ዕንባቆም 3:11-19 - Compare All Versions

ዕንባቆም 3:11-19 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)

ከሚወረወሩ ፍላጾችህ፣ ከሚያብረቀርቅ የጦርህ ነጸብራቅ የተነሣም፣ ፀሓይና ጨረቃ በቦታቸው ቆሙ። በምድር ላይ በመዓት ተመላለስህ፤ ሕዝቦችንም በቍጣ ረገጥሃቸው። ሕዝብህን ለመታደግ፣ የቀባኸውንም ለማዳን ወጣህ፤ የክፋትን ምድር መሪ ቀጠቀጥህ፤ ከራስ ጠጕሩ እስከ እግር ጥፍሩም ዕርቃኑን አስቀረኸው። ሴላ እንደ ዐውሎ ነፋስ ሊበታትነን የመጣውን፣ ምስኪኑን በስውር በመዋጥ የሚደሰተውን፣ የሰራዊት አለቃ ራስ፣ በገዛ ጦሩ ወጋህ። ታላላቅ ውሆችን በመናጥ፣ ባሕሩን በፈረሶችህ ረገጥህ። እኔ ሰማሁ፤ ልቤም ደነገጠብኝ፤ ከንፈሬ ከድምፁ የተነሣ ተንቀጠቀጠ፤ ፍርሀት እስከ ዐጥንቴ ዘልቆ ገባ፤ እግሬም ተብረከረከ፤ ሆኖም በሚወርረን ሕዝብ ላይ እስኪመጣ ድረስ፣ የጥፋትን ቀን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ። ምንም እንኳ የበለስ ዛፍ ባያፈራ፣ ከወይን ተክልም ፍሬ ባይገኝ፣ የወይራም ዛፍ ፍሬ ባይሰጥ፣ ዕርሻዎችም ሰብል ባይሰጡ፣ የበጎች ጕረኖ እንኳ ባዶውን ቢቀር፣ ላሞችም በበረት ውስጥ ባይገኙ፣ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በድነቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ። ጌታ እግዚአብሔር ኀይሌ ነው፤ እግሮቼን እንደ ዋላ እግሮች ያደርጋል፤ በከፍታዎችም ላይ ያስሄደኛል።

ዕንባቆም 3:11-19 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

እንደ ፍላጻ ከሚወረወረውና እንደ ጦር ከሚያንጸባርቀው መብረቅህ የተነሣ ፀሐይና ጨረቃ በየቦታቸው ቆሙ። በምድር ላይ ቆምክ፤ በቊጣህም ሕዝቦችን ረጋገጥካቸው። ሕዝብህን ለመታደግ፥ ቀብተህ ያነገሥከውንም ንጉሥ ለማዳን ወጣህ፤ የጥፋት አገር መሪ የሆነውን ቀጠቀጥከው፤ ተከታዮቹንም አጥፍተህ እርቃኑን አስቀረኸው። ከእግር እስከ ራሱም አራቈትከው። እኛን ለመበታተን እንደ ዐውሎ ነፋስ የመጣውን የጦረኞቹን አለቃ በገዛ ቀስቱ ወጋኸው። ደካማ እንስሶችን ለመቦጨቅ እንደሚጓጓ አውሬ እርሱም የተደበቁትን ድኾች ለማጥቃት የተዘጋጀ ነበር። አንተ ባሕሩን በፈረሶችህ በምትረጋግጥበት ጊዜ ጥልቁ ባሕር ይናወጣል። ይህን ሁሉ ስሰማ ሰውነቴ ይርበደበዳል፤ ድምፁም ከንፈሮቼን ያንቀጠቅጣል፤ አጥንቶቼ ይበሰብሳሉ፤ እግሮቼ ከታች ይብረከረካሉ፤ በጠላቶቻችን ላይ መከራ የሚደርስበትን ጊዜ በትዕግሥት እጠባበቃለሁ። ምንም እንኳ የበለስ ዛፍ ባያብብ፥ በወይን ተክል ላይም ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ዛፍም ምንም ፍሬ ባይሰጥ፥ በእርሻዎች ላይ ሰብል ቢጠፋ፥ የበግ መንጋዎች ሁሉ ቢያልቁ፥ በበረት ውስጥ ምንም ከብት ባይገኝ፥ ይህም ሁሉ ቢሆን፥ እኔ በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በአምላኬ፥ በመድኃኒቴ ሐሤት አደርጋለሁ። ጌታ እግዚአብሔር ብርታቴ ነው፤ እግሮቼንም እንደ ዋልያ እግሮች ያጠነክርልኛል፤ በተራሮችም ላይ እንድራመድ ያደርገኛል።

ዕንባቆም 3:11-19 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))

ፍላጾችህ ከወጡበት ብርሃን የተነሣ፥ ከሚንቦገቦገውም ከጦርህ ፀዳል የተነሣ፥ ፀሐይና ጨረቃ በመኖሪያቸው ቆሙ። በምድር ላይ በመዓት ተራመድህ፣ አሕዛብን በቍጣ አሄድሃቸው። ሕዝብህን ለመታደግ፥ የቀባኸውንም ለማዳን ወጣህ፣ የኃጢአተኛውን ቤት ራስ ቀጠቀጥህ፣ መሠረቱን እስከ አንገቱ ድረስ ገለጥህ። የአለቆችን ራስ በገዛ በትራቸው ወጋህ፣ እኔን ይበትኑ ዘንድ እንደ ዐውሎ ነፋስ መጡ፣ ችግረኛውን በስውር ለመዋጥ ደስታቸው ነው። ፈረሶችህን በባሕር፥ በብዙ ውኆችም ላይ አስረገጥህ። እኔ ሰምቻለሁ፥ ልቤም ደነገጠብኝ፣ ከድምፁ የተነሣ ከንፈሮቼ ተንቀጠቀጡ፣ መንቀጥቀጥ ወደ አጥንቶቼ ውስጥ ገባ፣ በስፍራዬ ሆኜ ተናወጥሁ፣ በሚያስጨንቁን ሕዝብ ላይ እስኪመጣ ድረስ የመከራን ቀን ዝም ብዬ እጠብቃለሁ። ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፥ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ሥራ ቢጐድል፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፥ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፥ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፣ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ። ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌ ነው፣ እግሮቼን እንደ ዋላ እግሮች ያደርጋል፣ በከፍታዎችም ላይ ያስሄደኛል።

ዕንባቆም 3:11-19 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))

ፍላጾችህ ከወጡበት ብርሃን የተነሣ፥ ከሚንቦገቦገውም ከጦርህ ፀዳል የተነሣ፥ ፀሐይና ጨረቃ በመኖሪያቸው ቆሙ። በምድር ላይ በመዓት ተራመድህ፥ አሕዛብን በቍጣ አሄድሃቸው። ሕዝብህን ለመታደግ፥ የቀባኸውንም ለማዳን ወጣህ፥ የኃጢአተኛውን ቤት ራስ ቀጠቀጥህ፥ መሠረቱን እስከ አንገቱ ድረስ ገለጥህ። የአለቆችን ራስ በገዛ በትራቸው ወጋህ፥ እኔን ይበትኑ ዘንድ እንደ ዐውሎ ነፋስ መጡ፥ ችግረኛውን በስውር ለመዋጥ ደስታቸው ነው። ፈረሶችህን በባሕር፥ በብዙ ውኆችም ላይ አስረገጥህ። እኔ ሰምቻለሁ፥ ልቤም ደነገጠብኝ፥ ከድምፁ የተነሣ ከንፈሮቼ ተንቀጠቀጡ፥ መንቀጥቀጥ ወደ አጥንቶቼ ውስጥ ገባ፥ በስፍራዬ ሆኜ ተናወጥሁ፥ በሚያስጨንቁን ሕዝብ ላይ እስኪመጣ ድረስ የመከራን ቀን ዝም ብዬ እጠብቃለሁ። ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፥ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ሥራ ቢጐድል፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፥ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፥ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፥ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ። ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌ ነው፥ እግሮቼን እንደ ዋላ እግሮች ያደርጋል፥ በከፍታዎችም ላይ ያስሄደኛል።

ዕንባቆም 3:11-19 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))

በቀስቶችህ ብርሃን፥ በጦርህ መብረቅ ፀዳል፥ ፀሐይና ጨረቃ በመኖሪያቸው ቀጥ ብለው ቆሙ። በቁጣ ምድርን ረገጥሃት፥ አሕዛብን በንዴት አሄድሃቸው። ሕዝብህን ለመታደግ፥ የቀባኸውንም ለማዳን ወጣህ፤ የኃጢአተኛውን ቤት ራስ ቀጠቀጥህ፥ ከመሠረቱ እስከ አንገቱ ድረስ አራቆትህ። ደስታቸው የተደበቁ ችግረኞችን እንደሚውጥ የሆነውን፥ እኛን ሊበትኑ እንደ ዐውሎ ነፋስ የመጡትን፤ የጦረኛውን ራስ በገዛ ጦሩ ወጋህ፤ በፈረሶችህ በባሕር ላይ ተራመድህ፥ ብዙ ውኆችንም ረገጥህ። እኔ ሰምቻለሁ፥ አንጀቴ ራደብኝ፥ ከድምፁ የተነሣ ከንፈሮቼ ተንቀጠቀጡ፤ መበስበስ ወደ አጥንቶቼ ውስጥ ገባ፥ በውስጤም ተንቀጠቀጥሁ፥ በአስጨነቁን ሕዝብ ላይ እስኪመጣ ድረስ፥ የመከራን ቀን ዝም ብዬ እጠብቃለሁ። የበለስ ዛፍ ባታብብም፥ በወይን ተክሎች ላይ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ምርት ቢቋረጥ፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፥ ከብቶችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፥ እኔ ግን በጌታ ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ። ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌ ነው፤ እግሮቼን እንደ ዋላ እግሮች ያደርጋል፤ በከፍታዎቼም ላይ ያስሄደኛል። ለመዘምራን አለቃ፥ በባለ አውታር መሣሪያዎቼ።