ገላትያ 1:1-9

ገላትያ 1:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በጌ​ታ​ችን በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶ​ስና ከሙ​ታን ለይቶ በአ​ስ​ነ​ሣው በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አብ ነው እንጂ ከሰ​ዎች ወይም በሰው ሐዋ​ርያ ካል​ሆነ ከጳ​ው​ሎስ፥ አብ​ረ​ውኝ ካሉ ከወ​ን​ድ​ሞ​ቻ​ች​ንም፥ በገ​ላ​ትያ ላሉ አብ​ያተ ክር​ስ​ቲ​ያን፤ ከአ​ባ​ታ​ችን ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር፥ ከጌ​ታ​ችን ከኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶ​ስም ሰላ​ምና ጸጋ ለእ​ና​ንተ ይሁን። በክፉ ከሚ​ቃ​ወም ከዚህ ዓለም ያድ​ነን ዘንድ በአ​ባ​ታ​ችን በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፈቃድ ስለ ኀጢ​አ​ታ​ችን ራሱን አሳ​ልፎ ሰጠ። ለእ​ርሱ ክብር ይሁን፤ ከዘ​ለ​ዓ​ለም እስከ ዘለ​ዓ​ለም አሜን። በጸ​ጋዉ የጠ​ራ​ች​ሁን ክር​ስ​ቶ​ስን ከማ​መን ወደ ልዩ ወን​ጌል እን​ዴት ፈጥ​ነው እን​ዳ​ስ​ወ​ጧ​ችሁ አደ​ን​ቃ​ለሁ። እርሱ ግን ሌላ አይ​ደ​ለም፤ የሚ​ያ​ው​ኳ​ችሁ ከክ​ር​ስ​ቶ​ስም ወን​ጌል ሊያ​ጣ​ምሙ የሚ​ወዱ አሉ እንጂ። እና​ንተ ግን የእ​ኛን ፍለጋ ተከ​ተሉ፤ እና​ን​ተስ እኛም ብን​ሆን ወይም መል​አክ ከሰ​ማይ ወርዶ እኛ ካስ​ተ​ማ​ር​ና​ችሁ ወን​ጌል ሌላ ቢሰ​ብ​ክ​ላ​ችሁ ውጉዝ ይሁን። አስ​ቀ​ድሜ እንደ አልሁ አሁ​ንም ደግሞ እላ​ለሁ፦ ካስ​ተ​ማ​ር​ና​ችሁ ሌላ ትም​ህ​ርት ያስ​ተ​ማ​ራ​ችሁ ቢኖር ውጉዝ ይሁን።

ገላትያ 1:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከሰዎች ወይም በሰው ከተላከው ሳይሆን፣ በኢየሱስ ክርስቶስና ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፤ ዐብረውኝም ካሉት ወንድሞች ሁሉ፤ በገላትያ ላሉት አብያተ ክርስቲያናት፦ ከአባታችን ከእግዚአብሔር፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ፣ ከዚህ ክፉ ዓለም ያድነን ዘንድ ስለ ኀጢአታችን ራሱን ሰጠ፤ ከዘላለም እስከ ዘላለም ለርሱ ክብር ይሁን። አሜን። በክርስቶስ ጸጋ የጠራችሁን እርሱን ትታችሁ፣ ወደ ተለየ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ መዞራችሁ ደንቆኛል፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ሌላ ወንጌል የለም። የሚያደነጋግሯችሁና የክርስቶስን ወንጌል ለማጣመም ጥረት የሚያደርጉ አንዳንድ ሰዎች አሉ። ነገር ግን እኛም ብንሆን ወይም የሰማይ መልአክ፣ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ እርሱ ለዘላለም የተረገመ ይሁን! ቀደም ብለን እንዳልነው፣ አሁንም ደግሜ እላለሁ፤ ማንም ከተቀበላችሁት ሌላ የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን!

ገላትያ 1:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሁሉ፥ ወደ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት፦ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ። ለአብ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን። በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤ እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ። ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።

ገላትያ 1:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በሰዎች ወይም በሰው አማካይነት ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስና እርሱንም ከሞት ባስነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ ሆኜ ከተላክሁ ከእኔ ከጳውሎስ፥ ከእኔም ጋር ካሉት ወንድሞች ሁሉ ለገላትያ አብያተ ክርስቲያን የተላከ። ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ከዚህ ከክፉ ዘመን ያድነን ዘንድ በአምላካችንና በአባታችን ፈቃድ ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ። ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን! አሜን። በክርስቶስ ጸጋ ከጠራችሁ አምላክ እንዲህ ፈጥናችሁ መለየታችሁና ወደ ሌላ ወንጌል ማዘንበላችሁ ያስደንቀኛል። ይህንንም ያልኩት ግራ የሚያጋቡአችሁና የክርስቶስንም ወንጌል ለማጣመም የሚፈልጉ አንዳንድ ሰዎች ስላሉ ነው እንጂ ወንጌልማ በመሠረቱ አንድ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ እኛም ብንሆን፥ ወይም የሰማይ መልአክ እንኳ ቢሆን፥ እኛ ከሰበክንላችሁ የተለየ ሌላ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን! ከዚህ በፊት እንዳልኩት አሁንም ደግሜ እላለሁ፤ እናንተ ከተቀበላችሁት የተለየ ሌላ ወንጌል ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን!

ገላትያ 1:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከሰዎች ወይም በሰው አማካኝነት ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስና እርሱንም ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሁሉ፥ ወደ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት፤ ከእግዚአብሔር አብና ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። እንደ አምላካችንና አባታችን ፈቃድ፥ ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ሊያድነን፥ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ። ለእርሱ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብር ይሁን፤ አሜን። በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ሌላ ወንጌል እንዴት ፈጥናችሁ እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ። ሌላ ወንጌል ያለ አይምሰላችሁ፤ የሚያናውጡአችሁና የክርስቶስንም ወንጌል ለማጣመም የሚፈልጉ አንዳንዶች አሉ። ነገር ግን እኛም ብንሆን ወይም ከሰማይ የመጣ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። ከዚህ በፊት እንዳልነው አሁንም ደግሜ እላለሁ፤ ማንም ከተቀበላችሁት የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።