ዘፍጥረት 36:1-8
ዘፍጥረት 36:1-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኤዶም የተባለው የዔሳው ትውልድ እንዲህ ነው። ዔሳው ከከነዓን ልጆች ሚስቶችን አገባ፤ የኬጤያዊውን የዔሎን ልጅ ሐዳሶን፥ የኤውያዊው የሴቤሶ ልጅ ሐና የወለዳትን ኤሌባማን፥ የይስማኤልን ልጅ የናቡአት እኅት ቤሴሞትን። ሐዳሶ ለእርሱ ኤልፋዝን ወለደች፤ ቤሴሞትም ራጉኤልን ወለደች፤ ኤሌባማም ዮሔልን፥ ይጉሜልን፥ ቆሬንም ወለደች። በከነዓን ምድር የተወለዱለት የዔሳው ልጆች እነዚህ ናቸው። ዔሳውም ሚስቶቹን፥ ወንዶች ልጆቹንና ሴቶች ልጆቹን፥ ቤተ ሰቡንም ሁሉ፥ እንስሶቹንም ሁሉ፥ በከነዓንም ሀገር ያገኘውን ገንዘቡን ሁሉ ይዞ ከወንድሙ ከያዕቆብ ፊት ከከነዓን ሀገር ሄደ። ከብታቸው ስለበዛ በአንድነት ይቀመጡ ዘንድ አልቻሉም፤ በእንግድነት የተቀመጡባትም ምድር ከከብታቸው ብዛት የተነሣ ልትበቃቸው አልቻለችም። ዔሳውም በሴይር ተራራ ተቀመጠ፤ ዔሳውም ኤዶም ነው።
ዘፍጥረት 36:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኤዶም የተባለው የዔሳው ትውልድ ይህ ነው። ዔሳው ከከነዓን ሴቶች አገባ፤ እነርሱም፦ የኬጢያዊው የኤሎን ልጅ ዓዳን፣ የኤዊያዊው የፂብዖን ልጅ ዓና የወለዳት ኦሆሊባማ፣ እንዲሁም የነባዮት እኅት የሆነችው የእስማኤል ልጅ ቤሴሞት ነበሩ። ዓዳ ለዔሳው ኤልፋዝን ወለደችለት፤ ቤሴሞት ደግሞ ራጉኤልን ወለደችለት። እንደዚሁም ኦሆሊባማ የዑስን፣ የዕላምንና ቆሬን ወለደችለት፤ እነዚህ ዔሳው በከነዓን አገር የወለዳቸው ልጆች ናቸው። ዔሳው ሚስቶቹን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን፣ ቤተ ሰቦቹን በሙሉ እንደዚሁም የቀንድ ከብቶቹንና ሌሎቹንም እንስሳት ሁሉ በከነዓን ምድር ያፈራውን ሀብት እንዳለ ይዞ ከወንድሙ ከያዕቆብ ራቅ ወዳለ ቦታ ሄደ። ብዙ ሀብት ስለ ነበራቸው ዐብረው መኖር አልቻሉም፤ የነበሩበትም ስፍራ ከከብቶቻቸው ብዛት የተነሣ ሊበቃቸው አልቻለም። ስለዚህ ኤዶም የተባለው ዔሳው መኖሪያውን በተራራማው አገር በሴይር አደረገ።
ዘፍጥረት 36:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የዔሳው ትውልድ ይህ ነው፤ እርሱም ኤዶም ነው። ዔሳው ከከነዓን ልጆች ሚስቶችን አገባ፤ የኬጢያዊውን የዔሎንን ልጅ ዓዳን የኤዊያዊው የፅብዖን ልጅ ዓን የወለዳትን አህሊባማም፥ የእስማኤልን ልጅ የነባዮትን እኅት ቤሴሞትን። ዓዳ ለዔሳው ኤልፋዝን ወለደች ቤሴሞትም ራጉኤልን ወለደች፤ አህሊባማም የዑስን የዕላምን፥ ቆሬን ወለደች፤ በከነዓን ምድር የተወለዱለት የዔሳው ልጆች እነዚህ ናቸው። ዔሳውም ሚስቶቹን ወንዶች ልጅቹንና ሴቶች ልጆቹን ቤተሰቡንም ሁሉ ከብቱንም ሁሉ እንስሶቹንም ሁሉ በከንዓንም አገር ያገኘውን ሁሉ ይዞ ከወንድሙ ከያዕቆብ ፊት ወደ ሌላ አገር ሄደ። ከብታቸው ስለ በዛ በአንድነት ይቀመጡ ዘንድ አልታሉም በእንግድነት የተቀመጡባትም ምድር ከከብታቸው ብዛት የተነሣ ልትበቃቸው አልቻለችም። ዔሳውም በሴይር ተራራ ተቀመጠ ዔሳውም ኤዶም ነው።
ዘፍጥረት 36:1-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኤዶም የተባለው የዔሳው የትውልድ ታሪክ የሚከተለው ነው፤ ዔሳው ከነዓናውያን ሴቶችን አገባ፤ እነርሱም የሒታዊው የኤሎን ልጅ ዓዳ፥ የሒዋዊው የጺባዖን ልጅ ዐና የወለዳት ኦሆሊባማን እና፥ የነባዮት እኅት የነበረችው የእስማኤል ልጅ ባሴማት ናቸው። ዓዳ ለዔሳው ኤሊፋዝን ወለደችለት፤ ባሴማትም ረዑኤልን ወለደችለት፤ ኦሆሊባማም የዑሻን፥ ያዕላምንና ቆሬን ወለደችለት። እነዚህ ሁሉ ለዔሳው በከነዓን ምድር የተወለዱለት ልጆች ናቸው። ከዚህ በኋላ ዔሳው ሚስቶቹን ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን፥ በቤቱ የሚገኙትን ሰዎች ሁሉ መንጋዎቹንና ሌሎቹንም ከብቶች ሁሉ፥ በከነዓን ሳለ ያፈራውን ንብረት ሁሉ ይዞ ከወንድሙ ከያዕቆብ ራቅ ወዳለ ቦታ ሄደ። ይህንንም ያደረገበት ምክንያት እርሱና ያዕቆብ ብዙ ንብረት ስለ ነበራቸው፥ የሚሰፍሩበት ምድር ለሁለት ስላልበቃ ነው፤ ሁለቱም ብዙ እንስሶች ስለ ነበሩአቸው አብረው ለመኖር አልቻሉም። ስለዚህ ኤዶም የተባለው ዔሳው በተራራማው አገር በኤዶም ተቀመጠ።
ዘፍጥረት 36:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የዔሳው ትውልድ ይህ ነው፥ እርሱም ኤዶም ነው። ዔሳው ከከነዓን ልጆች ሚስቶችን አገባ፥ የኬጢያዊውን የዔሎንን ልጅ ዓዳን፥ የሒዋዊው የፅብዖን ልጅ ዓና የወለዳትን ኦሆሊባማን፥ የእስማኤልን ልጅ የነባዮትን እኅት ባሴማትን። ዓዳ ለዔሳው ኤልፋዝን ወለደች፥ ባሴማትም ራዑኤልን ወለደች፥ ኦሆሊባማም የዑሽን፥ ያዕላምን፥ ቆሬን ወለደች። በከነዓን ምድር የተወለዱለት የዔሳው ልጆች እነዚህ ናቸው። ዔሳውም ሚስቶቹን፥ ወንዶች ልጆቹንና ሴቶች ልጆቹን፥ ቤተሰቡንም ሁሉ፥ እንስሶቹንም ሁሉ፥ በከነዓንም ሀገር ያገኘውን ንብረቱን ሁሉ ይዞ ከወንድሙ ከያዕቆብ ራቅ ወዳለ ቦታ ሄደ። ከብታቸው ስለ በዛ በአንድነት ይቀመጡ ዘንድ አልቻሉም፥ በእንግድነት የተቀመጡባትም ምድር ከከብታቸው ብዛት የተነሣ ልትበቃቸው አልቻለችም። ዔሳውም በሴይር ተራራ ተቀመጠ፥ ዔሳው ኤዶም ነው።