ዘፍጥረት 2:7-9
ዘፍጥረት 2:7-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር ፈጠረው፤ በፊቱም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። እግዚአብሔር አምላክም በኤዶም በስተምሥራቅ ገነትን ተከለ፤ የፈጠረውንም ሰው በዚያ አኖረው። እግዚአብሔር አምላክም ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፥ ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ደግሞ ከምድር አበቀለ፤ በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ፥ መልካምንና ክፉን የሚያሳየውንና የሚያስታውቀውንም ዛፍ አበቀለ።
ዘፍጥረት 2:7-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ። እግዚአብሔር አምላክ በምሥራቅ፣ በዔድን የአትክልት ስፍራ አዘጋጀ፤ ያበጀውንም ሰው በዚያ አኖረው። እግዚአብሔር አምላክም ለዐይን የሚያስደስት ለመብልም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፤ በአትክልቱ ቦታ መካከልም የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ እንዲሁም መልካምና ክፉን መለየት የሚያስችለው የዕውቀት ዛፍ ነበረ።
ዘፍጥረት 2:7-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔር አምላክም ሰውንም ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን ገነትን ተከለ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው። እግዚአብሔር አምላክም ለማየት ደስ የሚያስኘውን፤ ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፤ በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ፤ መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀውንም ዛፍ አበቀለ።
ዘፍጥረት 2:7-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ከመሬት ዐፈር ወስዶ፥ ሰውን ከዐፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም ሕይወትን የሚሰጥ እስትንፋስ “እፍ” አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ፍጡር ሆነ። እግዚአብሔር አምላክ በስተምሥራቅ በኩል በዔደን የአትክልት ቦታን አዘጋጀ፤ የፈጠረውንም ሰው በዚያ እንዲኖር አደረገው። በዚያም ለዐይን የሚያስደስቱና ለምግብነት የሚጠቅሙ ልዩ ልዩ ዛፎች እንዲበቅሉ አደረገ፤ ደግሞም በአትክልቱ ቦታ መካከል ሕይወት የሚሰጥ ዛፍ ነበረ፤ እንዲሁም ደጉን ከክፉ ለመለየት የሚያስችል ዕውቀት የሚሰጥ ሌላ ዛፍ ነበረ።
ዘፍጥረት 2:7-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዚህ በኋላ ጌታ እግዚአብሔር ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፥ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፥ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። ጌታ እግዚአብሔርም፥ በስተ ምሥራቅ፥ በዔድን ገነትን ተከለ፤ የፈጠረውንም ሰው ከዚያ አኖረው። በዚያም፥ ጌታ እግዚአብሔር ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፥ ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፥ በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ፥ መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀውንም ዛፍ አበቀለ።