላቸው ብስለት ያላቸው ሰዎች ናቸው።