ዘፍጥረት 6:5-9
ዘፍጥረት 6:5-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም የሰዎች ክፉ ሥራ በምድር ላይ እንደበዛ፥ የልባቸው ዐሳብ ምኞትም ሁል ጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደሆነ አየ። እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ በልቡም አዘነ። እግዚአብሔርም፥ “የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፤ ከሰው እስከ እንስሳና አራዊት፥ እስከ ተንቀሳቃሽም፥ እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ፤ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቻለሁና” አለ። ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ። የኖኅ ትውልድ እንዲህ ነው። ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ፥ ፍጹምም ሰው ነበረ፤ ኖኅም እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው።
ዘፍጥረት 6:5-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር አምላክ የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑን ተመለከተ። እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ ልቡም እጅግ ዐዘነ። ስለዚህም እግዚአብሔር፣ “የፈጠርሁትን የሰው ዘር ከምድረ ገጽ አጠፋለሁ፤ ከሰው እስከ እንስሳ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረታት እስከ ሰማይ ወፎች አጠፋለሁ፤ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቻለሁና” አለ። ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን አገኘ። የኖኅ ታሪክ እንደሚከተለው ነው።
ዘፍጥረት 6:5-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም የሰው ክፉት በምድር ላይ እንደ በዛ፤ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንድ ሆነ አየ። እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ በልቡም አዘነ። እግዚአብሔርም፤ የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፤ ከሰው እስከ እንስሳ እስከ ተንቀሳቃሽም እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ ስለ ፈጠርኍቸው ተጸጽቼእለሁና አለ። ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ። የኖኅ ትውልድ እንዲህ ነው። ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ስው ነበረ ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረግ።
ዘፍጥረት 6:5-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር በምድር ላይ ያሉ ሰዎች ሁሉ ምን ያኽል ዐመፀኞች እንደ ሆኑና ሐሳባቸውም ዘወትር ክፋት ብቻ እንደ ሆነ ተመለከተ፤ ስለዚህ ሰዎችን በመፍጠሩና በምድር ላይ እንዲኖሩ በማድረጉ አዘነ፤ እጅግም ተጸጸተ። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር “እነርሱን በመፍጠሬ አዝኛለሁ፤ ስለዚህ እነዚህን የፈጠርኳቸውን ሰዎች፥ እንስሶችን፥ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችንና ወፎችንም ጭምር ከምድር ላይ አጠፋለሁ” አለ። ይሁን እንጂ ኖኅ የተባለው ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን አግኝቶ ነበር። የኖኅ ታሪክ እንደሚከተለው ነው፤ ኖኅ በዘመኑ ምንም በደል የማይሠራና የእግዚአብሔርን መንገድ የሚከተል ደግ ሰው ነበር፤
ዘፍጥረት 6:5-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም የሰው ክፋት በምድር ላይ እንደ በዛ፥ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደሆነ አየ። ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩም ጌታ ተጸጸተ፥ በልቡም አዘነ። በዚህ ምክንያት ጌታ፥ “ከምድር ላይ የፈጠርኩትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፥ ሰው እና አራዊትን፥ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችን እና የሰማይ አእዋፍንም፥ ስለ ፈጠርኳቸው ተጸጽቼአለሁና” አለ። ይሁን እንጂ ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ። የኖኅ ትውልድ እንደሚከተለው ነው። ኖኅም ጻድቅ፥ በትውልዱም በደል ያልተገኘበት ሰው ነበረ፥ ኖኅም እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው።