ዘፍጥረት 45:1-28
ዘፍጥረት 45:1-28 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዮሴፍም በፊቱ ሰዎች ሁሉ ቆመው ሳሉ ሊታገሥ አልተቻለውም፥ “ሰዎቹንም ሁሉ ከፊቴ አስወጡልኝ” ብሎ ተናገረ፤ ዮሴፍ ለወንድሞቹ ራሱን በገለጠ ጊዜ በእርሱ ዘንድ የቆመ ማንም አልነበረም። ቃሉንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ፤ የግብፅ ሰዎችም ሰሙ፤ በፈርዖን ቤትም ተሰማ። ዮሴፍም ለወንድሞቹ፥ “እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ፤ አባቴ እስከ አሁን በሕይወቱ ነውን?” አላቸው። ወንድሞቹም ይመልሱለት ዘንድ አልቻሉም፤ ደንግጠው ነበርና። ዮሴፍም ወንድሞቹን፥ “ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው። ወደ እርሱም ቀረቡ። እንዲህም አላቸው፥ “ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። አሁንም ወደዚህ ስለሸጣችሁኝ አትፍሩ፤ አትቈርቈሩም፤ እግዚአብሔር ለሕይወት ከእናንተ በፊት ልኮኛልና። እነሆ፥ ይህ ሁለቱ ዓመት በምድር ላይ ራብ የሆነበት ነውና፤ የማይታረስበትና የማይታጨድበት አምስት ዓመት ገና አለ። እግዚአብሔርም በምድር ላይ እንድትድኑና እንድትተርፉ እመግባችሁ ዘንድ ከእናንተ በፊት ላከኝ። አሁንም እናንተ ወደዚህ የላካችሁኝ አይደላችሁም፤ እግዚአብሔር ላከኝ እንጂ፤ ለፈርዖንም እንደ አባት አደረገኝ፤ በቤቱም ሁሉ ላይ ጌታ፥ በግብፅ ምድርም ሁሉ ላይ አለቃ አደረገኝ። አሁንም ፈጥናችሁ ወደ አባቴ ሂዱ፤ እንዲህም በሉት፦ ልጅህ ዮሴፍ የሚለው ነገር ይህ ነው፦ እግዚአብሔር በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ጌታ አደረገኝ፤ ወደ እኔ ና፤ በዚያም አትዘግይ፤ በዐረብ በኩል በጌሤም ምድርም ትቀመጣለህ፤ ወደ እኔም ትቀርባለህ። አንተና ልጆችህ የልጆችህም ልጆች፥ በጎችህና ላሞችህ፥ የአንተ የሆነው ሁሉ፥ በዚያም አንተና የቤትህ ሰዎች የአንተ የሆነው ሁሉ እንዳትቸገሩ እመግብሃለሁ፤ የራቡ ዘመን ገና አምስት ዓመት ቀርቶአልና፤ እነሆም፥ ለእናንተ እኔ ራሴ በአፌ እንደ ተናገርሁአችሁ እናንተ በዐይኖቻችሁ አይታችኋል፤ ወንድሜ ብንያም በዐዓይኖቹ አይቶአል። ለአባቴ በግብፅ ምድር ያለኝን ክብሬን ሁሉ፥ በዐይኖቻችሁ ያያችሁትንም ሁሉ ንገሩት፤ አባቴንም ወደዚህ ፈጥናችሁ አምጡት።” የወንድሙን የብንያምንም አንገት አቅፎ አለቀሰ፤ ብንያምም በአንገቱ ላይ አለቀሰ። ወንድሞቹን ሁሉ ሳማቸው፤ በእነርሱም ላይ አለቀሰ፤ ከዚያም በኋላ ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር ተጨዋወቱ። በፈርዖንም ቤት፥ “የዮሴፍ ወንድሞች መጡ” ተብሎ ወሬ ተሰማ፤ ፈርዖንና ቤተ ሰቡም ሁሉ ደስ አላቸው። ፈርዖንም ዮሴፍን አለው፥ “ለወንድሞችህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ይህን አድርጉ፤ ዕቃችሁን ጭናችሁ ወደ ከነዓን ምድር ሂዱ፤ አባታችሁንና ንብረታችሁን ሁሉ ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም የግብፅን ምድር በረከት ሁሉ እሰጣችሁአለሁ፤ የምድሪቱንም ድልብ ትበላላችሁ። አንተም ወንድሞችህን፦ እንዲህ አድርጉ በላቸው፤ ከግብፅ ምድር ለሕፃኖቻችሁ፥ ለሴቶቻችሁም ሰረገሎችን ውሰዱ፤ አባታችሁንም ይዛችሁ ኑ፤ ለዕቃችሁም ዐይናችሁ ለአየውም ሁሉ አታስቡ፤ የግብፅ በረከት ሁሉ ለእናንተ ነውና።” የእስራኤል ልጆችም እንደ አዘዛቸው አደረጉ፤ ዮሴፍም የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን እንደ ነገረው ሰረገሎችንና ለመንገድ ስንቅን ሰጣቸው፤ ለሁሉም ሁለት ሁለት መለወጫ ልብስ ሰጣቸው፤ ለብንያም ግን ሦስት መቶ ብርና አምስት መለወጫ ልብስ ሰጠው። ለአባቱም እንደዚሁ ላከ፤ ከግብፅ በረከት ሁሉ የተጫኑ ዐሥር አህዮችን፥ ደግሞም በመንገድ ለአባቱ ስንቅ የተጫኑ ዐሥር በቅሎዎችን። ዮሴፍም ወንድሞቹን አሰናበታቸው፤ እንዲህም አላቸው፥ “በመንገድ እርስ በርሳችሁ አትጣሉ።” እነርሱም ከግብፅ ሀገር ወጥተው ሄዱ፤ ወደ ከነዓንም ምድር ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ ደረሱ። እንዲህም ብለው ነገሩት፥ “ልጅህ ዮሴፍ በሕይወቱ ነው፤ እርሱም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ገዥ ሆኖአል።” ያዕቆብም ልቡ ደነገጠ፤ አላመናቸውምም፤ እነርሱም ዮሴፍ ያላቸውን፥ የተናገራቸውንም ነገር ሁሉ ነገሩት፤ ይወስዱት ዘንድ ዮሴፍ የላካቸውን ሰረገሎች በአየ ጊዜ የአባታቸው የያዕቆብ ልቡ፥ መንፈሱም ታደሰ። እስራኤልም፥ “ልጄ ዮሴፍ ገና በሕይወት ከሆነ ይህ ለእኔ ታላቅ ነገር ነው፤ ሳልሞት እንዳየው እሄዳለሁ” አለ።
ዘፍጥረት 45:1-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚያ ጊዜ ዮሴፍ አጠገቡ በነበሩ ሰዎች ፊት ስሜቱን ሊገታ ባለመቻሉ፣ “እዚህ ያሉትን ሰዎች በሙሉ አስወጡልኝ” ብሎ ጮኾ ተናገረ፤ ስለዚህም ዮሴፍ ራሱን ለወንድሞቹ በገለጠበት ጊዜ፣ ከርሱ ጋራ ሌላ ማንም ሰው አልነበረም። ዮሴፍም ድምፁን ከፍ አድርጎ በማልቀሱ፣ ግብጻውያን ሰሙት፤ ወሬውም ወደ ፈርዖን ቤተ ሰዎች ደረሰ። ዮሴፍም ወንድሞቹን፣ “እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ ለመሆኑ አባቴ እስካሁን በሕይወት አለ?” ሲል ጠየቃቸው። ወንድሞቹ ግን በፊቱ ተደናግጠው ስለ ነበር መልስ ሊሰጡት አልቻሉም። ዮሴፍም ወንድሞቹን፣ “እስኪ ወደ እኔ ቀረብ በሉ” አላቸው፤ ወደ እርሱም በቀረቡ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “ወደ ግብጽ የሸጣችሁኝ ወንድማችሁ እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ አሁንም በመሸጣችሁ አትቈጩ፤ በራሳችሁም አትዘኑ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሕይወት ለማዳን ሲል ከእናንተ አስቀድሞ እኔን ወደዚህ ልኮኛል። በምድር ላይ ራብ ከገባ ይኸው ሁለት ዓመት ሆነ፤ ከዚህ በኋላም የማይታረስባቸውና ሰብል የማይሰበሰብባቸው ዐምስት ዓመታት ገና አሉ። ነገር ግን እግዚአብሔር ሕይወታችሁን በታላቅ ማዳን ለመታደግና ዘራችሁ ከምድር ላይ እንዳይጠፋ በማሰብ ከእናንተ አስቀድሞ ወደዚህ ላከኝ። “ስለዚህ አሁን ወደዚህ የላከኝ እግዚአብሔር እንጂ እናንተ አይደላችሁም፤ እርሱም ለፈርዖን እንደ አባት፣ በቤት ንብረቱ ላይ ጌታ፣ እንዲሁም በግብጽ ምድር ላይ ገዥ አደረገኝ። አሁንም በፍጥነት ወደ አባቴ ተመልሳችሁ እንዲህ በሉት፤ ልጅህ ዮሴፍ እንዲህ ይላል፤ ‘እግዚአብሔር የመላው ግብጽ ጌታ አድርጎኛል፤ ስለዚህ ሳትዘገይ ወደ እኔ ና። ልጆችህን፣ የልጅ ልጆችህን፣ በጎችህን፣ ፍየሎችህን፣ ከብቶችህንና ያለህን ሁሉ ይዘህ በአቅራቢያዬ በጌሤም ትኖራለህ። ገና ወደ ፊት የሚመጣ የዐምስት ዓመት ራብ ስላለ፣ በዚያ የሚያስፈልጋችሁን እኔ እሰጣችኋለሁ፤ አለዚያ ግን አንተና ቤተ ሰዎችህ ያንተም የሆነው ሁሉ፣ ችግር ላይ ትወድቃላችሁ።’ “ፊታችሁ ሆኜ የማናግራችሁ እኔ ዮሴፍ ራሴ መሆኔን እናንተም ሆናችሁ ወንድሜ ብንያም በዐይናችሁ የምታዩት ነው። በግብጽ ስላለኝ ክብርና ስላያችሁትም ሁሉ ለአባቴ ንገሩት፤ አባቴንም በፍጥነት ይዛችሁት ኑ።” ከዚያም በወንድሙ በብንያም ዐንገት ላይ ተጠምጥሞ አለቀሰ፤ ብንያምም እያለቀሰ ዮሴፍን ዐቀፈው። የቀሩትንም ወንድሞቹን አንድ በአንድ እየሳመ አለቀሰ። ከዚያም ወንድሞቹ ከርሱ ጋራ መጨዋወት ጀመሩ። የዮሴፍ ወንድሞች መምጣት በፈርዖን ቤተ መንግሥት በተሰማ ጊዜ፣ ፈርዖንና ሹማምቱ ሁሉ ደስ አላቸው። ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ለወንድሞችህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እንዲህ አድርጉ፤ አህዮቻችሁን ጭናችሁ ወደ ከነዓን ምድር ተመለሱ። ከዚያም አባታችሁንና ቤተ ሰባችሁን ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እጅግ ለም ከሆነው የግብጽ ምድር እሰጣችኋለሁ፤ በምድሪቱ በረከት ደስ ብሏችሁ ትኖራላችሁ።’ “ደግሞም እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፤ ‘ይህን አድርጉ፤ ከግብጽ ምድር ልጆቻችሁንና ሚስቶቻችሁን የምታጓጕዙበት ሠረገላዎች ወስዳችሁ፣ አባታችሁን ይዛችሁት ኑ። ስለ ንብረታችሁ ምንም አታስቡ፤ ከግብጽ ምድር እጅግ ለም የሆነው የእናንተ ይሆናልና።’ ” የእስራኤልም ልጆች ይህንኑ አደረጉ። ዮሴፍም ፈርዖን ባዘዘው መሠረት ሠረገላዎች አቀረበላቸው፤ የመንገድም ስንቅ አስያዛቸው። ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት የክት ልብስ ሰጣቸው፤ ለብንያም ግን ሦስት መቶ ጥሬ ብርና ዐምስት የክት ልብስ ሰጠው። ለአባቱም በግብጽ ምድር ከሚገኘው የተመረጠ ነገር በዐሥር አህዮች፣ እንደዚሁም ለመንገዱ ስንቅ የሚሆነው እህል፣ ዳቦና ሌላ ምግብ በዐሥር እንስት አህዮች አስጭኖ ሰደደለት። ከዚህ በኋላ ወንድሞቹን አሰናበታቸው፤ ከርሱም ሲሰናበቱ፣ “መንገድ ላይ እንዳትጣሉ!” አላቸው። እነርሱም ከግብጽ ወጥተው በከነዓን ምድር ወደሚኖረው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ መጡ። አባታቸውንም፣ “እነሆ ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ እንዲያውም በግብጽ ምድር ሁሉ ገዥ ሆኗል” ብለው ነገሩት። ያዕቆብም በድንጋጤ ክው አለ፤ ሊያምናቸውም አልቻለም። ነገር ግን ዮሴፍ የነገራቸውን ሁሉ ሲያጫውቱትና እርሱንም ወደ ግብጽ ለማጓጓዝ ዮሴፍ የላከለትን ሠረገላዎች ሲያይ የአባታቸው የያዕቆብ መንፈስ ታደሰ። ከዚያም እስራኤል፤ “ልጄ ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ ከመሞቴ በፊት ሄጄ ልየው” አለ።
ዘፍጥረት 45:1-28 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዮሴፍም በእርሱ ዘንድ ቆመው ባሉት ሰዎች ሁሉ ፊት ሊታገሥ አልተቻለውም፦ ሰዎቹንም ሁሉ ከፊቴ አስወጡልኝ ብሎ ጮኽ ተናገረ ዮሴፍ ለወንድሞቹ ራሱን በገለጠ ጊዜ በእርሱ ዘንድ የቆመ ማንም አልነበረም። ቃሉንም ከፍ አድርጎ አልቀሰ የግብፅ ሰዎችም ሰሙ በፈርዖን ቤትም ተሰማ። ዮሴፍም ለወንድሞቹ፦ እኔ ዮሴፍ ነኝ አባቴ እስከ አሁን በሕይወቱ ነውን? አለ። ወንድሞቹም ይመጠው ነበርና። ዮሴፍም ወንድሞቹን፦ ወደ እኔ ቅረቡ አለ። ወደ እርሱም ቀረቡ እንዲህም አላቸው፦ ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። አሁንም ወደዚህ ስለ ሸጣችሁኝ አትዘኑ አትቆርቆሩም እግዚአብሔር ሕይወትን ለማዳን ከእናንተ በፊት ሰድዶኛልና። ይህ ሁለቱ ዓመት በምድር ላይ ራብ የሆነበት ነውና የማይታረስበትና የማይታጨድበት አምስት ዓመት ገና ቀረ። እግዚአብሔርም በምድር ላይ ቅሬታን አስቀርላችሁ ዘንድ በታላቅ መድኃኒትም አድናችሁ ዘንድ ከእናንተ በፊት ላከኝ። አሁንም እናንተ ወደዚህ የላካችሁኝ አይደላችሁም እግዚአብሔር ላከኝ እንጂ ለፈርዖንም እንደ አባት አደረገኝ በቤቱምም ሁሉ ላይ ጌታ በግብፅ ምድርም ሁሉ ላይ አለቃ አደረገኝ። አሁንም ፈጥናችሁ ወደ አባቴ ውጡ እንዲህም በሉት፦ ልጅህ ዮሴፍ የሚለው ነገር ይህ ነው፦ እግዚአብሔር በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ጌታ አደረገኝ፥ ወደ እኔ ና አትዘግይ በጌሤምም ምድር ትቀመጣለህ ወደ እኔም ትቀርባለህ አንተና ልጆችህ የልጆችህም ልጆች በጎችህና ላሞችህ ከብትህም ሁሉ፤ በዚያም አንተና የቤትህ ሰዎች የአንተ የሆነው ሁሉ እንዳትቸገሩ እመግብሃለሁ የራቡ ዘመን ገና አምስት ዓመት ቀርቶአልና። እነሆም ለእናንተ የተናገረቻችሁ የእኔ አፍ እንደ ሆነች የእናንተ ዓይኖች አይተዋል የወንድሜ የብንያምም ዓይኖች አይተዋል ለአባቴም በግብፅ ምድር ያለኝን ክብሬን ሁሉ ያያችሁትንም ሁሉ ንገሩት አባቴንም ወደዚህ ፈጥናችሁ አምጡት። የወንድሙን የብንያምንም አንገት አቅፎ አለቀሰ ብንያምም በአንገቱ ላይ አለቀሰ። ወንድሞቹን ሁሉ ሳማቸው በእነርሱም ላይ አለቀሰ ከዚያም በኋላ ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር ተጫወቱ። በፈርዖን ቤት፦ የዮሴፍ ወንድሞች መጡ ተብሎ ወሬ ተሰማ በዚያውም ፈርዖንና ሎላልቱ ደስ ተሰኙበት። ፈርዖንም ዮሴፍን አለው፦ ለወንድሞችህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ይህን አድርጉ ከብቶቻችሁን ጭናችሁ ወደ ከዓን ምድር ሂዱ አባታችሁንና ቤተሰቦቻችሁን ይዛችሁም ወደ እኔ ኑ እኔም የግብፅን ምድር በረከት ሁሉ እሰጣችኍለሁ፥ የምድሪቱንም ስብ ትበላላችሁ። አንተም ወንድሞችህን፦ እንዲህ አድርጉ በላቸው ከግብፅ ምድር ለሕፃናቶቻችሁ ለሴቶቻችሁም ሰረገሎች ውሰዱ አባታችሁንም ይዛችሁ ኑ ለዕቃችሁም ሁሉ አታስቡ የግብፅ በረከት ሁሉ ለእናንተ ነውና። የእስራኤል ልጆችም እንደዚሁ አደረጉ ዮሴፍም በፈርዖን ትእዛዝ ሰረገሎችንና ለመንገድ ስንቅ ሰጣቸው ለሁሉም ሁለት ሁለት መለወጫ ልብስ ሰጣቸው ለብንያም ግን ሦስት መቶ ብርና አምስት መለወጫ ልብስ ሰጠው። ለአባቱም እንደዚሁ ሰደደ የግብፅ በረከት የተሸከሙ አሥር አህዮችን ደግሞም በመንገድ ለአባቱ ስንቅ ስንዴና እንጀራ የተሸከሙ አሥር ሴቶች አህዮችን። ዮሴፍም ወንድሞቹን አሰናበታቸው እንዲህም አላቸው፦ በመንገድ እርስ በርሳችሁ አትጣሉ። እነርሱም ሄዱ ከግብፅ አገርም ወጡ ወደ ከነዓንም ምድር ከአባታቸው ከያዕቆብም ዘንድ ደረሱ። እንዲህም ብለው ነገሩት፦ ዮሴፍ ገና በሕይወት ነው እርሱም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ገዥ ሆኖአል። ያዕቆብም ልቡ ደነገጠ አላመናቸውም ነበርና። እነርሱም ዮሴፍ የነገራቸውን ነገር ሁሉ ነገሩት እርሱን ያነሡት ዘንድ ዮሴፍ የሰደዳቸውን ሰረገሎች ባያ ጊዜ የአብዝታችው የያዕቆብ የነፍሱ ሕይወት ታደስች። እስራኤልም፦ ልጄ ዮሴፍ ገና በሕይወት ከሆነ ይበቃኛል ሳልሞት እንዳየው እሄዳለሁ አለ።
ዘፍጥረት 45:1-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ዮሴፍ የናፍቆት ስሜቱን በአገልጋዮቹ ፊት መቈጣጠር ባለመቻሉ “ሁላችሁም ከዚህ ውጡ” ብሎ አዘዘ፤ ስለዚህ ዮሴፍ ማንነቱን ለወንድሞቹ በገለጠ ጊዜ ማንም የውጪ ሰው በአጠገቡ አልነበረም። በዚህ ጊዜ ግብጻውያን እስኪሰሙት ድረስ ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ፤ የፈርዖንም ቤተሰብ ወሬውን ሰማ። ዮሴፍ ወንድሞቹን “እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ አባቴ እስከ አሁን በሕይወት አለን?” አላቸው። ወንድሞቹ የተናገረውን በሰሙ ጊዜ እጅግ ደነገጡ፤ መልስ መስጠትም ተሳናቸው። በዚህ ጊዜ ዮሴፍ “እስቲ ወደ እኔ ቀረብ በሉ” አላቸው፦ ከቀረቡም በኋላ እንዲህ አላቸው፦ “እኔ ወደ ግብጽ የሸጣችሁኝ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ፤ ነገር ግን ይህን በማድረጋችሁ በመጸጸት አትበሳጩ፤ እግዚአብሔር እኔን አስቀድሞ የላከኝ የሰዎችን ሕይወት እንዳተርፍ ነው። በምድር ላይ ራብ ከገባ ሁለተኛ ዓመቱን ይዞአል፤ ሰዎች አርሰው መከር መሰብሰብ የማይችሉባቸው አምስት ዓመቶች ገና ይመጣሉ። እግዚአብሔር አስቀድሞ ወደዚህ የላከኝ በዚህ በአስደናቂ ዘዴ የእናንተን ሕይወት በማዳን በምድር ላይ ዘር እንዲቀርላችሁ አስቦ ነው። “ስለዚህ ወደዚህ የላከኝ ራሱ እግዚአብሔር እንጂ እናንተ አይደላችሁም፤ እግዚአብሔር ለፈርዖን እንደ መካሪ አባት፥ በቤት ንብረቱ ላይ ጌታና የመላው ግብጽ አገር ገዢ አደረገኝ። አሁን በፍጥነት ተመልሳችሁ ወደ አባቴ ሂዱና ልጅህ ዮሴፍ እንዲህ ይልሃል በሉት፤ ‘እግዚአብሔር የመላው ግብጽ ገዢ አድርጎኛል፤ ስለዚህ ሳትዘገይ ወደ እኔ ና፤ ልጆችህን፥ የልጅ ልጆችህን፥ በጎችህን፥ ፍየሎችህን፥ ከብቶችህን ሌላም ያለህን ነገር ሁሉ ይዘህ ና፥ በእኔው አቅራቢያ በሚገኘው በጌሴም ምድር ትኖራለህ። አምስት የራብ ዓመቶች ገና ስለሚቀሩ አንተና ቤተሰብህ እንስሶችህም ጭምር ራብ እንዳይደርስባችሁ በጌሴም እመግብሃለሁ።’ ” ቀጥሎም ዮሴፍ እንዲህ አለ፤ “አሁን የምናገራችሁ እኔ ዮሴፍ መሆኔን እናንተና አንተም ወንድሜ ብንያም አይታችሁ ለማረጋገጥ ችላችኋል፤ በግብጽ አገር ያለኝን ታላቅ ክብርና ያያችሁትንም ሁሉ ለአባቴ ንገሩት፤ በፍጥነትም ወደዚህ አምጡት።” ከዚህ በኋላ የወንድሙን የብንያምን አንገት ዐቅፎ አለቀሰ፤ ብንያምም ወንድሙን ዐቅፎ አለቀሰ፤ ዮሴፍ የቀሩትንም ወንድሞቹን አንድ ባንድ እየሳመ አለቀሰ፤ ከዚህ በኋላ ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር መነጋገር ጀመሩ። የዮሴፍ ወንድሞች መምጣት በፈርዖን ቤተ መንግሥት በተሰማ ጊዜ ፈርዖንና ባለሥልጣኖቹ ደስ አላቸው፤ ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “ወንድሞችህ አህዮቻቸውን ጭነው ወደ ከነዓን እንዲመለሱ ንገራቸው፤ አባታቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ይምጡ፤ እኔም በግብጽ አገር ለም የሆነውን ቦታ መርጬ እሰጣቸዋለሁ፤ በቂ ምግብ አግኝተው በደስታ መኖር ይችላሉ። እንዲሁም ሚስቶቻቸውን፥ ልጆቻቸውንና አባታቸውን አሳፍረው የሚያመጡበት ከግብጽ አገር ሠረገሎችን ይዘው እንዲሄዱ እዘዛቸው። በግብጽ ምድር ለም የሆነውን ቦታ ስለሚያገኙ ቤት ንብረታቸውን ትተው በመምጣታቸው ቅር አይሰኙ።” የያዕቆብ ልጆች ልክ እንደ ተነገራቸው አደረጉ፤ ዮሴፍም በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት ሠረገሎችንና ለጒዞ የሚሆናቸውን ስንቅ ሰጣቸው፤ ለእያንዳንዳቸውም አንድ አንድ የክት ልብስ ሰጣቸው፤ ለብንያም ግን አምስት የክት ልብስና ሦስት መቶ ብር ሰጠው። ለአባቱም በዐሥር አህዮች የተጫነ ከግብጽ ምድር የሚገኘውን መልካም ነገር ሁሉ ላከለት፤ እንዲሁም በሚመጣበት ጊዜ ለስንቅ የሚሆነው በሌሎች ዐሥር እንስት አህዮች የተጫነ እህል፥ ዳቦና ሌላም ምግብ ላከለት። በዚህ ሁኔታ ወንድሞቹን ካሰናበታቸው በኋላ “በመንገድ አትጣሉ” ብሎ መከራቸው። የዮሴፍ ወንድሞች ከግብጽ ተነሥተው በከነዓን ወደሚኖረው አባታቸው ወደ ያዕቆብ ተመለሱ። እዚያም እንደ ደረሱ አባታቸውን “ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ እንዲያውም በመላው ግብጽ ላይ አስተዳዳሪ ሆኖአል” አሉት። ያዕቆብ ግን እጅግ ደነገጠ፤ ሊያምናቸውም አልቻለም። ነገር ግን ዮሴፍ ያላቸውን ሁሉ በነገሩት ጊዜና እርሱን ወደ ግብጽ የሚወስዱበትን ዮሴፍ የላከለትን ሠረገላ ባየ ጊዜ ሕይወቱ በደስታ ታደሰ፤ ከዚህ በኋላ ያዕቆብ “ልጄ ዮሴፍ በሕይወት መኖሩን ካረጋገጥሁ ይበቃኛል፤ ከመሞቴ በፊት ሄጄ አየዋለሁ” አለ።
ዘፍጥረት 45:1-28 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዮሴፍም በእርሱ ዘንድ ቆመው ባሉት ሰዎች ሁሉ ፊት ሊታገሥ አልተቻለውም፦ “ሰዎቹንም ሁሉ ከፊቴ አስወጡልኝ” ብሎ ጮኾ ተናገረ፥ ዮሴፍ ለወንድሞቹ ራሱን በገለጠ ጊዜ ማንም ከአጠገቡ የቆመ አልነበረም። ድምፁንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ፥ የግብጽ ሰዎችም ሰሙ፥ በፈርዖን ቤትም ተሰማ። ዮሴፍም ለወንድሞቹ “እኔ ዮሴፍ ነኝ፥ አባቴ እስከ አሁን በሕይወቱ አለን?” አለ። ወንድሞቹም፥ በፊቱ ደንግጠው ነበርና፥ ሊመልሱለት አልቻሉም። ዮሴፍም ወንድሞቹን “እስቲ ወደ እኔ ቅረቡ” አለ። ወደ እርሱም ቀረቡ። እንዲህም አላቸው “ወደ ግብጽ የሸጣችሁኝ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። አሁንም ወደዚህ ስለ ሸጣችሁኝ አትዘኑ፥ አትቈርቈሩም፥ እግዚአብሔር ሕይወትን ለማዳን ከእናንተ በፊት ልኮኛልና። ይህ በምድር ላይ ሁለት ዓመት ራብ የሆነበት ነው፥ ገና የማይታረስበትና የማይታጨድበት አምስት ዓመት ይመጣል። እግዚአብሔርም በምድር ላይ ቅሬታን አስቀርላችሁ ዘንድ በታላቅ መድኃኒትም አድናችሁ ዘንድ ከእናንተ በፊት ላከኝ። አሁንም እናንተ ወደዚህ የላካችሁኝ አይደላችሁም፥ እግዚአብሔር ላከኝ እንጂ፥ ለፈርዖንም እንደ አባት አደረገኝ፥ በቤቱምም ሁሉ ላይ ጌታ፥ በግብጽ ምድርም ሁሉ ላይ አለቃ አደረገኝ። አሁንም ፈጥናችሁ ወደ አባቴ ውጡ፥ እንዲህም በሉት፦ ‘ልጅህ ዮሴፍ የሚለው ነገር ይህ ነው፦ እግዚአብሔር በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ ጌታ አደረገኝ፥ ወደ እኔ ና አትዘግይ፥ አንተና ልጆችህ የልጆችህም ልጆች፥ በጎችህና ላሞችህ ከብትህም ሁሉ፥ ከእኔም በቅርበት፥ በጌሤምም ምድር ትቀመጣለህ። በዚያም፥ የራቡ ዘመን ገና አምስት ዓመት ቀርቶአልና፥ አንተና የቤትህ ሰዎች የአንተ የሆነው ሁሉ እንዳትቸገሩ እመግብሃለሁ።’ እነሆም የተናገረቻችሁ የእኔ አንደበት እንደ ሆነች የእናንተ ዐይኖች አይተዋል፥ የወንድሜ የብንያምም ዐይኖች አይተዋል። ለአባቴም በግብጽ ምድር ያለኝን ክብሬን ሁሉ ያያችሁትንም ሁሉ ንገሩት፥ አባቴንም ወደዚህ ፈጥናችሁ አምጡት።” የወንድሙን የብንያምንም አንገት አቅፎ አለቀሰ፥ ብንያምም በአንገቱ ላይ አለቀሰ። ወንድሞቹን ሁሉ ሳማቸው፥ በእነርሱም ላይ አለቀሰ፥ ከዚያም በኋላ ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር ተጫወቱ። በፈርዖንም ቤት፥ “የዮሴፍ ወንድሞች መጡ ተብሎ ወሬ ተሰማ፥” በሰሙትም ነገር ፈርዖንና አገልጋዮቹ ደስ ተሰኙበት። ፈርዖንም ዮሴፍን አለው፦ “ለወንድሞችህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘ይህን አድርጉ፥ ከብቶቻችሁን ጭናችሁ ወደ ከዓን ምድር ሂዱ፥ አባታችሁንና ቤተሰቦቻችሁን ይዛችሁም ወደ እኔ ኑ፥ እኔም የግብጽን ምድር በረከት ሁሉ እሰጣችኋለሁ፥ የምድሪቱንም ስብ ትበላላችሁ።’ አንተም ወንድሞችህን፦ እንዲህ አድርጉ በላቸው፥ ከግብጽ ምድር ለሕፃናቶቻችሁ ለሴቶቻችሁም ሰረገሎችን ውሰዱ፥ አባታችሁንም ይዛችሁ ኑ፥ ለዕቃችሁም ሁሉ አታስቡ፥ የግብጽ በረከት ሁሉ ለእናንተ ነውና።” የእስራኤል ልጆችም እንደተነገራቸው አደረጉ፤ ዮሴፍም በፈርዖን ትእዛዝ ሰረገሎችንና ለመንገድ ስንቅ ሰጣቸው፤ ለእያንዳንዳቸውም አዳዲስ ልብስ ሰጣቸው፤ ለብንያም ግን አምስት የክት ልብስና ሦስት መቶ ብር ሰጠው። ለአባቱም እንደዚሁ፥ በዐሥር አህዮች የተጫነ ከግብጽ ምድር የሚገኘውን መልካም ነገር ላከለት፤ እንዲሁም በሚመጣበት ጊዜ ለስንቅ የሚሆነው በሌሎች ዐሥር እንስት አህዮች የተጫነ እህል፥ ዳቦና ምግብ ላከለት። ከዚያም ዮሴፍ ወንድሞቹን አሰናበታቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ “በመንገድ እርስ በርሳችሁ አትጣሉ።” እነርሱም ከግብጽ አገርም ወጡ፥ ወደ ከነዓንም ምድር ከአባታቸው ከያዕቆብ ዘንድ ደረሱ። እንዲህም ብለው ነገሩት፦ “ዮሴፍ ገና በሕይወቱ አለ፥ እርሱም በግብጽ ምድር ላይ ሁሉ ገዥ ሆኖአል።” ያዕቆብም ልቡ ደነገጠ፥ ሊያምናቸውም አልቻለም። ነገር ግን ዮሴፍ ያላቸውን ሁሉ በነገሩት ጊዜና እርሱን ወደ ግብጽ የሚወስዱበትን ዮሴፍ የላከለትን ሠረገላ ባየ ጊዜ ሕይወቱ በደስታ ታደሰ፤ እስራኤልም፦ “ልጄ ዮሴፍ ገና በሕይወት ከሆነ ይበቃኛል፥ ሳልሞት እንዳየው እሄዳለሁ” አለ።