ገላትያ 1:6-10
ገላትያ 1:6-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በጸጋዉ የጠራችሁን ክርስቶስን ከማመን ወደ ልዩ ወንጌል እንዴት ፈጥነው እንዳስወጧችሁ አደንቃለሁ። እርሱ ግን ሌላ አይደለም፤ የሚያውኳችሁ ከክርስቶስም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አሉ እንጂ። እናንተ ግን የእኛን ፍለጋ ተከተሉ፤ እናንተስ እኛም ብንሆን ወይም መልአክ ከሰማይ ወርዶ እኛ ካስተማርናችሁ ወንጌል ሌላ ቢሰብክላችሁ ውጉዝ ይሁን። አስቀድሜ እንደ አልሁ አሁንም ደግሞ እላለሁ፦ ካስተማርናችሁ ሌላ ትምህርት ያስተማራችሁ ቢኖር ውጉዝ ይሁን። አሁንስ ለእግዚአብሔር ያይደለ ለሰው ብዬ አስተምራለሁን? ወይስ ሰውን ደስ አሰኛለሁን? ሰውን ደስ ላሰኝ ብወድስ የክርስቶስ ባሪያ አይደለሁም።
ገላትያ 1:6-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በክርስቶስ ጸጋ የጠራችሁን እርሱን ትታችሁ፣ ወደ ተለየ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ መዞራችሁ ደንቆኛል፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ሌላ ወንጌል የለም። የሚያደነጋግሯችሁና የክርስቶስን ወንጌል ለማጣመም ጥረት የሚያደርጉ አንዳንድ ሰዎች አሉ። ነገር ግን እኛም ብንሆን ወይም የሰማይ መልአክ፣ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ እርሱ ለዘላለም የተረገመ ይሁን! ቀደም ብለን እንዳልነው፣ አሁንም ደግሜ እላለሁ፤ ማንም ከተቀበላችሁት ሌላ የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን! አሁን እኔ ተቀባይነት ለማግኘት የምሻው በሰዎች ዘንድ ነው ወይስ በእግዚአብሔር ዘንድ? ወይስ ሰዎችን ደስ ለማሠኘት እየተጣጣርሁ ነው? ሰዎችን ደስ ለማሠኘት የምጥር ብሆን ኖሮ፣ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁ ነበር።
ገላትያ 1:6-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤ እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ። ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን። ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም።
ገላትያ 1:6-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በክርስቶስ ጸጋ ከጠራችሁ አምላክ እንዲህ ፈጥናችሁ መለየታችሁና ወደ ሌላ ወንጌል ማዘንበላችሁ ያስደንቀኛል። ይህንንም ያልኩት ግራ የሚያጋቡአችሁና የክርስቶስንም ወንጌል ለማጣመም የሚፈልጉ አንዳንድ ሰዎች ስላሉ ነው እንጂ ወንጌልማ በመሠረቱ አንድ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ እኛም ብንሆን፥ ወይም የሰማይ መልአክ እንኳ ቢሆን፥ እኛ ከሰበክንላችሁ የተለየ ሌላ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን! ከዚህ በፊት እንዳልኩት አሁንም ደግሜ እላለሁ፤ እናንተ ከተቀበላችሁት የተለየ ሌላ ወንጌል ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን! ታዲያ፥ እኔ የምፈልገው ሰው እንዲያመሰግነኝ ነውን? ወይስ እግዚአብሔር እንዲያመሰግነኝ? ወይስ ሰውን ደስ ለማሰኘት የምፈልግ መስሎአችሁ ይሆን? ሰዎችን ለማስደሰት የምፈልግ ብሆን ኖሮ የክርስቶስ አገልጋይ ባልሆንኩም ነበር።
ገላትያ 1:6-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ሌላ ወንጌል እንዴት ፈጥናችሁ እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ። ሌላ ወንጌል ያለ አይምሰላችሁ፤ የሚያናውጡአችሁና የክርስቶስንም ወንጌል ለማጣመም የሚፈልጉ አንዳንዶች አሉ። ነገር ግን እኛም ብንሆን ወይም ከሰማይ የመጣ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። ከዚህ በፊት እንዳልነው አሁንም ደግሜ እላለሁ፤ ማንም ከተቀበላችሁት የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን። አሁን ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሳምናለሁን? ወይስ ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? እስከ አሁን ሰውን ደስ የማሰኝ ብሆን ኖሮ የክርስቶስ ባርያ አልሆንም ነበር።