ገላትያ 6:7-18
ገላትያ 6:7-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አያስቱአችሁ፤ በእግዚአብሔርም የሚዘብት አይኑር፤ ሰውም የሚዘራውን ያጭዳል። በሥጋው የሚዘራ ሞትን ያጭዳል፤ በመንፈሱም የሚዘራ የዘለዓለም ሕይወትን ያጭዳል። በጎ ሥራ መሥራትን ቸል አንበል፥ በጊዜው እናገኘዋለንና። እንግዲህ ጊዜ ሳለን ለሁሉ መልካም ሥራ እናድርግ፤ ይልቁንም ለሃይማኖት ሰዎች። በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ እዩ። ለሰው ፊት ሊያደሉ የሚወዱ እነዚያ እንድትገዘሩ ያስገድዱአችኋል፤ ነገር ግን የክርስቶስን መስቀል እንዳትከተሉ ነው። የተገዘሩትም ቢሆኑ በሰውነታችሁ እንደምትመኩ ልትገዘሩ ይወዳሉ እንጂ ኦሪትን አልጠበቁም። እኔ ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንጂ በሌላ አልመካም፤ በእኔ ዘንድ ዓለሙ የሞተ ነው፥ እኔም በዓለሙ ዘንድ የሞትሁ ነኝ። በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ አዲስ ፍጥረት መሆን ነው እንጂ መገዘር አይጠቅምም፤ አለመገዘርም ግዳጅ አይፈጽምም። ይህን ሕግ ለሚፈጽሙ ሰዎች ሰላምና ይቅርታ ይሁን፤ የእግዚአብሔር ወገኖች በሆኑ በእስራኤል ላይም ይሁን። እንግዲህ ወዲህስ የሚያደክመኝ አይኑር፤ እኔ የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ በሥጋዬ እሸከማለሁ። ወንድሞች ሆይ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን። በሮሜ ተጽፋ በቲቶ እጅ ወደ ገላትያ ሰዎች የተላከች መልእክት ተፈጸመች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ አሜን።
ገላትያ 6:7-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አትታለሉ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ያንኑ ያጭዳል። ሥጋዊ ምኞቱን ለማርካት የሚዘራ፣ ከሥጋ ጥፋትን ያጭዳል፤ መንፈስን ለማስደሰት የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል። በጎ ነገር ከማድረግ አንታክት፤ ተስፋ ካልቈረጥን ጊዜው ሲደርስ መከሩን እናጭዳለን። ስለዚህ ዕድሉ ካለን ለሰው ሁሉ፣ በተለይም ለእምነት ቤተ ሰቦች መልካም እናድርግ። እንዴት ባሉ ታላላቅ ፊደላት በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ ተመልከቱ! ውጫዊ በሆነ ነገር ለመታየት የሚፈልጉ ሰዎች ትገረዙ ዘንድ ሊያስገድዷችሁ ይጥራሉ፤ ይህንም የሚያደርጉት ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ነው። እነርሱ በሥጋችሁ ለመመካት ሲሉ እንድትገረዙ ፈለጉ እንጂ፣ የተገረዙት ራሳቸው እንኳ ሕግን የሚጠብቁ አይደሉም። ነገር ግን ዓለም ለእኔ ከተሰቀለበት፣ እኔም ለዓለም ከተሰቀልሁበት፣ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር፣ ሌላ ትምክሕት ፈጽሞ ከእኔ ይራቅ። መገረዝም ሆነ አለመገረዝ አይጠቅምም፤ የሚጠቅመው አዲስ ፍጥረት መሆን ነው። ይህን ትእዛዝ በሚከተሉ ሁሉ፣ የእግዚአብሔር በሆነው እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን። እኔ የኢየሱስን ምልክት በሥጋዬ ተሸክሜአለሁና፣ ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ። ወንድሞች ሆይ፤ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋራ ይሁን። አሜን።
ገላትያ 6:7-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል። ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት። እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ። እንዴት ባሉ ታላላቆች ፊደላት በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ እዩ። በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሉአችሁ፥ ነገር ግን ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው። በሥጋችሁ እንዲመኩ ልትገረዙ ይወዳሉ እንጂ የተገረዙቱ ራሳቸው እንኳ ሕግን አይጠብቁም። ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። በዚህም ሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን። እኔ የኢየሱስን ማኅተም በሥጋዬ ተሸክሜአለሁና ከእንግዲህ ወዲህ አንድ ስንኳ አያድክመኝ። ወንድሞች ሆይ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን። አሜን።
ገላትያ 6:7-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ራሳችሁን አታታሉ፤ ሰው የሚያጭደው የዘራውን ስለ ሆነ በእግዚአብሔር ላይ አትቀልዱ፤ ሥጋውን ለማስደሰት የሚዘራ ከሥጋው ሞትን ያጭዳል፤ መንፈስን ለማስደሰት የሚዘራ ከመንፈስ የዘለዓለም ሕይወትን ያጭዳል። ተስፋ ካልቈረጥን ወቅቱ ሲደርስ መከር ስለምንሰበስብ መልካም ሥራን ከመሥራት አንስነፍ። ምቹ ጊዜ ካገኘን ለሰዎች ሁሉ ይልቁንም ለሚያምኑ ቤተ ሰዎች መልካም ነገርን እናድርግ። እንዴት ባሉ ታላላቅ ፊደሎች ይህን በእጄ እንደ ጻፍኩላችሁ ተመልከቱ! እንድትገረዙ የሚያስገድዱአችሁ በውጭ መልካም መስለው ለመታየት የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው። ይህን የሚያደርጉትም በክርስቶስ መስቀል ምክንያት ስደት እንዳይደርስባቸው ብለው ነው። እነርሱ በእናንተ ሥጋ ለመመካት ብለው እንድትገረዙ ይፈልጋሉ እንጂ የተገረዙትም እንኳ ራሳቸው ሕግን አይፈጽሙም። ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር በሌላ መመካት ከእኔ ይራቅ፤ በዚህም መስቀል ዓለም ከእኔ ተለይቶአል፤ እኔም ከዓለም ተለይቼአለሁ። ስለዚህ መገረዝም ሆነ አለመገረዝ ምንም አይጠቅምም፤ የሚጠቅመውስ አዲስ ፍጥረት መሆን ነው። ይህን መመሪያ ለሚከተሉ ሁሉና የእግዚአብሔር ወገኖች ለሆኑት እስራኤላውያን ሰላምና ምሕረት ይሁን። በሰውነቴ ላይ ያለው የግርፋት ምልክት የኢየሱስ አገልጋይ መሆኔን ስለሚያመለክት ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ። ወንድሞች ሆይ! የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን! አሜን።
ገላትያ 6:7-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም፤ ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳልና። ምክንያቱም ወደ ገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ ጥፋትን ያጭዳል፥ በመንፈስ የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘለዓለምን ሕይወት ያጭዳል። መልካምን ሥራ ለመሥራት አንታክት፥ ካልዛልን ወቅቱ በደረሰ ጊዜ እናጭዳለንና። ስለዚህ ጊዜ ሳለን ለሰው ሁሉ፥ በተለይም ለእምነት ቤተሰቦች መልካም እናድርግ። እንዴት ባሉ ታላላቅ ፊደላት በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ እዩ። በሥጋ መልካም ሆነው መታየት የሚፈልጉ ሁሉ እንድትገረዙ አስገደዱአችሁ፤ ይህን ያደረጉት ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው። የተገረዙት ራሳቸው እንኳ ሕግን አይጠብቁም፥ ነገር ግን በሥጋችሁ እንዲመኩ እንድትገረዙ ይፈልጋሉ። ለእኔ ግን፥ ዓለም ለእኔ እኔም ለዓለም ከተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት አይሁንብኝ። አዲስ ፍጥረት መሆን እንጂ፥ መገረዝ ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። በዚህ ሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ እና በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን። እኔ የኢየሱስን ምልክት በሰውነቴ ላይ ተሸክሜአለሁና ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ። ወንድሞች ሆይ! የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን። አሜን።