ዘፍጥረት 50:15-26
ዘፍጥረት 50:15-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የዮሴፍም ወንድሞች አባታቸው እንደ ሞተ በአዩ ጊዜ እንዲህ አሉ፥ “ምናልባት ዮሴፍ ያደረግንበትን ክፋት ያስብብን ይሆናል፤ ባደረግንበትም ክፋት ሁሉ ብድራት ይመልስብን ይሆናል።” ወደ ዮሴፍም መጡ፤ እንዲህም አሉት፥ “አባትህ ገና ሳይሞት እንዲህ ብሎ አዝዟል፦ ‘ዮሴፍን እንዲህ በሉት፦ እባክህ የወንድሞችህን በደል ኀጢአታቸውንም ይቅር በል፤ እነርሱ በአንተ ክፉ አድርገውብሃልና፤’ አሁንም እባክህ የአባትህ አምላክ ባሪያዎች የበደሉህን ይቅር በል።” ዮሴፍም ይህን ሲሉት አለቀሰ። ወንድሞቹ ደግሞ መጡ፤ “እነሆ፥ እኛ ለአንተ አገልጋዮችህ ነን” አሉት። ዮሴፍም አላቸው፥ “አትፍሩ፤ ይህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆኖአልና። እናንተ በእኔ ላይ ክፉ መከራችሁ፤ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደ ሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲመገብ ለማድረግ ለእኔ መልካም መከረ። አሁንም አትፍሩ፤ እኔ እናንተንና ቤተ ሰቦቻችሁን እመግባችኋለሁ።” አጽናናቸውም፤ በልባቸው የሚገባ ነገርም ነገራቸው። ዮሴፍም በግብፅ ሀገር ተቀመጠ፤ እርሱና ወንድሞቹ የአባቱም ቤተ ሰብ፤ ዮሴፍም መቶ ዐሥር ዓመት ኖረ። ዮሴፍም የኤፍሬምን ልጆች እስከ ሦስት ትውልድ አየ። የምናሴ ልጅ የማኪር ልጆችም በዮሴፍ ጭን ላይ ተወለዱ። ዮሴፍም ወንድሞቹን አላቸው፥ “እኔ እሞታለሁ፤ እግዚአብሔርም መጐብኘትን ይጐበኛችኋል፤ ከዚህችም ምድር ያወጣችኋል። ለአባቶቻችን ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ያገባችኋል።” ዮሴፍም የእስራኤልን ልጆች፥ “እግዚአብሔር በጐበኛችሁ ጊዜ አጥንቴን ከዚህ አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር አውጡ” ብሎ አማላቸው። ዮሴፍም በመቶ ዐሥር ዓመት ዕድሜው ሞተ፤ በሽቱም አሹት፤ በግብፅ ምድርም በሣጥን ውስጥ አኖሩት።
ዘፍጥረት 50:15-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የዮሴፍ ወንድሞች ከአባታቸው ሞት በኋላ፣ “ከፈጸምንበት በደል የተነሣ ዮሴፍ ቂም ይዞ ቢበቀለን ምን እናደርጋለን?” ተባባሉ። ስለዚህ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ዮሴፍ ላኩ፤ “አባትህ ከመሞቱ በፊት እንዲህ የሚል ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር፤ ‘ለዮሴፍ፣ “ወንድሞችህ በአንተ ላይ የፈጸሙትን ኀጢአትና ክፉ በደል ይቅር በላቸው” ብላችሁ ንገሩት።’ አሁንም የእኛን የአባትህን አምላክ አገልጋዮች ኀጢአት ይቅር በለን።” መልእክታቸው ሲደርሰው ዮሴፍ አለቀሰ። ከዚያም ወንድሞቹ መጡና በፊቱ ተደፍተው፣ “እኛ የአንተ ባሮች ነን” አሉት። ዮሴፍ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትፍሩ፤ እኔን በእግዚአብሔር ቦታ ማን አስቀመጠኝ? እናንተ እኔን ለመጕዳት ዐስባችሁ አድርጋችሁት ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደሚታየው ሁሉ የብዙዎችን ሕይወት ለማዳን ለበጎ ነገር አዋለው። አሁንም ቢሆን አትፍሩ፤ ለእናንተና ለልጆቻችሁ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አደርግላችኋለሁ” በማለት አረጋግጦ፣ በደግ ቃል አናገራቸው። ዮሴፍ ከአባቱ ቤተ ሰቦች ጋራ በግብጽ ተቀመጠ፤ አንድ መቶ ዐሥር ዓመትም ኖረ፤ የኤፍሬምንም የልጅ ልጆች እስከ ሦስት ትውልድ ድረስ አየ። የምናሴ ልጅ ማኪር የወለዳቸውም ልጆች በዮሴፍ ጭን ላይ ተወለዱ። ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ወንድሞቹን፣ “እነሆ፤ የመሞቻዬ ጊዜ ተቃርቧል፤ እግዚአብሔርም በረድኤቱ ይጐበኛችሁና ከዚህ አገር ያወጣችኋል፤ ለአባቶቻችን ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለያዕቆብ በመሐላ ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ያገባችኋል” አላቸው። ዮሴፍም የእስራኤልን ልጆች፣ “እግዚአብሔር በረድኤቱ ያስባችኋል፤ በዚያ ጊዜ ዐፅሜን ከዚህ አገር ይዛችሁ እንድትወጡ” ሲል አስማላቸው። ዮሴፍም በመቶ ዐሥር ዓመቱ ሞተ፤ ሬሳው እንዳይፈርስ በአገሩ ደንብ በመድኀኒት ከደረቀ በኋላ፣ ሣጥን ውስጥ አስገብተው በግብጽ ምድር አስቀመጡት።
ዘፍጥረት 50:15-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የዮሴፍም ወንድሞች አባታቸው እንደ ሞተ ባዪ ጊዜ እንዲህ አሉ፦ ምናልባትም ዮሴፍ ይጠላን ይሆናል ባደረግንበትን ክፋት ሁሉ ብድራት ይመልስብን ይሆናል። ወደ ዮሴፍም መልእክት ላኩ እንዲህም አሉት፦ አባትህ ገና ሳይሞት እንዲህ ብሎ አዝዞአል፦ ዮሴፍን እንዲህ በሉት፦ እባክህ የውንድሞችህን በደል ኃጢአታቸውንም ይቅር በል እነርሱ በአንተ ከፍተውብሃልና አሁን እባክህ የአባትህ አምላክ ባሪያዎች የበደሉን ይቅር በል። ዮሴፍም ይህን ሲሉት አለቀሰ። ወንድሞቹ ደግሞ መጡ በፊቱም ሰግደው፦ እነሆ እኛ ለአንተ ባሪያዎችህ ነን አሉት። ዮሴፍም አላቸው፦ አትፍሩ እኔ በእግዚአብሔር ፋንታ ነኝን? እናንተ ክፋ ነገርን አሰባችሁብኝ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደ ሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው። አሁንም አትፍሩ እኔ እናንተና ልጆቻችሁን እመግባችኍለሁ አጽናናቸውም ደስ አሰኛቸውም። ዮሴፍም በግብፅ ተቀመጠ እርሱና የአባቱም ቤተ ስብ ዮሴፍም መቶ አሥር ዓመት ኖረ። ዮሴፍም የኤፍሬምን ልጆች እስከ ሦስት ትውልድ አየ የምናሴ ልጅ የማኪር ልጆችም በዮሴፍ ጭን ላይ ተወለዱ። ዮሴፍም ወንድሞቹን አለ፦ እኔ እሞታለሁ እግዚአብሔር መጎብኘትን ይጎበኛችኍል ከዚህችም ምድር ያወጣችኍል ለአብርሃምን ለይስሕቅ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ያደርሳችኍል። ዮሴፍም የእስራኤልን ልጆች፦ እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚን አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ ብሎ አማላቸው። ዮሴፍም በመቶ አሥር ዓመት ዕድሜው ሞተ በሽቱ፥ አሹት በግብፅ ምድር በሣጥን ውስጥ አኖሩት።
ዘፍጥረት 50:15-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የዮሴፍ ወንድሞች አባታቸው ከሞተ በኋላ “ዮሴፍ ባደረስንበት በደል ሁሉ እስከ አሁንም ቂም ይዞ ሊበቀለን ቢፈልግ ምን እናደርጋለን?” ተባባሉ። ስለዚህ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ዮሴፍ ላኩ፤ “አባትህ ከመሞቱ በፊት፥ ‘ወንድሞችህ በበደሉህ ጊዜ ያደረሱብህን ጒዳት ሁሉ አትቊጠርባቸው ብሎሃል’ ብለን እንድንነግርህ አዞናል፤ ስለዚህ እኛ የአባትህ አምላክ አገልጋዮች ያደረስንብህን በደል ሁሉ ይቅር እንድትለን እንለምንሃለን።” ዮሴፍ ይህን በሰማ ጊዜ አለቀሰ። ከዚህ በኋላ ወንድሞቹ ራሳቸው በፊቱ ቀርበው ጐንበስ ብለው እጅ ነሡና “እነሆ እኛ ሁላችን አገልጋዮችህ ነን” አሉት። ነገር ግን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፤ “አይዞአችሁ አትፍሩ፤ እኔ በእግዚአብሔር ምትክ የምሆን አይደለሁም፤ በእርግጥ እናንተ ክፉ ነገር መክራችሁብኝ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ወደ መልካም ነገር ለወጠው፤ ይህንንም ያደረገው አሁን በሕይወት ያሉትን የብዙ ሰዎችን ሕይወት ለማትረፍ ብሎ ነው። ምንም የሚያስፈራችሁ ነገር የለም፤ እኔ እናንተንና ልጆቻችሁን እመግባችኋለሁ።” በዚህም ዐይነት በመልካም ንግግር በማጽናናት አረጋጋቸው። ዮሴፍ ከአባቱ ቤተሰቦች ጋር በግብጽ ተቀመጠ፤ ከዚያም ዕድሜው መቶ ዐሥር ዓመት እስኪሆነው ኖረ፤ የኤፍሬምንም ልጆችና የልጅ ልጆች እስከሚያይ ድረስ ቈየ፤ ከምናሴ የተወለደውንም የማኪርንም ልጆች እንደ ልጆቹ አድርጎ ተቀበላቸው። ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ እኔ የምሞትበት ጊዜ ተቃርቦአል፤ እናንተን ግን እግዚአብሔር በረድኤት ይጐበኛችኋል፤ ከዚህም አገር አውጥቶ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ለመስጠት በመሐላ ቃል ወደ ገባላቸው ምድር ይመልሳችኋል። እግዚአብሔር በሚጐበኛችሁና ወደዚያች ምድር በሚመልሳችሁ ጊዜ ዐፅሜን ከዚህ ይዛችሁ የምትወጡ መሆናችሁን በማረጋገጥ ቃል ግቡልኝ” ብሎ አስማላቸው። ዮሴፍም ዕድሜው መቶ ዐሥር ዓመት ሲሞላው ሞተ፤ አስከሬኑንም በሽቶ አሽተው በማድረቅ በግብጽ ምድር በሣጥን ውስጥ አኖሩት።
ዘፍጥረት 50:15-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የዮሴፍም ወንድሞች አባታቸው እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ እንዲህ አሉ፦ “ምናልባት ዮሴፍ ይጠላን ይሆናል፥ ባደረግንበትም ክፋት ሁሉ ብድራት ይመልስብን ይሆናል።” ወደ ዮሴፍም መልእክት ላኩ እንዲህም አሉት፦ “አባትህ ገና ሳይሞት እንዲህ ብሎ አዝዞአል፦ ዮሴፍን እንዲህ በሉት፦ ‘እባክህ የወንድሞችህን በደል ኃጢአታቸውንም ይቅር በል፥ እነርሱ በአንተ ከፍተውብሃልና፥ አሁንም እባክህ የአባትህ አምላክ ባርያዎች የበደሉህን ይቅር በል።’” ዮሴፍም ይህን ሲሉት አለቀሰ። ወንድሞቹ ደግሞ መጡ በፊቱም ሰግደው፦ “እነሆ እኛ ለአንተ ባርያዎችህ ነን አሉት።” ዮሴፍም አላቸው፦ “አይዞአችሁ አትፍሩ፤ እኔ በእግዚአብሔር ምትክ የምሆን ነኝ? እናንተ ክፋ ነገርን አሰባችሁብኝ፥ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደ ሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው። አሁንም አትፍሩ፥ እኔ እናንተንና ልጆቻችሁን እመግባችኋለሁ።” አጽናናቸውም ደስ አሰኛቸውም። ዮሴፍ ከአባቱ ቤተሰቦች ጋር በግብጽ ተቀመጠ፤ ዮሴፍም መቶ ዐሥር ዓመት ኖረ። የኤፍሬምንም ልጆችና የልጅ ልጆች እስከሚያይ ድረስ ቈየ፤ ከምናሴ የተወለደውንም የማኪርንም ልጆች እንደ ልጆቹ አድርጎ ተቀበላቸው። ዮሴፍም ወንድሞቹን፦ “እኔ እሞታለሁ፥ እግዚአብሔርም መጎብኘትን ይጎበኛችኋል፥ ከዚህችም ምድር ያወጣችኋል፥ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ያደርሳችኋል” አላቸው። ዮሴፍም የእስራኤልን ልጆች፦ “እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚህ አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ ብሎ” አስማላቸው። ዮሴፍም ዕድሜው መቶ ዐሥር ዓመት ሲሞላው ሞተ፤ በሽቶም አሹት፥ በግብጽ ምድር በሣጥን ውስጥ አኖሩት።