ዘፍጥረት 3:14-24
ዘፍጥረት 3:14-24 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔር አምላክም እባቡን አለው፥ “ይህን ስላደረግህ ከእንስሳት ሁሉ፥ ከምድር አራዊትም ሁሉ ተለይተህ አንተ የተረገምህ ሁን ፤ በደረትህና በሆድህም ትሄዳለህ፤ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ አፈርን ትበላለህ። በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ሰኰናውን ትነድፋለህ።” ለሴቲቱም እግዚአብሔር አላት፥ “ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ከወለድሽም በኋላ ፈቃድሽ ወደ ባልሽ ይሆናል፤ እርሱም ይገዛሻል።” እግዚአብሔርም አዳምን አለው፥ “የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ከአዘዝሁህ ከዚያ ዛፍም በልተሃልና ምድር በሥራህ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ። ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራህን ትበላለህ፤ አፈር ነህና ወደ አፈርም ትመለሳለህና።” አዳምም ለሚስቱ “ሔዋን” ብሎ ስም አወጣ፤ የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና። እግዚአብሔር አምላክም ለአዳምና ለሚስቱ የቁርበትን ልብስ አደረገላቸው፥ አለበሳቸውም። እግዚአብሔር አምላክም አለ፥ “እነሆ፥ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤ አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ፥ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፥ ለዘለዓለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር፥” ስለዚህ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ደስታ ከሚገኝባት ገነት አስወጣው። አዳምንም አስወጣው፤ ደስታ በሚገኝባት በገነት አንጻርም አኖረው፤ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በእጃቸው የያዙ ኪሩቤልን አዘዛቸው።
ዘፍጥረት 3:14-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር አምላክ እባብን እንዲህ አለው፤ “ይህን ስለ ሠራህ፣ “ከከብቶችና ከዱር እንስሳት ሁሉ ተለይተህ የተረገምህ ሁን፤ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፣ በደረትህ እየተሳብህ ትሄዳለህ፤ ዐፈርም ትበላለህ። በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።” ሴቲቱንም እንዲህ አላት፤ “በምጥ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛለሁ፤ በሥቃይም ትወልጃለሽ፤ ፍላጎትሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፤ እርሱም የበላይሽ ይሆናል።” አዳምንም እንዲህ አለው፤ “የሚስትህን ቃል ሰምተህ፣ ‘ከርሱ አትብላ’ ብዬ ያዘዝሁህን ዛፍ በልተሃልና፣ “ከአንተ የተነሣ ምድር የተረገመች ትሁን፤ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ምግብህን ጥረህ ግረህ ከርሷ ታገኛለህ። ምድርም እሾኽና አሜከላ ታበቅልብሃለች፤ ከቡቃያዋም ትበላለህ። ከምድር ስለ ተገኘህ፣ ወደ መጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ እንጀራህን በፊትህ ላብ ትበላለህ፤ ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ።” አዳምም የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና ሚስቱን ሔዋን ብሎ ጠራት። እግዚአብሔር አምላክ ከቈዳ ልብስ አዘጋጅቶ አዳምንና ሚስቱን አለበሳቸው። ከዚያም እግዚአብሔር አምላክ፣ “ሰው መልካምንና ክፉውን ለይቶ በማወቅ ረገድ አሁን ከእኛ እንደ አንዱ ሆኗል፤ አሁን ደግሞ እጁን ዘርግቶ ከሕይወት ዛፍ ቀጥፎ እንዳይበላ፣ ለዘላለምም እንዳይኖር ይከልከል” አለ። ስለዚህ የተገኘበትን ምድር እንዲያርስ፣ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከዔድን የአትክልት ስፍራ አስወጣው፤ ሰውንም ካስወጣው በኋላ፣ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና በየአቅጣጫው የምትገለባበጥ ነበልባላዊ ሰይፍ ከዔድን በስተምሥራቅ አኖረ።
ዘፍጥረት 3:14-24 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔር አምላክም እባቡን አለው፦ ይህን ስላደረገህ ከእንስሳት ከምድር አራዊትም ሁሉ ተለይተህም ትሄዳለህ፤ አፈርንም በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ትበላለህ። በአንተና በሴቲቱ መካከል፤ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ። ለሴቲቱም አለ፤ በፀነሰሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፤ እርሱም ገዥሽ ይሆናል። አዳምም አለው፤ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፤ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ። ወደ ወጣህብት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀርን ትበላለህ፤ አፈር ነህና ወደ አፈርም ትመለሳለህና። አዳምም ለሚስቱ ሔዋን ብሎ ስም አወጣ፤ የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና። እግዚአብሔር አምላክም ለአዳምና ለሚስቱ የቁርበትን ልብስ አደረገላቸው፤ አለበሳቸውም። ፕ እግዚአብሔር አምላክም አለ፤ እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኚ እንደ አንዱ ሆኑ፤ አሁንም እጁን እንዳይዘጋ፤ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፤ ለዘላለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ከዔድን ገነት አስወጣው፤ የተገኘባርን መሬት ያርስ ዘንድ። አዳምንም አስወጣው፤ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልበል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ።
ዘፍጥረት 3:14-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ እባቡን እንዲህ አለው፦ “ይህን በማድረግህ ከእንስሶችና ከአራዊት ሁሉ ተለይተህ የተረገምክ ሁን፤ ከዛሬ ጀምሮ በደረትህ እየተሳብክ ሂድ፤ ዕድሜህን ሙሉ ዐፈር ብላ፤ በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በአንተ ዘርና በእርስዋ ዘር መካከል ጠላትነት እንዲኖር አደርጋለሁ። የእርስዋ ዘር የአንተን ራስ ይቀጠቅጣል፤ አንተም የእርስዋን ዘር ተረከዝ ትነክሳለህ።” ሴቲቱንም፥ “በእርግዝናሽ ወራት ጭንቀትሽን፥ በምትወልጂበትም ጊዜ የምጥ ሥቃይሽን አበዛሁ፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ፍላጎትሽ ለባልሽ ይሆናል። ለእርሱም ታዛዥ ትሆኚአለሽ” አላት። አዳምንም እንዲህ አለው፥ “የሚስትህን ቃል ሰምተህ ‘አትብላ’ ያልኩህን ፍሬ ከዛፉ ወስደህ ስለ በላህ፥ አንተ በፈጸምከው ክፉ ሥራ ምክንያት ምድር የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህ ሁሉ ምግብህን ከእርስዋ የምትበላው በብርቱ ድካም ነው። ምድር እሾኽና አሜከላ ታበቅላለች፤ አንተም የዱር ተክሎችን ትበላለህ። ወደ መጣህበት ወደ መሬት እስክትመለስ ድረስ፥ እንጀራህን በግንባርህ ላብ ትበላለህ።” ዐፈር ነህና፥ ወደ ዐፈርም ትመለሳለህ። አዳምም ሚስቱ ሕይወት ላላቸው ሰብአዊ ፍጡሮች ሁሉ እናት ስለ ሆነች “ሔዋን” የሚል ስም አወጣላት። እግዚአብሔር አምላክም ለአዳምና ለሔዋን ከቆዳ ልብስ ሠርቶ አለበሳቸው። እግዚአብሔር አምላክም እንዲህ አለ፦ “እነሆ፥ አዳም ክፉንና ደግን በማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤ አሁንም እጁን ዘርግቶ ከሕይወት ዛፍ ወስዶ በመብላት ለዘለዓለም እንዲኖር አይገባውም።” በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ከዔደን የአትክልት ቦታ አስወጣው፤ የተገኘበትንም ምድር እንዲያለማ አደረገው። አዳምንም ካስወጣው በኋላ ከዔደን የአትክልት ቦታ በስተ ምሥራቅ በኩል ኪሩቤል የተባሉትን መላእክትንና በየአቅጣጫው እየተገለባበጠ እንደ እሳት የሚንበለበለውን ሰይፍ አኖረ፤ ይህንንም ያደረገው ማንም ወደ ሕይወት ዛፍ እንዳይጠጋ ነው።
ዘፍጥረት 3:14-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታ እግዚአብሔርም እባቡን አለው፦ “ይህን በማድረግህ፥ ከእንስሳት ከምድር አራዊትም ሁሉ ተለይተህ አንተ የተረገምህ ትሆናለህ፤ በሆድህም ትሄዳለህ፥ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ አፈርን ትበላለህ። “በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ “በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፥ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትነድፋለህ።” ለሴቲቱም አላት፥ “በእርግዝናሽ ወራት ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፥ በጭንቅ ትወልጃለሽ፥ ይህም ሁሉ ሆኖ ፍላጎትሽ ለባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል።” አዳምንም አለው፦ “የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም ከእርሱ በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፥ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርሷ ትበላለህ፤ “እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፥ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ።” “ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በግንባርህ ላብ እንጀራን ትበላለህ፥ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህ።” አዳምም ለሚስቱ “ሔዋን” ብሎ ስም አወጣ፤ የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና። ጌታ እግዚአብሔርም ለአዳምና ለሚስቱ የቁርበትን ልብስ አደረገላቸው፥ አለበሳቸውም። ከዚያም ጌታ እግዚአብሔርም፥ “እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፥ አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ፥ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፥ ለዘለዓለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር”፥ አለ። ስለዚህ፥ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ፥ ጌታ እግዚአብሔር ከዔድን ገነት አስወጣው። አዳምንም ካስወጣው በኋላ፥ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና በሁሉም አቅጣጫ የምትውለበለብ ነበልባላዊ ሰይፍን በዔድን ገነት በስተ ምሥራቅ አስቀመጠ።