ዕብራውያን 11:33-40
ዕብራውያን 11:33-40 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እነርሱ በእምነት ተጋደሉ፤ ነገሥታትን ድል ነሡ፤ ጽድቅን አደረጉ፤ ተስፋቸውን አገኙ፤ የአናብስትንም አፍ ዘጉ ። የእሳት ኀይልን አጠፉ፤ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፤ ከድካማቸው በረቱ፤ በጦርነት ኀይለኞች ሆኑ፤ የባዕድ ጭፍሮችንም አባረሩ። ሴቶችም እንደ ትንሣኤ ቀን ተነሥተውላቸው ሙታኖቻቸውን ተቀበሉ፤ ተፈርዶባቸው የሞቱም አሉ፤ የምትበልጠውን ሕይወት ያገኙ ዘንድ ሊድኑ አልወደዱምና። የገረፉአቸው፥ የዘበቱባቸውና ያሠሩአቸው ወደ ወህኒ ያገቡአቸውም አሉ። በመጋዝ የሰነጠቁአቸው፥ በድንጋይ የወገሩአቸው፥ በሰይፍም ስለት የገደሉዋቸው አሉ፤ ማቅ፥ ምንጣፍና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ተጨነቁ፤ ተቸገሩ፤ መከራ ተቀበሉ፤ ተራቡ፥ ተጠሙም። ዓለም የማይገባቸው እነዚህ ናቸው፤ ዱር ለዱርና ተራራ ለተራራ፥ ዋሻ ለዋሻና ፍርኩታ ለፍርኩታም ዞሩ። እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ፥ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙም። ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ፥ እግዚአብሔር ስለ እኛ የምትበልጠውን አስቀድሞ በይኖአልና።
ዕብራውያን 11:33-40 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እነዚህ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፤ በቅን ፈረዱ፤ የተሰጠውን የተስፋ ቃል ተቀበሉ፤ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፤ የእሳትን ኀይል አጠፉ፤ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፤ ከድካማቸው በረቱ፤ በጦርነት ኀያል ሆኑ፤ ባዕዳን ወታደሮችን አባረሩ። ሴቶች፣ ሙታናቸው ተነሡላቸው። ሌሎቹ ደግሞ የተሻለውን ትንሣኤ ለማግኘት ሲሉ፣ መትረፍን ንቀው ለሞት ለሚዳርግ ሥቃይ ራሳቸውን ሰጡ፤ ከዚህም ነጻ ለመውጣት አልፈለጉም። አንዳንዶቹ መዘባበቻ ሆኑ፤ ተገረፉ። ሌሎቹ ደግሞ ታስረው ወደ ወህኒ ተጣሉ፤ በድንጋይ ተወገሩ፤ በመጋዝ ለሁለት ተሰነጠቁ፤ በሰይፍ ተወግተው ሞቱ፤ እየተጐሳቈሉ፣ እየተሰደዱና እየተንገላቱ የበግና የፍየል ቈዳ ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም ለእነርሱ አልተገባቻቸውምና። በየበረሓውና በየተራራው፣ በየዋሻውና በየጕድጓዱ ተንከራተቱ። እነዚህ ሁሉ ስለ እምነታቸው የተመሰከረላቸው ቢሆኑም፣ ከእነርሱ ማንም የተስፋውን ቃል የተቀበለ የለም፤ እግዚአብሔር ለእኛ የሚበልጥ ነገር ስላዘጋጀ፣ ያለ እኛ ፍጹማን ሊሆኑ አልቻሉምና።
ዕብራውያን 11:33-40 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ። ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ። እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና።
ዕብራውያን 11:33-40 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፤ በፍትሕ አስተዳደሩ፤ የተሰጣቸውንም ተስፋ አገኙ፤ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፤ የእሳትን ኀይል አጠፉ፤ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፤ ከደካማነት ወደ ብርቱነት ተለወጡ፤ በጦርነት ኀይለኞች ሆኑ፤ የወራሪ ጠላትን ወታደሮች አባረሩ፤ ሴቶች የሞቱባቸውን ዘመዶቻቸውን ከሞት ተነሥተው አገኘአቸው። ሌሎችም የበለጠ ትንሣኤ ለማግኘት አስበው ልዩ ልዩ ሥቃይ ተቀበሉ፤ ከእስራት ነጻ መሆንንም አልፈቀዱም። ሌሎች መዘባበቻ ሆነው ተገረፉ፤ ሌሎች በእግር ብረት ታስረው ወደ ወህኒ ቤት ተጣሉ፤ በድንጋይ ተወገሩ፤ በመጋዝ ተሰነጠቁ፤ በሰይፍ ተገደሉ፤ የበግና የፍየል ቆዳ ለብሰው ተንከራተቱ፤ ድኾችና ስደተኞች ሆነው ተንገላቱ፤ በበረሓ፥ በተራራ፥ በምድር ውስጥ ባሉ ዋሻዎችና ፈፋዎች ዞሩ። በዚህም ዐይነት ዓለም ለእነርሱ ተገቢ ስፍራ ሆና አልተገኘችም። እነዚህ ሁሉ ስለ እምነታቸው የተመሰከረላቸው ቢሆኑም የተሰጣቸውን ተስፋ ገና አላገኙም። እግዚአብሔር ለእኛ የተሻለ ነገር ዐቅዶአልና፤ ስለዚህ እነርሱ ከእኛ ጋር እንጂ ብቻቸውን ፍጹሞች መሆን አይችሉም።
ዕብራውያን 11:33-40 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፤ ጽድቅን አደረጉ፤ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፤ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፤ የእሳትን ኃይል አጠፉ፤ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፤ ከድካማቸው ብርቱ ሆኑ፤ በጦርነት ኀይለኞች ሆኑ፤ የባዕድ ወራሪዎችን አባረሩ። ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም የሚታደጓቸውን ሳይሹ የሚበልጠውን ትንሣኤ ለማግኘት እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ ሌሎችም መዘበቻ መሆንን፥ መገረፍን፥ ከዚህም በላይ እስራትንና ወኅኒን ቻሉ። በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፤ በመጋዝ ተሰነጠቁ፤ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፤ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ፥ እየተጨነቁ፥ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ። ዓለም አልተገባቸውምና፥ በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ። እነዚህም ሁሉ ስለ እምነታቸው የተመሰከረላቸው ቢሆኑም የተገባውን የተስፋ ቃል አላገኙም። ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ፥ እግዚአብሔር ለእኛ የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበር።