ሕዝቅኤል 9:1-3
ሕዝቅኤል 9:1-3 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እርሱም፥ “እያንዳንዳቸው የሚያጠፉባት መሣሪያን በእጃቸው ይዘው ከተማዪቱን የሚቀሥፉ ይቅረቡ” ብሎ በታላቅ ድምፅ በጆሮዬ ጮኸ። እነሆም እያንዳንዳቸው ገጀሞ መሣሪያ በእጃቸው ይዘው ስድስት ሰዎች ወደ ሰሜን ከሚመለከተው ከላይኛው በር መንገድ መጡ፤ በመካከላቸውም የበፍታ ልብስ የለበሰና የሰንፔር መታጠቂያ በወገቡ የታጠቀ አንድ ሰው ነበረ። እነርሱም ገብተው በናሱ መሠዊያ አጠገብ ቆሙ። የእስራኤልም አምላክ ክብር በበላዩ ከነበረበት ኪሩብ ተነሥቶ ወደ ቤቱ መድረክ ሄዶ ነበር፤ በፍታም የለበሰውን፥ የሰንፔር መታጠቂያም በወገቡ የታጠቀውን ሰው ጠራ።
ሕዝቅኤል 9:1-3 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም እኔ እየሰማሁ ከፍ ባለ ድምፅ፣ “እያንዳንዳቸው በእጃቸው የጦር መሣሪያ የያዙ፣ ከተማዪቱን የሚቀጡ ወደዚህ ይምጡ” ብሎ ከፍ ባለ ድምፅ ጮኸ። እነሆም፤ አጥፊ የሆነ የጦር መሣሪያ በእጃቸው የያዙ ስድስት ሰዎች በሰሜን አቅጣጫ ካለው ከላይኛው በር መጡ፤ ከእነርሱም ጋራ ቀጭን በፍታ የለበሰ፣ በጐኑም የጽሕፈት ዕቃ ማኅደር ያነገበ ሰው ነበር። እነርሱም ገብተው በናሱ መሠዊያ አጠገብ ቆሙ። በዚህ ጊዜ የእስራኤል አምላክ ክብር ከነበረበት ከኪሩብ በላይ ተነሥቶ ወደ ቤተ መቅደሱ መድረክ ሄደ። እግዚአብሔርም በፍታ የለበሰውን በጐኑም የጽሕፈት ዕቃ ማኅደር ያነገበውን ሰው ጠራ፤
ሕዝቅኤል 9:1-3 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እርሱም፦ እያንዳንዳቸው የሚያጠፋ መሣሪያን በእጃቸው ይዘው ከተማይቱን የሚቀሥፉ ይቅረቡ ብሎ በታላቅ ድምፅ በጆሮዬ ጮኸ። እነሆም፥ እያንዳንዳቸው አጥፊውን መሣሪያ በእጃቸው ይዘው ስድስት ሰዎች ወደ ሰሜን ከሚመለከተው ከላይኛው በር መንገድ መጡ፥ በመካከላቸውም የበፍታ ልብስ የለበሰ የጸሐፊም ቀለም ቀንድ በወገቡ የያዘ አንድ ሰው ነበረ። እነርሱም ገብተው በናሱ መሠዊያ አጠገብ ቆሙ። የእስራኤልም አምላክ ክብር በበላዩ ከነበረበት ኪሩብ ተነሥቶ ወደ ቤቱ መድረክ ሄዶ ነበር፥ በፍታ የለበሰውን የጸሐፊውንም ቀለም ቀንድ በወገቡ የያዘውን ሰው ጠራ።
ሕዝቅኤል 9:1-3 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ድምፁን ከፍ አድርጎ “ከተማይቱን የምትቀጡ እናንተ ወደዚህ ቅረቡ፤ ለማጥፋት የተዘጋጀ የጦር መሣሪያዎቻችሁንም ይዛችሁ ኑ!” ብሎ ሲናገር ሰማሁ። ስድስት ሰዎችም የመግደያ መሣሪያዎቻቸውን ይዘው ወደ ሰሜን ከሚመለከተው ከላይኛው በር መጡ፤ ከእነርሱም መካከል በፍታ የለበሰና የጽሕፈት ዕቃ ማኅደር በጐኑ የያዘ አንድ ሰው ነበር። ስድስቱም ሰዎች ገብተው በነሐሱ መሠዊያ አጠገብ ቆሙ። ከዚህ በኋላ የእስራኤልን አምላክ ክብር የሚገልጥ ነጸብራቅ ቀድሞ ካረፈበት ከኪሩብ ላይ ተነሥቶ ወደ ቤተ መቅደሱ መግቢያ በር ሄደ፤ እግዚአብሔርም በፍታ የለበሰውንና የጽሕፈት ዕቃ ማኅደር የያዘውን ሰው፥ ጠራው፤
ሕዝቅኤል 9:1-3 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በታላቅ ድምፅ በጆሮዬ ጮኸ፥ እንዲህም አለ፦ እያንዳንዳቸው በእጃቸው የጦር ይያዙ፤ ከተማይቱን የሚቀጡ በዚህ ይምጡ። እነሆ ስድስት ሰዎች ወደ ሰሜን ከሚመለከተው ከላይኛው በር መንገድ መጡ፥ እያንዳንዱም አጥፊውን መሣሪያ በእጁ ይዞ ነበር፥ በመካከላቸውም የበፍታ ልብስ የለበሰ፥ የጸሐፊ የቀለም ቀንድ በወገቡ የያዘ አንድ ሰው ነበረ። እነርሱም ገብተው በናሱ መሠዊያ አጠገብ ቆሙ። የእስራኤልም አምላክ ክብር በላዩ ላይ አርፎ ከነበረበት ኪሩብ ተነሥቶ ወደ ቤቱ መግቢያ ሄዶ ነበር፥ በፍታ የለበሰውን በወገቡም የጸሐፊ ቀለም ቀንድ የያዘውን ሰው ጠራ።