ዕብራውያን 1:1-14
ዕብራውያን 1:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዐይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ። በኋላ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገው፥ ሁሉንም በፈጠረበት በልጁ ነገረን። እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የመልኩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ ኀጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ፥ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ። በዚህን ያህል መብለጥ ከመላእክት በላይ ሆኖ ከስማቸው የሚበልጥና የሚከብር ስምን ወረሰ። ከመላእክትስ ከሆነ ጀምሮ፥ “አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወለድሁህ” ዳግመኛም፥ “እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጄ ይሆነኛል” ያለው ከቶ ለማን ነው? ዳግመኛም በኵርን ወደ ዓለም በላከው ጊዜ “የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይሰግዱለታል” አለ። ስለ መላእክቱም፥ “መላእክቱን ነፋሳት፥ የሚላኩትንም የእሳት ነበልባል የሚያደርጋቸው እርሱ ነው” አለ። ስለ ልጁ ግን፥ “ጌታ ሆይ፥ ዙፋንህ ለዘለዓለም ነው፤ የመንግሥትህ በትርም የጽድቅ በትር ነው” አለ። “ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃንም ጠላህ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር አምላክህ እንዳንተ ካሉት ይልቅ የሚበልጥ የደስታ ዘይትን ቀባህ።” ዳግመኛም እንዲህ አለ፥ “አቤቱ አንተ አስቀድሞ ምድርን መሠረትህ፤ ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ያልፋሉ፤ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁሉ እንደ ልብስ ያረጃል፤ እንደ መጋረጃም ትጠቀልላቸዋለህ፤ ይለወጣሉም፤ አንተ ግን መቼም መች አንተ ነህ፤ ዘመንህም የማይፈጸም ነው።” ከሆነ ጀምሮ ከመላእክት፥ “ጠላቶችህን ከእግርህ ጫማ በታች እስከ አደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” ማንን አለው? መላእክት ሁሉ መናፍስት አይደሉምን? የዘለዓለም ሕይወትን ይወርሱ ዘንድ ስለ አላቸው ሰዎችስ ለአገልግሎት ይላኩ የለምን?
ዕብራውያን 1:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በተለያየ ጊዜና በልዩ ልዩ መንገድ በነቢያት በኩል ለአባቶቻችን ተናግሮ፣ በዚህ መጨረሻ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገውና ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ ለእኛ ተናገረን። እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅና የባሕርዩ ትክክለኛ ምሳሌ ሆኖ፣ በኀያል ቃሉ ሁሉን ደግፎ ይዟል። የኀጢአት መንጻት ካስገኘ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ። ስለዚህ የወረሰው ስም ከመላእክት ስም እንደሚበልጥ ሁሉ፣ እርሱም ከመላእክት እጅግ የላቀ ሆኗል። እግዚአብሔር፣ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ፤” ወይስ ደግሞ፣ “እኔ አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል” ያለው ከመላእክት ከቶ ለማን ነው? ደግሞም እግዚአብሔር በኵሩን ወደ ዓለም ሲያስገባ፣ “የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይስገዱለት” ይላል። ስለ መላእክትም ሲናገር፣ “መላእክቱን ነፋሳት፣ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል ያደርጋል” ይላል። ስለ ልጁ ግን እንዲህ ይላል፤ “አምላክ ሆይ፤ ዙፋንህ ከዘላለም እስከ ዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ይሆናል። ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃን ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከባልንጀሮችህ በላይ አስቀመጠህ፣ የደስታንም ዘይት ቀባህ።” ደግሞም እንዲህ ይላል፤ “ጌታ ሆይ፤ አንተ በመጀመሪያ የምድርን መሠረት አኖርህ፤ ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ እንደ መጐናጸፊያ ትጠቀልላቸዋለህ፤ እንደ ልብስም ይለወጣሉ። አንተ ግን ያው አንተ ነህ፤ ዘመንህም ፍጻሜ የለውም።” እግዚአብሔር፣ “ጠላቶችህን ለእግርህ መረገጫ እስከማደርግልህ ድረስ፣ በቀኜ ተቀመጥ” ያለው ከመላእክት ከቶ ለማን ነው? መላእክት ሁሉ መዳንን የሚወርሱትን ለማገልገል የሚላኩ አገልጋይ መናፍስት አይደሉምን?
ዕብራውያን 1:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤ ከመላእክት ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ስምን በወረሰ መጠን እንዲሁ ከእነርሱ አብዝቶ ይበልጣል። ከመላእክትስ፦ አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፥ ደግሞም፦ እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ያለው ከቶ ለማን ነው? ደግሞም በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ፦ የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል። ስለ መላእክትም፦ መላእክቱን መናፍስት አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ ይላል፤ ስለ ልጁ ግን፦ አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው። ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ ይላል። ደግሞ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም ይላል። ነገር ግን ከመላእክት፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ ከቶ ለማን ብሎአል? ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?
ዕብራውያን 1:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር በቀድሞ ዘመናት በተለያዩ መንገዶች፥ በነቢያት አማካይነት ለአባቶቻችን ብዙ ጊዜ ተናግሮ ነበር፤ አሁን ግን በእነዚህ በኋለኞቹ ዘመናት ሁሉን ነገር ወራሽ ባደረገው በልጁ አማካይነት ለእኛ ተናገረን፤ ዓለምንም ሁሉ የፈጠረው በእርሱ ነው። እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅ ነው፤ እርሱ በባሕርዩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም ትክክል ነው። በኀያል ቃሉ ዓለምን ሁሉ ደግፎ ይዞአል፤ ሰዎችንም ከኃጢአት ካነጻ በኋላ በሰማይ በኀያሉ እግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦአል። ለእርሱ የተሰጠው ስም ከመላእክት ስም በላይ እንደ መሆኑ መጠን የእግዚአብሔር ልጅ ከመላእክት እጅግ በጣም የላቀ ነው። እግዚአብሔር ከቶ ከመላእክት መካከል፥ “አንተ ልጄ ነህ፤ ዛሬ ወልጄሃለሁ፤” ወይም “እኔ አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል” ያለው ማንን ነው? እግዚአብሔር የበኲር ልጁን ወደ ዓለም በላከ ጊዜ “የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይስገዱለት” ይላል። ስለ መላእክቱ ግን “መላእክቱን መናፍስት፥ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል ያደርጋል” ይላል። ስለ ልጁ ግን፥ “አምላክ ሆይ! ዙፋንህ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይኖራል፤ መንግሥትህንም በትክክል ታስተዳድራለህ፤ ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃንም ጠላህ፤ በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር አምላክህ መረጠህ፤ ከጓደኞችህም ይበልጥ ደስታን በሚሰጥ ቅባት ቀባህ” ይላል። እንዲሁም፥ “ጌታ ሆይ! አንተ በመጀመሪያ ምድርን መሠረትህ፤ ሰማያት የእጅህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱ ሁሉ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ትኖራለህ፤ እነርሱ ሁሉ እንደ ልብስ ያረጃሉ። እንደ መጐናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ፤ እነርሱም እንደ ልብስ ይለወጣሉ። አንተ ግን ሁልጊዜ ያው ነህ፤ ለዘመንህም ፍጻሜ የለውም” ይላል። እግዚአብሔር ከመላእክቱ መካከል፥ “ጠላቶችህን ከሥልጣንህ ሥር እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” ያለው ማንን ነው? ታዲያ፥ መላእክት ሁሉ የሚድኑትን ሰዎች ለማገልገል የሚላኩ የእግዚአብሔር አገልጋዮች የሆኑ መናፍስት አይደሉምን?
ዕብራውያን 1:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በብዙ እና በልዩ ልዩ መንገዶች ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፤ በእነዚህ በኋለኞቹ ዘመናት ግን፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ ለእኛ ተናገረን፥፥ እርሱም የክብሩ ጸዳልና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኀጢአታችንን ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤ ከመላእክት ይልቅ እጅግ የላቀ ስምን በተቀበለ መጠን፥ እንደዚሁ ከእነርሱ እጅግ ልቆ ይበልጣል። ከመላእክትስ፥ “አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፤” ደግሞም “እኔ አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤” ያለው ከቶ ለማን ነው? ደግሞም የበኲር ልጁን ወደ ዓለም በላከ ጊዜ “የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ፤” ይላል። ስለ መላእክትም “መላእክቱን ነፋሳት፥ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ” ይላል፤ ስለ ልጁ ግን፥ “አምላክ ሆይ! ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤ የጽድቅ በትር የመንግሥትህ በትር ነው። ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፅንም ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ፤” ይላል። እናም፥ “ጌታ ሆይ! አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ፤ ይለወጣሉም፤ አንተ ግን አንተ ነህ፤ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም፤” ነገር ግን ከመላእክት፥ “ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ፤” ከቶ ለማን ብሎአል? ታዲያ፥ መላእክት ሁሉ መዳንን ስለሚቀበሉ ሰዎች፥ ለአገልግሎት የሚላኩ አገልጋይ መናፍስት አይደሉምን?