ዘፍጥረት 9:12-17
ዘፍጥረት 9:12-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔር አምላክም ለኖኅ አለው፥ “በእኔና በእናንተ መካከል፥ ከእናንተም ጋር ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል፥ ለዘለዓለም ትውልድ የማደርገው የቃል ኪዳኔ ምልክት ይህ ነው፤ ቀስቴን በደመና አኖራለሁ፤ የቃል ኪዳኔም ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይሆናል። በምድር ላይ ደመናን በጋረድሁ ጊዜ ቀስቴ በደመናው ትታያለች፤ በእኔና በእናንተ መካከል፥ ሕያው ነፍስ ባለውም ሥጋ ሁሉ መካከል ያለውን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ሥጋ ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ ዳግመኛ የጥፋት ውኃን አላመጣም። ቀስቴም በደመና ትሆናለች፤ በእኔና በምድር መካከል፥ በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል ያለውን የዘለዓለም ቃል ኪዳን ለማሰብ አያታለሁ።” እግዚአብሔርም ኖኅን፥ “በእኔና በምድር ላይ በሚኖር፥ ሥጋ ባለው ሁሉ መካከል ያጸናሁት የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው” አለው።
ዘፍጥረት 9:12-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “በእኔና በእናንተ መካከል፣ ከእናንተም ጋራ ካሉ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ጋራ ከሚመጣውም ትውልድ ሁሉ ጋራ፣ የማደርገው የኪዳኑ ምልክት ይህ ነው፤ ቀስተ ደመናዬን በደመና ላይ አደርጋለሁ፤ ይህም በእኔና በምድር መካከል ለገባሁት ኪዳን ምልክት ይሆናል። ደመናን በምድር ላይ በጋረድሁና ቀስቴም በደመና ላይ በሚታይበት ጊዜ ሁሉ፣ ከእናንተና ከሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ጋራ የገባሁትን ኪዳን ዐስባለሁ፤ ሕይወት ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ፣ ከእንግዲህ የጥፋት ውሃ ከቶ አይመጣም። ቀስቱ በደመና ላይ ተገልጦ በማይበት ጊዜ ሁሉ፣ በእግዚአብሔርና በምድር ላይ ባሉ ሕያዋን ፍጥረታት መካከል ያለውን ዘላለማዊ ኪዳን ዐስባለሁ።” ስለዚህ እግዚአብሔር ኖኅን፣ “ይህ በእኔና በምድር ላይ በሚኖሩ ሕያዋን ሁሉ መካከል የገባሁት ኪዳን ምልክት ነው” አለው።
ዘፍጥረት 9:12-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም አለ፤ በእኔና በእናንተ መካከላ፤ ከእናንትም ጋር ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል፥ ለዘላለም የማደርገው የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው። ቀስቴን በደመና አድርጌአለሁ፥ የቃል ኪዳኑም ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይሆናል። በምድር ላይ ደመናን በጋረድሁ ጊዜ ቀስቲቱ በደመናው ትታያለች፤ በእኔና በእናንተ መካከል፥ ሕያው ነፍስ ባለውም ሥጋ ሁሉ መካከል ያለውን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ሥጋ ያለውንም ሁሉ ያጠፉ ዘንድ ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም። ቀስቲቱም በደመነ ትሆናለች በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባከው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል ያለውን የዘላለም ቃል ኪዳን ለማሰብ አያታለሁ። እግዚአብሔርም ኖኅን፥ በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥግ ባለው ሁሉ መካከል ያቆምሁት የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው አለው።
ዘፍጥረት 9:12-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፦ “ከእናንተና ከሕያዋን ፍጥረቶች ሁሉ ጋር ለምገባው ለዚህ ለዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን ምልክት ይሆን ዘንድ፥ ቀስቴን በደመናዎች ላይ አደርጋለሁ፤ ይህም ቀስት ከምድር ጋር ለገባሁት ቃል ኪዳን ምልክት ሆኖ ይኖራል። ሰማይን በደመና በምሸፍንበትና ቀስትም በደመና ላይ በሚታይበት ጊዜ ሁሉ፥ ‘ከእንግዲህ ወዲህ የጥፋት ውሃ፤ ሕያዋን ፍጥረቶችን ሁሉ ከቶ አያጠፋም’ ብዬ ከእናንተና ከሌሎች ሕያዋን ፍጥረቶች ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አስታውሳለሁ። ቀስት በደመናዎች ላይ በሚታይበት ጊዜ ተመልክቼ በእኔና በምድር ላይ ባሉት ሕይወት ባላቸው ፍጥረቶች መካከል ያለውን ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን አስታውሳለሁ።” እግዚአብሔርም ኖኅን እንዲህ አለው፦ “ይህ ቀስት በምድር ላይ በእኔና ሕይወት ባላቸው ፍጥረቶች ሁሉ መካከል የገባሁትን ቃል ኪዳን የሚያስታውስ ምልክት ነው።”
ዘፍጥረት 9:12-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንዲህም ሲል እግዚአብሔር ተናገረ፦ “በእኔና በእናንተ፥ ከእናንተም ጋር ባለው በሕያው ፍጥረት ሁሉ መካከል፥ ለዘለዓለም የማደርገው፥ የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው፥ ቀስቴን በደመና አደርጋለሁ፥ ይህም በእኔና በምድር መካከል የቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል። ምድር በደመና በምትሸፈንበት ቀስቲቱም በደመናው በምትታይበት ጊዜ፥ በእኔና በእናንተ፥ ሕያው ነፍስ ባለውም ፍጥረት መካከል ያለውን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ውኃም ዳግመኛ ፍጥረትን ሁሉ ያጠፋ ዘንድ የውኃ ሙላት አይመጣም። ቀስቲቱም በደመና ስትሆን፥ አያታለሁም በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው በሕያው ፍጥረት ሁሉ መካከል ያለውን ዘላለማዊ ቃል ኪዳን አስታውሳለሁ።” እግዚአብሔርም ኖኅን፦ “ይህ በእኔና በምድር ላይ በሚኖሩ ሕይወት ባላቸው ፍጥረቶች መካከል ያቆምሁት የቃል ኪዳን ምልክት ነው” አለው።