ዘፍጥረት 17:17-22 - Compare All Versions

ዘፍጥረት 17:17-22 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))

አብ​ር​ሃ​ምም በግ​ን​ባሩ ወደቀ፤ ሳቀም፤ በል​ቡም እን​ዲህ ብሎ አሰበ፥ “የመቶ ዓመት ሰው ስሆን በውኑ እኔ ልጅ እወ​ል​ዳ​ለ​ሁን? ዘጠና ዓመት የሆ​ና​ትም ሣራ ትወ​ል​ዳ​ለ​ችን?” አብ​ር​ሃ​ምም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን አለው፥ “ይህ ይስ​ማ​ኤል ብቻ በፊ​ትህ ይኖ​ር​ልኝ ዘንድ አቤቱ፥ እማ​ል​ድ​ሃ​ለሁ።” እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም አብ​ር​ሃ​ምን አለው፥ “እሺ እነሆ፥ ሚስ​ትህ ሣራ ወንድ ልጅን ትወ​ል​ድ​ል​ሃ​ለች፤ ስሙ​ንም ይስ​ሐቅ ብለህ ትጠ​ራ​ዋ​ለህ፤ ለእ​ር​ሱና ከእ​ርሱ በኋላ ለዘሩ አም​ላክ እሆን ዘንድ ቃል ኪዳ​ኔን ለዘ​ለ​ዓ​ለም ቃል ኪዳን ከእ​ርሱ ጋር አቆ​ማ​ለሁ። ስለ ይስ​ማ​ኤ​ልም እነሆ፥ ሰም​ቼ​ሃ​ለሁ፤ እባ​ር​ከ​ዋ​ለሁ፤ አበ​ዛ​ዋ​ለሁ፤ እጅ​ግም አበ​ዛ​ዋ​ለሁ፤ ዐሥራ ሁለት አለ​ቆ​ች​ንም ይወ​ል​ዳል፤ ታላቅ ሕዝ​ብም አደ​ር​ገ​ዋ​ለሁ። ቃል ኪዳ​ኔን ግን በሚ​መ​ጣው ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከም​ት​ወ​ል​ድ​ልህ ከይ​ስ​ሐቅ ጋር አቆ​ማ​ለሁ።” እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ንግ​ግ​ሩን ከእ​ርሱ ጋር በፈ​ጸመ ጊዜ ከአ​ብ​ር​ሃም ተለ​ይቶ ወጣ።

ዘፍጥረት 17:17-22 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)

አብርሃምም በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤ ሣቀና በልቡ፣ “እንዲያው ምንስ ቢሆን የመቶ ዓመት ሽማግሌ የልጅ አባት መሆን ይችላልን? ሣራስ በዘጠና ዓመቷ ልጅ መውለድ ትችላለችን?” አለ። አብርሃም እግዚአብሔርን፣ “እስማኤልን ብቻ ባርከህ ባኖርህልኝ” አለው። እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “ይሁን ዕሺ፤ ነገር ግን ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ይሥሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ፤ እኔም ከርሱ በኋላ ለዘሩ ሁሉ የሚሆን የዘላለም ኪዳን ከርሱ ጋራ እገባለሁ። ስለ እስማኤልም ቢሆን ልመናህን ሰምቼሃለሁ፤ እርሱንም እባርከዋለሁ፤ ፍሬያማም አደርገዋለሁ፤ እጅግም አበዛዋለሁ፤ የዐሥራ ሁለት አለቆች አባት ይሆናል፤ ታላቅም ሕዝብ አደርገዋለሁ። ኪዳኔን ግን የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ ልጅ፣ ከይሥሐቅ ጋራ አደርጋለሁ።” እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋራ መነጋገሩን ከፈጸመ በኋላ ወደ ላይ ወጣ።

ዘፍጥረት 17:17-22 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))

አብርሃምም በግምባሩ ወደቀ፥ ሳቀም፥ በልቡም አለ፥ የመቶ ዓመት ሰው በውኑ ልጅ ይወልዳልን? ዘጠና ዓመት የሆናትም ሣራ ትወልዳለችን? አብርሃምም እግዚአብሔርን፥ እስማኤል በፊትህ ቢኖር በወደድሁ ነበር አለው። እግዚአብሔርም አለ፥ በእውነት ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ይስሐቅ ብልህ ትጠራዋለህ፤ ከእርሱ በኍላ ለዘሩ የዘላለም ቃል ኪዳን እንዲሆን ቃል ኪዳኔን ከእርሱ ጋር አቆማለሁ። ስለ እስማኤልም ሰምቼሃለሁ፤ እነሆ ባርኬዋለሁ፥ ፍሬያምም አደርገዋለሁ፥ እጅግም አበዛዋለሁ፤ አሥራ ሁለት አለቆችንም ይወልዳል፥ ታላቅ ሕዝብም እንዲሆን አደርገዋለሁ። ቃለ ኪዳኔን ግን በሚመጣው ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ ከይስሐቅ ጋር አቆማለሁ። ንግግሩንም ከእርሱ ጋር በፈጸም ጊዜ እግዚአብሔር ከአብርሃም ተለይቶ ወጣ።

ዘፍጥረት 17:17-22 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

አብርሃም ግንባሩ መሬት እስኪነካ ድረስ ዝቅ ብሎ ሰገደ፤ ነገር ግን “ዕድሜው መቶ ዓመት የሆነው ሰው ልጅ መውለድ ይችላልን? ሣራስ በዘጠና ዓመትዋ ልጅ ልትወልድ ትችላለችን?” ብሎ በማሰብ ሳቀ፤ አብርሃምም እግዚአብሔርን፦ “እስማኤልን በፊትህ ብታኖረው ምንኛ መልካም ነበር” አለው። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “እንዲህስ አይሆንም፤ ነገር ግን ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ይስሐቅ ትለዋለህ፤ ቃል ኪዳኔን ከእርሱና ከዘሩ ጋር ለዘለዓለም አጸናለሁ፤ ስለ እስማኤል ያቀረብከውንም ልመና ሰምቼአለሁ፤ እርሱንም እባርከዋለሁ፤ ብዙ ልጆችን እሰጠዋለሁ፤ ዘሩንም እጅግ አበዛዋለሁ፤ እርሱ የዐሥራ ሁለት መሳፍንት አባት ይሆናል፤ ዘሩንም ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁ። ነገር ግን የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ ከሣራ ከሚወለደው ልጅህ ከይስሐቅ ጋር ቃል ኪዳኔን አጸናለሁ።” እግዚአብሔር አብርሃምን ካነጋገረው በኋላ ከእርሱ ተለይቶ ወደ ላይ ወጣ።

ዘፍጥረት 17:17-22 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))

አብርሃምም በግምባሩ ወደቀ፥ ሳቀም፥ በልቡም አለ፦ “የመቶ ዓመት ሰው በውኑ ልጅ ይወልዳልን? ዘጠና ዓመት የሆናትም ሣራ ትወልዳለችን?” አብርሃምም እግዚአብሔርን፥ “እስማኤል በፊትህ ቢኖር በወደድሁ ነበር” አለው። እግዚአብሔርም አለ፦ “በእውነት ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ፥ ከእርሱ በኋላ ለዘሩ የዘለዓለም ቃል ኪዳን እንዲሆን ቃል ኪዳኔን ከእርሱ ጋር አቆማለሁ። ስለ እስማኤልም ሰምቼሃለሁ፥ እነሆ ባርኬዋለሁ፥ ፍሬያምም አደርገዋለሁ፥ እጅግም አበዛዋለሁ፥ ዐሥራ ሁለት አለቆችንም ይወልዳል፥ ታላቅ ሕዝብም እንዲሆን አደርገዋለሁ። ቃል ኪዳኔን ግን በሚመጣው ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ ከይስሐቅ ጋር አቆማለሁ።” ንግግሩንም ከእርሱ ጋር በፈጸመ ጊዜ እግዚአብሔር ከአብርሃም ተለይቶ ወጣ።