ዘፍጥረት 4:1-16
ዘፍጥረት 4:1-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አዳምም ሚስቱን ሔዋንን ዐወቃት፤ ፀነሰችም፤ ቃየልንም ወለደችው። እርስዋም “ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር አገኘሁ” አለች። ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደችው። አቤልም በግ ጠባቂ ሆነ፤ ቃየልም ምድርን የሚያርስ ሆነ። ከብዙ ቀን በኋላም እንዲህ ሆነ፤ ቃየል ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ መጀመሪያ የተወለደውንና ከሰቡት አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ ወደ ቃየልና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየልንም እጅግ አሳዘነው፤ ፊቱም ጠቈረ። እግዚአብሔር አምላክም ቃየልን አለው፥ “ለምን ታዝናለህ? ለምንስ ፊትህ ጠቈረ? በእውነት ያመጣህልኝ አይደለም፤ አግባብስ በእውነት ታመጣልኝ ዘንድ ነበር። በደልህ፤ እንግዲህ ዝም በል፤ የወንድምህ መመለሻው ወደ አንተ ነው፤ አንተም ትሰለጥንበታለህ።” ቃየልም ወንድሙን አቤልን፥ “ና ወደ ሜዳ እንሂድ” አለው። በሜዳም ሳሉ ቃየል በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፤ ገደለውም። እግዚአብሔርም ቃየልን አለው፥ “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?” ቃየልም አለ፥ “አላውቅም፤ በውኑ የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?” እግዚአብሔርም አለው፥ “ቃየል! ምን አደረግህ? የወንድምህ የአቤል የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮሃል። አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ። ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኀይልዋን አትሰጥህም፤ በምድር ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ።” ቃየልም እግዚአብሔርን አለው፥ “ኀጢአቴ ይቅር የማትባል ታላቅ ናትን? እነሆ፥ ዛሬ ከምድር ፊት ከአሳደድኸኝ፥ ከፊትህ እሰወራለሁ፤ በምድርም ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ፤ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።” እግዚአብሔርም አለው፥ “እንዲህ አይደለም፤ እንግዲህ ቃየልን የገደለ ሁሉ ሰባት እጥፍ ይበቀልበታል።” እግዚአብሔርም ቃየልን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት። ቃየልም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፤ በኤዶም አንጻር ባለችው ኖድ በምትባለው ምድርም ኖረ።
ዘፍጥረት 4:1-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አዳም ሚስቱን ሔዋንን ተገናኛት፤ እርሷም ፀንሳ ቃየንን ወለደች፤ “በእግዚአብሔር ርዳታ ወንድ ልጅ አገኘሁ” አለች። ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደች። አቤል የበግ እረኛ፣ ቃየንም ዐራሽ ነበር። በአንድ ወቅት፣ ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረበ። አቤልም መጀመሪያ ከተወለዱት በጎቹ መካከል ስባቸውን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። እግዚአብሔር ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ በቃየንና በመሥዋዕቱ ግን አልተደሰተም፤ ስለዚህ ቃየን ክፉኛ ተናደደ፤ ፊቱም ጠቈረ። እግዚአብሔርም ቃየንን እንዲህ አለው፤ “ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቈረ? መልካም ብታደርግ ተቀባይነትን አታገኝምን? መልካም ባታደርግ ግን፣ ኀጢአት በደጅህ እያደባች ናት፤ ልታሸንፍህ ትፈልጋለች፤ አንተ ግን ተቈጣጠራት።” ቃየንም ወንድሙን አቤልን፣ “እስኪ ና፤ ወደ መስኩ እንውጣ” አለው፤ በመስኩም ሳሉ፣ ቃየን ወንድሙን አቤልን አጠቃው፤ ገደለውም። ከዚያም፣ እግዚአብሔር ቃየንን፣ “ወንድምህ አቤል የት ነው?” አለው። ቃየንም፣ “አላውቅም፤ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” ሲል መለሰ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “ምንድን ነው ያደረግኸው? የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። እንግዲህ የተረገምህ ነህ፤ የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፏን ከከፈተችው መሬት ትሰደዳለህ። ብታርሳትም ፍሬዋን አትለግስህም፤ በምድር ላይ ኰብላይና ተንከራታች ትሆናለህ።” ቃየንም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ቅጣቴ ልሸከመው ከምችለው በላይ ነው። እነሆ፤ ዛሬ ከምድሪቱ አባረርኸኝ፤ ከፊትህም እሸሸጋለሁ፤ በምድር ላይ ኰብላይና ተንከራታች እሆናለሁ፤ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።” እግዚአብሔር ግን፣ “የለም! እንደርሱ አይሆንም፤ ማንም ቃየንን ቢገድል፣ ሰባት ዕጥፍ የበቀል ቅጣት ይቀበላል” አለው፤ ስለዚህ፣ ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው እግዚአብሔር በቃየን ላይ ምልክት አደረገለት። ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ ሄዶ፣ ከዔድን በስተምሥራቅ በምትገኝ ኖድ በተባለች ምድር ተቀመጠ።
ዘፍጥረት 4:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አዳምም ሚስቱን ሔዋንን አወቀ ፀነሰችም፤ ቃየንንም ወለደች። እርስዋም ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር አገኘሁ አለች። ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደች። አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ፤ ቃየንም ምድርን የሚያርስ ነበረ። ከብዙ ቀን በኍላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ። እግዚአብሔርም ቃየንን አለው፤ ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለም? መልካም ባታደርግ ግን ኂጢአት በደጅ ታደባለች፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት። ቃየንም ወንድሙን አቤልን፤ ና ወደ ሜዳ እንሂድ አለው። በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፤ ገደለውም። እግዚአብሔርም ቃየንን አለው፤ ወንድምህ አቤል ወዴት ነው? እርሱም አለ፤ አላውቅም የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን? አለውም፤ ምን አደረግህ? የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኽል። አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፍተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ። ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኂይልዋን አትሰጥህም፤ በምድርም ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ። ቃየንም እግዚአብሔርን አለው፤ ኂጢአቴ ልሸከማት የማልችላት ታላቅ ናት። እነሆ ዛሬ ከምድር ፊት አሳደድኽኝ፤ ከፊትህም እሰወራለሁ፤ በምድርም ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ፤ የሚያገኘንም ሁሉ ይገድለኚል። እግዚአብሔርም እርሱን አለው፤ እንግዲህ ቃየንን የገደለ ሁሉ ሰባት እጥፍ ይበቀልብታል። እግዚአብሔርም ቃየንን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት። ፕ ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ ከዔድንም ወደ ምሥራቅ በኖድ ምድር ተቀመጠ።
ዘፍጥረት 4:1-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አዳም ከሚስቱ ከሔዋን ጋር ግንኙነት አደረገ፤ እርስዋም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ “በእግዚአብሔር ርዳታ ወንድ ልጅ አገኘሁ” ስትል “ቃየል” የሚል ስም አወጣችለት። ቀጥሎም የቃየልን ወንድም አቤልን ወለደች፤ አቤል የበጎች ጠባቂ ሆነ፤ ቃየል ግን ገበሬ ሆነ። ከብዙ ቀን በኋላም ቃየል ካመረተው ሰብል ወስዶ ለእግዚአብሔር መባ አቀረበ። አቤልም ከበጎቹ መንጋ በመጀመሪያ የተወለደውን አንድ ጠቦት አመጣ፤ ካረደውም በኋላ የሰባውንና መልካም የሆነውን ብልት ሁሉ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ እግዚአብሔርም በአቤልና በመሥዋዕቱ ደስ አለው። ለቃየልና ለመሥዋዕቱ ግን ግምት አልሰጣቸውም፤ በዚህ ምክንያት ቃየል በጣም ተቈጣ፤ ፊቱም በቊጣ ተኮሳተረ፤ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ቃየልን እንዲህ አለው፤ “የተቈጣኸውና ፊትህም በቊጣ የተኰሳተረው ለምንድን ነው? መልካም ነገር አድርገህ ቢሆን ኖሮ ተቀባይነት አይኖርህም ነበርን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በበርህ ላይ ያደባል፤ በቊጥጥሩ ሥር ሊያደርግህም ይፈልጋል፤ ሆኖም አንተ ልታሸንፈው ይገባል።” ከዚህ በኋላ ቃየል ወንድሙን አቤልን “ና ወደ ሜዳ እንሂድ” አለው፤ ወደ ሜዳም በሄዱ ጊዜ ቃየል በጠላትነት ተነሥቶ ወንድሙን አቤልን ገደለው። እግዚአብሔርም ቃየልን “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?” ሲል ጠየቀው፤ ቃየልም “የት እንዳለ አላውቅም፤ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” ብሎ መለሰ። እግዚአብሔርም ቃየልን እንዲህ አለው፤ “ምን አደረግህ? የፈሰሰው የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ እየጮኸ ነው፤ የወንድምህን ደም ከአንተ ለመቀበል አፍዋን በከፈተችው ምድር ላይ የተረገምክ ነህ። ምድርንም በምታርስበት ጊዜ ምንም ፍሬ አትሰጥህም፤ በምድር ላይም ስደተኛ ሆነህ ትንከራተታለህ።” ቃየልም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ይህ ቅጣት እኔ ልሸከመው ከምችለው በላይ ነው፤ እነሆ፥ ዛሬ ከምድር አባረርከኝ፤ ከፊትህም እሰወራለሁ፤ በምድርም ላይ ስደተኛና ተንከራታች እሆናለሁ፤ እንግዲህ ማንም ሰው ቢያገኘኝ ይገድለኛል።” እግዚአብሔር ግን “ማንም አይነካህም፤ አንተን የሚገድል ሰባት እጥፍ የበቀል ቅጣት ይደርስበታል” አለው። ስለዚህ እግዚአብሔር ቃየልን ማንም ቢያገኘው እንዳይገድለው የሚያስጠነቅቅ ልዩ ምልክት አደረገለት። ከዚህ በኋላ ቃየል ከእግዚአብሔር ፊት ርቆ ሄደ፤ በዔደን በስተምሥራቅ በሚገኘው በኖድ ምድር ኖረ።
ዘፍጥረት 4:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አዳምም ሚስቱን ሔዋንን አወቀ፥ እሷም ፀነሰች፥ ቃየንንም ወለደች። እርሷም፦ “ወንድ ልጅ በጌታ ርዳታ አገኘሁ” አለች። ደግሞም፥ ወንድሙን አቤልን ወለደች። አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ፥ ቃየንም መሬትን የሚያርስ ነበረ። ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለጌታ መሥዋዕትን አቀረበ፥ እንዲሁም አቤል ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። ጌታም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፥ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየንም እጅግ ተቈጣ፥ ፊቱም ጠቆረ። ጌታም ቃየንን አለው፦ “ስለምን ተናደድህ? ፊትህስ ለምን ጠቆረ? መልካም ነገር አድርገህ ቢሆን ኖሮ ተቀባይነት አይኖርህም ነበርን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች፥ ፍላጎትዋም ወደ አንተ ነው፥ አንተ ግን በእርሷ ልትሰለጥንባት ይገባል።” ቃየንም ወንድሙን አቤልን፥ “ና ወደ ሜዳ እንሂድ” አለው። በሜዳም ሳሉ፥ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፥ ገደለውም። ጌታም ቃየንን፥ “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?” አለው። እርሱም፥ “አላውቅም፥ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝ?” አለ። ጌታም ቃየልን እንዲህ አለው፥ “ምን አደረግህ? የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ። ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኃይልዋን አትሰጥህም፥ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ።” ቃየንም ጌታን አለው፦ “ኃጢአቴ ልሸከማት የማልችላት ታላቅ ናት። እነሆ ዛሬ ከምድር ፊት አሳደድኸኝ፥ ከፊትህም እሰወራለሁ፥ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ፥ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።” እግዚአብሔርም ለእርሱ፥ “እንዲህስ አይሆንም! ማንም ቃየንን የሚገድል፥ ሰባት እጥፍ የበቀል ቅጣት ይደርስበታል” አለው። ጌታም ቃየንን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት። ከዚያም ቃየን ከጌታ ፊት ወጣ፥ ከዔድንም በስተ ምሥራቅ፥ በኖድም ምድር ተቀመጠ።