ዕብራውያን 4:12-16
ዕብራውያን 4:12-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፤ የሚሠራም ሁለት ልሳን ካለው ሰይፍም ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስንም፥ ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፤ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል። እኛን በሚቈጣጠር በእርሱ በዐይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው እንጂ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም። እንግዲህ ወደ ሰማያት የወጣ ታላቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን፤ በእርሱ በማመን ጸንተን እንኑር። ሊቀ ካህናታችን ለድካማችን መከራ መቀበልን የማይችል አይደለምና፤ ነገር ግን ከብቻዋ ከኀጢአት በቀር እኛን በመሰለበት ሁሉ የተፈተነ ነው። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል፥ በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ፥ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።
ዕብራውያን 4:12-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል። ከእግዚአብሔር ዐይን የተሰወረ ምንም ፍጥረት የለም፤ ስለ ራሳችን መልስ መስጠት በሚገባን በርሱ ፊት ሁሉም ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው። እንግዲህ ወደ ሰማያት ያረገ ታላቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፣ እምነታችንን አጥብቀን እንያዝ። በድካማችን የማይራራልን ሊቀ ካህናት የለንምና፤ ነገር ግን እንደ እኛ በማንኛውም ነገር የተፈተነ ሊቀ ካህናት አለን፤ ይሁን እንጂ ምንም ኀጢአት አልሠራም። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበልና በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ፣ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።
ዕብራውያን 4:12-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም። እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ። ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።
ዕብራውያን 4:12-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነው፤ ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ ይልቅ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፥ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ የሚቈራርጥ ነው፤ በልብ ውስጥ የተሰወረውንም ሐሳብና ምኞት መርምሮ የሚፈርድ ነው። ከእግዚአብሔር ፊት የሚሰወር ምንም ፍጥረት የለም፤ በእርሱ ዐይን ፊት ሁሉ ነገር ግልጥና ዕርቃኑን ሆኖ የሚታይ ነው፤ እኛም መልስ መስጠት የሚገባን በእርሱ ፊት ነው። እንግዲህ ሰማያትን ዘልቆ ወደ ላይ ወደ ሰማይ የወጣ ታላቅ የካህናት አለቃ ስላለን እምነታችንን አጥብቀን እንያዝ፤ የካህናት አለቃውም የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ነው። እኛ ያለን የካህናት አለቃ በድካማችን ሊራራልን የሚችል ነው፤ እርሱ በሁሉ ነገር እንደ እኛ ተፈተነ፤ ሆኖም ምንም ኃጢአት አልሠራም። እንግዲህ ምሕረት እንድንቀበልና ርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ጸጋ እንድናገኝ ጸጋው ወደሚገኝበት ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ያለ አንዳች ፍርሀት እንቅረብ።
ዕብራውያን 4:12-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፤ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም አሳብና ትኩረት ይመረምራል፤ በፊቱም የሚሰወር ምንም ፍጥረት የለም፤ እኛ መልስ መስጠት በሚገባን ከእርሱ ፊት ሁሉ ነገር ግልጥና ዕርቃኑን ሆኖ የሚታይ ነው። እንግዲህ በሰማያት የወጣ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ። እኛ ያለን ሊቀ ካህናት በድካማችን ሊራራልን የሚችል ነው፤ እርሱ በሁሉ ነገር እንደ እኛ ተፈተነ፤ ሆኖም ምንም ኃጢአት አልሠራም። እንግዲህ ምሕረት እንድንቀበልና ርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ጸጋ እንድናገኝ፥ ጸጋው ወደሚገኝበት በመታመን እንቅረብ።