ገላትያ 3:19-25

ገላትያ 3:19-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ታዲያ፥ ሕግ የተሰጠው ለምንድን ነው? ሕግ የተጨመረው ለአብርሃም በተስፋ የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ ክፉ ሥራ ምን መሆኑን ለማመልከት ነው፤ ሕጉ በሥራ ላይ የዋለው በመላእክት ተሰጥቶ በአንድ ሰው አማካይነት ነው። ይሁን እንጂ በመካከል ሆኖ የሚያስታርቅ ሰው ለሁለት ወገን ነው እንጂ ለአንድ ወገን ብቻ አይሠራም፤ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። እንግዲህ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ይቃወማልን? ከቶ አይቃወምም! ሕይወት የሚገኝበት ሕግ ተሰጥቶ ቢሆን ኖሮ ጽድቅ በሕግ አማካይነት በተገኘ ነበር። ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የተስፋ ቃል ለሚያምኑ እንዲሰጥ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚለው ዓለም በሙሉ ለኃጢአት በመገዛት የኃጢአት እስረኛ ሆኖአል። እምነት ከመምጣቱ በፊት የሕግ እስረኞች ነበርን፤ ይህም እምነት እስከሚገለጥበት ጊዜ ድረስ በሕግ ጥበቃ ሥር ነበርን። በዚህ ዐይነት በእምነት እንድንጸድቅ ክርስቶስ እስኪመጣ ሕግ ሞግዚታችን ሆኖ ነበር። አሁን ግን እምነት ስለ መጣ በሕግ ሞግዚትነት ሥር መሆናችን ቀርቶአል።