ገላትያ 2:16-21
ገላትያ 2:16-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንጂ የኦሪትን ሥራ በመሥራት እንደማይጸድቅ እናውቃለንና፤ እኛም የኦሪትን ሥራ በመሥራት ሳይሆን በእርሱ በማመናችን እንጸድቅ ዘንድ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነናል፤ ሰው ሁሉ በኦሪት ሥራ አይጸድቅምና። በክርስቶስ ልንጸድቅ የምንሻ እኛ እንደ ኀጢአተኞች ከሆን እንግዲህ ክርስቶስ የኀጢአት አገልጋይ መሆኑ ነውን? አይደለም። ያን ያፈረስሁትን መልሼ የማንጽ ከሆነ ራሴን ሕግ አፍራሽ አደረግሁ። እኔስ ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኜ በሁለተኛው ሕግ እኖር ዘንድ ከቀደመው ሕግ ተለየሁ። ከክርስቶስ ጋርም ተሰቀልሁ፤ ሕይወቴም አለቀች፤ ነገር ግን በክርስቶስ ሕይወት አለሁ፤ ዛሬም በሥጋዬ የምኖረውን ኑሮ የወደደኝን ስለ እኔም ራሱን አሳልፎ የሰጠውን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመን እኖራለሁ። የእግዚአብሔርንም ጸጋ አልክድም፤ የኦሪትን ሥራ በመሥራት የሚጸድቁ ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ።
ገላትያ 2:16-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንጂ፣ ሕግን በመጠበቅ እንደማይጸድቅ እናውቃለን። ስለዚህ ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን፣ በክርስቶስ በማመን እንጸድቅ ዘንድ እኛም ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል፤ ሕግን በመጠበቅ ማንም አይጸድቅምና። “በክርስቶስ ለመጽደቅ ስንፈልግ፣ እኛ ራሳችን ኀጢአተኞች መሆናችን ግልጽ ነው፤ ታዲያ ክርስቶስ ኀጢአት እንዲስፋፋ ያደርጋልን? ከቶ አይሆንም! ያፈረስሁትን መልሼ የምገነባ ከሆነማ፣ ሕግ ተላላፊ መሆኔን አረጋግጣለሁ። “ለእግዚአብሔር እኖር ዘንድ በሕግ በኩል ለሕግ ሞቻለሁና። ከክርስቶስ ጋራ ተሰቅያለሁ፤ ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው። የእግዚአብሔርን ጸጋ አላቃልልም፤ ጽድቅ በሕግ በኩል የሚገኝ ከሆነማ፣ ክርስቶስ እንዲያው በከንቱ ሞተ ማለት ነዋ!”
ገላትያ 2:16-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል። ነገር ግን በክርስቶስ ልንጸድቅ የምንፈልግ ስንሆን ራሳችን ደግሞ ኃጢአተኞች ሆነን ከተገኘን፥ እንግዲያስ ክርስቶስ የኃጢአት አገልጋይ ነዋ? አይደለም። ያፈረስሁትን ይህን እንደ ገና የማንጽ ከሆንሁ ራሴ ሕግ ተላላፊ እንድሆን አስረዳለሁና። እኔ ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኜ እኖር ዘንድ በሕግ በኩል ለሕግ ሞቼ ነበርና። ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም፤ ጽድቅስ በሕግ በኩል ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ።
ገላትያ 2:16-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ነገር ግን ሰው የሚጸድቀው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንጂ ሕግን በመፈጸም እንዳልሆነ እናውቃለን፤ እኛም ሕግን በመፈጸም ሳይሆን በክርስቶስ በማመን እንድንጸድቅ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነናል፤ ማንም ሰው የኦሪትን ሕግ በመፈጸም አይጸድቅም። በክርስቶስ በማመን ለመጽደቅ ስንፈልግ እኛ ራሳችን ኃጢአተኞች ሆነን ብንገኝ ታዲያ፥ ኃጢአት እንድንሠራ የሚያደርገን ክርስቶስ ነው ማለት ነውን? ከቶ አይደለም! እኔ ራሴ ያፈረስኩትን የሕግ ሥርዓት መልሼ የምሠራው ከሆንኩ እኔው ራሴ ሕግ አፍራሽ መሆኔን አረጋግጣለሁ ማለት ነው። ለእግዚአብሔር እኖር ዘንድ በሕግ አማካይነት በሞት የመለየትን ያኽል ከሕግ ተለይቼአለሁ። እኔ ከክርስቶስ ጋር እንደ ተሰቀልኩ ያኽል ስለምቈጥር ከእንግዲህ ወዲህ ክርስቶስ በእኔ ውስጥ ይኖራል እንጂ እኔ ለራሴ ሕይወት የምኖር አይደለሁም፤ አሁንም በሥጋዊ አካሌ የምኖረው በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ በማመን በተገኘው ሕይወት ነው። የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ አላስቀርም፤ ሰው የሚጸድቀው ሕግን በመፈጸም ከሆነ ክርስቶስ የሞተው በከንቱ ነው ማለት ነው።
ገላትያ 2:16-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሆኖም ሰው የሚጸድቀው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንጂ በሕግ ሥራ እንዳልሆነ አውቀን፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ በማመን እንድንጸድቅ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል። ሥጋ ሁሉ በሕግ ሥራ አይጸድቅም። ነገር ግን በክርስቶስ ልንጸድቅ የምንፈልግ፥ እኛ ራሳችን ደግሞ ኃጢአተኞች ሆነን ብንገኝ፥ ታዲያ ክርስቶስ የኃጢአት አገልጋይ ነውን? በጭራሽ አይደለም። ይህን ያፈረስኩትን እንደገና የማንጽ ከሆንሁ፥ እኔ ራሴ ሕግ ተላላፊ ነኝ። ለእግዚአብሔር እንድኖር በሕግ በኩል ለሕግ ሞቼአለሁ፤ ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ። ክርስቶስ በእኔ ይኖራል እንጂ ከእንግዲህ ወዲያ እኔ አልኖርም፤ አሁን በሥጋ የምኖረው በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ በማመን የምኖረው ነው። የእግዚአብሔርን ጸጋ አልናቅሁም፤ ጽድቅ በሕግ በኩል የሚገኝ ከሆነ እንግዲያውስ ክርስቶስ የሞተው በከንቱ ነው ማለት ነዋ!