ሕዝቅኤል 48:1-35
ሕዝቅኤል 48:1-35 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“የነገዶችም ስም ይህ ነው። በሔትሎን መንገድ አጠገብ ወደ ሐማት መግቢያ፥ በደማስቆም ድንበር በአለው በሐጸርዔናን በሐማትም አጠገብ በሰሜን በኩል ይጀምራል። ድንበራቸውም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ይሆናል። ለዳን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከዳንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለአሴር አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከአሴርም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለንፍታሌም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከንፍታሌም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለምናሴ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከምናሴም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለኤፍሬም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከኤፍሬምም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለሮቤል አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከሮቤልም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለይሁዳ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። “ከይሁዳም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለመባ የተለየ ክፍል ይሆናል፤ ወርዱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል፤ ርዝመቱም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ከዕጣ ክፍሎች እንደ አንዱ ይሆናል፤ ቤተ መቅደሱም በመካከሉ ይሆናል። ለእግዚአብሔር የምትለዩት መባ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ወርዱም ዐሥር ሺህ ክንድ ይሆናል። የመቅደሱም ቀዳምያት ለካህናቱ ይሆናል፤ በሰሜን በኩል ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ፥ በምዕራብም በኩል ወርዱ ዐሥር ሺህ፥ በምሥራቅም በኩል ወርዱ ዐሥር ሺህ፥ በደቡብም በኩል ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል። የእግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ በመካከሉ ይሆናል። የእስራኤልም ልጆች በሳቱ ጊዜ፥ ሌዋውያን እንደ ሳቱ ላልሳቱት፥ ሥርዐቴን ለጠበቁት፥ ከሳዶቅ ልጆች ወገን ለተቀደሱት ካህናት ይሆናል። ከምድርም መባ የተለየ ሌላ መባ ይሆንላቸዋል፤ ከተቀደሱትም ይልቅ የተቀደሰ ይሆናል፤ በሌዋውያን ድንበር አጠገብ ይሆናል። በካህናቱም ድንበር አቅራቢያ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ፥ ወርዱም ዐሥር ሺህ የሆነ ዕጣ ለሌዋውያን ይሆናል፤ ርዝመቱ ሁሉ ሃያ አምስት ሺህ፥ ወርዱም ሃያ ሺህ ክንድ ይሆናል። ለእግዚአብሔርም የተቀደሰ ነውና ከእርሱ ምንም አይሸጡም፤ አይለውጡምም፤ የምድሩም ቀዳምያት አይፋለስም። በሃያ አምስቱ ሺህ አንጻር አምስት ሺህ ወርድ ያለው የቀረ ቅዱስ ያይደለ ስፍራ ለከተማዪቱ ለጋራ ጉዳይዋ፥ ለመኖሪያ፥ ለማሰማርያም ይሆናል፤ ከተማዪቱም በመካከሉ ትሆናለች። ልክዋም ይህ ነው፤ በሰሜን በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በደቡብም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በምሥራቅም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በምዕራብም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ይሆናል። ለከተማዪቱም ማሰማርያ ይኖራታል፤ በሰሜን በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በደቡብም በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በምሥራቅም በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በምዕራብም በኩል ሁለት መቶ አምሳ ክንድ ይሆናል። “በተቀደሰው መባ አንጻር የተረፈው ርዝመቱ ወደ ምሥራቅ ዐሥር ሺህ፥ ወደ ምዕራብም ዐሥር ሺህ ክንድ ይሆናል። በተቀደሰው መባ አንጻር ይሆናል። ፍሬውም ከተማዪቱን ለሚያገለግሉ መብል ይሆናል። ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከተማዪቱን የሚያገለግሉ ያርሱታል። መባው ሁሉ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ፥ ወርዱም ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል፤ የተቀደሰውን መባ ከከተማዪቱ ይዞታ ጋር አራት ማዕዘን አድርጋችሁ ትሰጣላችሁ። “በተቀደሰው መባና በከተማዪቱ ይዞታ፥ በዚህና በዚያ ወገን የቀረው ለአለቃው ይሆናል፤ በመባው በሃያ አምስት ሺህ ፊት እስከ ምሥራቁ ድንበር፥ በምዕራብም በኩል በሃያ አምስት ሺህ ፊት እስከ ምዕራቡ ድንበር፥ እንደ ዕጣ ክፍል ሁሉ መጠን፥ ለአለቃው ይሆናል፤ የተቀደሰውም መባና ቤተ መቅደሱ በመካከሉ ይሆናል። የሌዋውያን ርስት፥ የከተማዪቱም ይዞታ ለአለቃው በሆነው መካከል ይሆናል፤ በይሁዳ ድንበርና በብንያም ድንበር መካከል የአለቃው ዕጣ ክፍል ይሆናል። “ለቀሩትም ነገዶች እንዲህ ይሆናል፤ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለብንያም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከብንያምም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለስምዖን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከስምዖንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለይሳኮር አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከይሳኮርም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለዛብሎን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከዛብሎንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለጋድ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከጋድም ድንበር ቀጥሎ በደቡብ በኩል ድንበሩ ከታማር ጀምሮ እስከ ሜሪባ ቃዴስ ውኃ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሆናል። ርስት አድርጋችሁ ለእስራኤል ነገዶች በዕጣ የምታካፍሉአት ምድር ይህች ናት፤ የእያንዳንዱም ዕጣ እንደዚህ ነው፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። “የከተማዪቱም መውጫዎች እነዚህ ናቸው። በሰሜን ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ነው። የከተማዪቱ በሮች እንደ እስራኤል ነገዶች ስም ይሆናሉ፤ በሰሜን በኩል አንዱ የሮቤል በር፤ አንዱም የይሁዳ በር፥ አንዱም የሌዊ በር ሦስት በሮች ይሆናሉ። በምሥራቁም ወገን አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፤ አንዱ የዮሴፍ በር፥ አንዱም የብንያም በር፥ አንዱም የዳን በር ነው። በደቡቡም ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፤ አንዱ የስምዖን በር፥ አንዱም የይሳኮር በር፥ አንዱም የዛብሎን በር ነው። በምዕራቡም ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፤ አንዱ የጋድ በር፥ አንዱም የአሴር በር፥ አንዱም የንፍታሌም በር ነው። ዙሪያዋም ዐሥራ ስምንት ሺህ ክንድ ይሆናል፥ ከዚያም ቀን ጀምሮ የከተማዪቱ ስም፦ ‘እግዚአብሔር በዚያ አለ’ ተብሎ ይጠራል።”
ሕዝቅኤል 48:1-35 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ስማቸው የተዘረዘረው ነገዶች እነዚህ ናቸው፤ “በሰሜኑ ድንበር የዳን ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የሔትሎንን መንገድ ተከትሎ እስከ ሐማት መተላለፊያ ይደርሳል። ሐጻርዔናንና ከሐማት ቀጥሎ ያለው የደማስቆ ሰሜናዊ ድንበር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ላለው ወሰኑ አንድ ክፍል ይሆናል። የአሴር ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የዳንን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል። የንፍታሌም ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የአሴርን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል። የምናሴ ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የንፍታሌምን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል። የኤፍሬም ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የምናሴን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል። የሮቤል ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የኤፍሬምን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል። የይሁዳ ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የሮቤልን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል። “ይሁዳን ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የሚያዋስነው ምድር ለመባ የሚቀርብ ድርሻ ይሆናል፤ ስፋቱም ሃያ ዐምስት ሺሕ ክንድ ነው፤ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያለውም ርዝመቱ፣ ከነገዶቹ ድርሻ እንደ አንዱ ሆኖ፣ መቅደሱ በመካከሉ ይሆናል። “ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት የዚህ መባ ርዝመት ሃያ ዐምስት ሺሕ ክንድ ሲሆን፣ ስፋቱ ዐሥር ሺሕ ክንድ ይሆናል። ይህ ለካህናቱ የተቀደሰ ድርሻ ይሆናል፤ በሰሜን በኩል ርዝመቱ ሃያ ዐምስት ሺሕ ክንድ፣ በምዕራብ በኩል ወርዱ ዐሥር ሺሕ ክንድ በምሥራቅ በኩል ወርዱ ዐሥር ሺሕ ክንድ ሲሆን፣ በደቡብ በኩል ርዝመቱ ሃያ ዐምስት ሺሕ ክንድ ይሆናል፤ የእግዚአብሔርም መቅደስ በመካከሉ ይቆማል። ይህም እስራኤላውያን በሳቱ ጊዜ፣ እንደ ሳቱት ሌዋውያን ሳይስቱ ለቀሩት፣ በታማኝነት ላገለገሉኝ ለተቀደሱት ካህናት ለሳዶቃውያን ይሆናል። የሌዋውያንን ምድር ከሚያዋስነው፣ ከምድሪቱ ቅዱስ ድርሻ እጅግ የተቀደሰው ድርሻ ለእነርሱ ልዩ ስጦታ ይሆናል። “ከካህናቱም ምድር ጐን ለጐን ሌዋውያኑ ሃያ ዐምስት ሺሕ ክንድ ርዝመትና ዐሥር ሺሕ ክንድ ወርድ ያለው ይዞታ ይኖራቸዋል፤ ጠቅላላ ርዝመቱ ሃያ ዐምስት ሺሕ ክንድ፣ ወርዱም ዐሥር ሺሕ ክንድ ይሆናል። ከዚህ ላይ መሸጥ ወይም መለወጥ የለባቸውም። ይህ ከምድሪቱ ሁሉ ምርጥ ስለ ሆነ፣ ወደ ሌላ እጅ አይተላለፍም፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነውና። “ዐምስት ሺሕ ክንድ ወርድና ሃያ ዐምስት ሺሕ ክንድ ርዝመት ያለው የቀረው ቦታ ለከተማዪቱ የጋራ ጥቅም፣ ለቤት ሥራና ለከብት ማሰማሪያ ይውላል፤ ከተማዪቱም በመካከሉ ትሆናለች፤ የከተማዪቱም መጠን በሰሜን አራት ሺሕ ዐምስት መቶ ክንድ፣ በደቡብ አራት ሺሕ ዐምስት መቶ ክንድ፣ በምሥራቅ አራት ሺሕ ዐምስት መቶ ክንድ፣ የምዕራቡም እንዲሁ አራት ሺሕ ዐምስት መቶ ክንድ ይሆናል። የከተማዪቱ ከብት ማሰማሪያ ቦታ፣ በሰሜን ሁለት መቶ ዐምሳ ክንድ፣ በደቡብ ሁለት መቶ ዐምሳ ክንድ፣ በምሥራቅ ሁለት መቶ ዐምሳ ክንድ፣ በምዕራብም ሁለት መቶ ዐምሳ ክንድ ይሆናል። ከዚህ የሚቀረው፣ የተቀደሰውን ክፍል የሚያዋስነውና በተጓዳኝ ያለው ቦታ በምሥራቅ ዐሥር ሺሕ ክንድ፣ በምዕራብ ዐሥር ሺሕ ክንድ ይሆናል። ምርቱም ለከተማዪቱ ሠራተኞች ምግብ ይሆናል። ምድሪቱን የሚያርሱ የከተማዪቱ ሠራተኞች ከሁሉም የእስራኤል ነገዶች ይመጣሉ። አጠቃላይ ይዞታው በአራቱም ማእዘን እኩል ሲሆን፣ እያንዳንዱ ማእዘን ሃያ ዐምስት ሺሕ ክንድ ነው፤ ከከተማዪቱ ድርሻ ጋራ የተቀደሰውን ክፍል ልዩ መባ በማድረግ ታስቀምጣላችሁ። “በተቀደሰው ድርሻና በከተማዪቱ ቦታ ግራና ቀኝ ያለው ቀሪ ቦታ፣ ለገዢው ይሆናል፤ ይህም ሃያ ዐምስት ሺሕ ክንድ ከሆነው ከተቀደሰው ቦታ አንሥቶ በምሥራቅ በኩል እስከ ምሥራቁ ወሰን ይዘልቃል፤ በምዕራቡም በኩል እንዲሁ ሃያ ዐምስት ሺሕ ክንድ ከሆነው ይዞታ አንሥቶ እስከ ምዕራቡ ወሰን ይዘልቃል። የየነገዱ ድርሻ ከሆነውም መሬት ጐን ለጐን የሚሄዱት ቦታዎች የገዢው ይሆናሉ። የተቀደሰው ቦታና መቅደሱ በመካከላቸው ይሆናሉ። ስለዚህ የሌዋውያኑ ይዞታና የከተማዪቱ ይዞታ ለገዢው በተሰጠው ቦታ መካከል ይሆናል፤ የገዢው ቦታም በይሁዳ ድንበርና በብንያም ድንበር መካከል ይሆናል። “የቀሩት ነገዶች ድርሻ እንደሚከተለው ይሆናል፤ “የብንያም ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ይዘልቃል። የስምዖን ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የስምዖንን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል። የይሳኮር ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የስምዖንን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል። የዛብሎን ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የይሳኮርን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል። የጋድ ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የዛብሎንን ግዛት ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል። የጋድ ደቡባዊ ወሰን ከታማር ደቡብ እስከ መሪባ ቃዴስ ውሆች ይደርሳል፤ የግብጽን ደረቅ ወንዝ ይዞ እስከ ታላቁ ባሕር ይዘልቃል። “ለእስራኤል ነገዶች ርስት አድርጋችሁ የምታከፋፍሏት ምድር ይህች ናት፤ ድርሻዎቻቸውም እነዚህ ናቸው” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። “የከተማዪቱ መውጫ በሮች እነዚህ ናቸው፤ “ከሰሜን በኩል አራት ሺሕ ዐምስት መቶ ክንድ ርዝመት ካለው በር አንሥቶ፣ የከተማዪቱ በሮች በእስራኤል ነገዶች ስም ይጠራሉ፤ በሰሜን በኩል ያሉት ሦስቱ በሮች የሮቤል ነገድ በር፣ የይሁዳ ነገድ በርና የሌዊ ነገድ በር ይሆናሉ። በምሥራቅ በኩል አራት ሺሕ ዐምስት መቶ ክንድ ርዝመት ባለው በር ሦስት በሮች ይኖራሉ፤ እነዚህም የዮሴፍ በር፣ የብንያም በርና የዳን በር ናቸው። በደቡብ በኩል አራት ሺሕ ዐምስት መቶ ክንድ ርዝመት ባለው በር ሦስት በሮች አሉ፤ እነዚህም የስምዖን በር፣ የይሳኮር በርና የዛብሎን በር ናቸው። በምዕራብ በኩል አራት ሺሕ ዐምስት መቶ ክንድ ርዝመት ባለው በር ሦስት በሮች ይኖራሉ፤ እነዚህም የጋድ በር፣ የአሴር በርና የንፍታሌም በር ናቸው። “የከተማዪቱም ዙሪያ ዐሥራ ስምንት ሺሕ ክንድ ይሆናል፤
ሕዝቅኤል 48:1-35 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የነገዶችም ስም ይህ ነው። በሔትሎን መንገድ አጠገብ ወደ ሐማት መግቢያ በደማስቆም ድንበር ባለው በሐጸርዔናን በሐማትም አጠገብ በሰሜን በኩል ካለው ከሰሜን ድንበር ይጀምራል። ወርዳቸውም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ይሆናል። ለዳን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከዳን ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለአሴር አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከአሴርም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለንፍታሌም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከንፍታሌም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለምናሴ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከምናሴም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለኤፍሬም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከኤፍሬምም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለሮቤል አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከሮቤልም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለይሁዳ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከይሁዳም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለመባ የሆነ የዕጣ ክፍል ይሆናል፥ ወርዱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል ርዝመቱም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ከዕጣ ክፍሎች እንደ አንዱ ይሆናል፥ መቅደሱም በመካከሉ ይሆናል። ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት መባ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ወርዱም ሃያ ሺህ ክንድ ይሆናል። ለእነዚህም ለካህናቱ የተቀደሰ መባ ይሆናል፥ በሰሜን በኩል ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ፥ በምዕራብም በኩል ወርዱ አሥር ሺህ፥ በምሥራቅም በኩል ወርዱ አሥር ሺህ፥ በደቡብም በኩል ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል። የእግዚአብሔርም መቅደስ በመካከሉ ይሆናል። የእስራኤልም ልጆች በሳቱ ጊዜ፥ ሌዋውያን እንደ ሳቱ ላልሳቱት ሥርዓቴን ለጠበቁት ከሳዶቅ ልጆች ወገን ለተቀደሱት ካህናት ይሆናል። ከምድርም መባ የተለየ መባ ይሆንላቸዋል፥ ከሁሉም ይልቅ የተቀደሰ ይሆናል፥ በሌዋውያን ድንበር አጠገብ ይሆናል። በካህናቱም ድንበር አንጻር ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም አሥር ሺህ የሆነ ዕጣ ለሌዋውያን ይሆናል፥ ርዝመቱ ሁሉ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም ሀያ ሺህ ክንድ ይሆናል። ለእግዚአብሔርም የተቀደሰ ነውና ከእርሱ ምንም አይሸጡም አይለውጡምም፥ የምድሩም በኵራት አይፋለስም። በሀያ አምስቱም ሺህ አንጻር አምስት ሺህ ወርድ ያለው የቀረ ስፍራ ለከተማይቱ ለጋራ ጉዳይዋ፥ ለመኖሪያ ለማሰማርያም ይሆናል፥ ከተማይቱም በመካከሉ ትሆናለች። ልክዋም ይህ ነው፥ በሰሜን በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በደቡብም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በምሥራቅም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በምዕራብም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ይሆናል። ለከተማይቱም ማሰማርያ ይኖራታል፥ በሰሜን በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በደቡብም በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በምሥራቅም በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በምዕራብም በኩል ሁለት መቶ አምሳ ክንድ ይሆናል። በተቀደሰው መባ አንጻር የተረፈው ርዝመቱ ወደ ምሥራቅ አሥር ሺህ ወደ ምዕራብም አሥር ሺህ ክንድ ይሆናል። በተቀደሰው መባ አንጻር ይሆናል። ፍሬውም ከተማይቱን ለሚያገለግሉ ለመብል ይሆናል። ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከተማይቱን የሚያገለግሉ ያርሱታል። መባው ሁሉ ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል፥ የተቀደሰውን መባ ከከተማይቱ ይዞታ ጋር አራት ማዕዘን አድርጋችሁ ትሰጣላችሁ። በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ በዚህና በዚያ ወገን የቀረው ለአለቃው ይሆናል፥ በመባው በሃያ አምስቱ ሺህ ፊት ወደ ምሥራቁ ድንበር፥ በምዕራብም በኩል በሀያ አምስቱ ሺህ ፊት ወደ ምዕራቡ ድንበር፥ እንደ ዕጣ ክፍል ሁሉ መጠን፥ ለአለቃው ይሆናል፥ የተቀደሰውም መባና ቤተ መቅደሱ በመካከሉ ይሆናል። የሌዋውያንም ርስት የከተማይቱም ይዞታ ለአለቃው በሆነው መካከል ይሆናል፥ በይሁዳ ድንበርና በብንያም ድንበር መካከል የአለቃ ዕጣ ክፍል ይሆናል። ለቀሩትም ነገዶች እንዲህ ይሆናል፥ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለብንያም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከብንያምም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለስምዖን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከስምዖንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለይሳኮር አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከይሳኮርም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለዛብሎን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከዛብሎንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለጋድ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከጋድም ድንበር ቀጥሎ በደቡብ በኩል ድንበሩ ከታማር ጀምሮ እስከ ሜሪባ ቃዴስ ውኃ እስከ ግብጽ ወንዝ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሆናል። ርስት አድርጋችሁ ለእስራኤል ነገዶች በዕጣ የምታካፍሉአት ምድር ይህች ናት፥ የእያንዳንዱም ዕጣ እንደዚህ ነው፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የከተማይቱም መውጫዎች እነዚህ ናቸው። በሰሜን ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ነው። የከተማይቱ በሮች እንደ እስራኤል ነገዶች ስም ይሆናሉ፥ በሰሜን በኩል አንዱ የሮቤል በር አንዱም የይሁዳ በር አንዱም የሌዊ በር፥ ሦስት በሮች ይሆናሉ። በምሥራቁም ወገን አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፥ አንዱ የዮሴፍ በር አንዱም የብንያም በር አንዱም የዳን በር ነው። በደቡብም ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፥ አንዱ የስምዖን በር አንዱም የይሳኮር በር አንዱም የዛብሎን በር ነው። በምዕራቡም ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፥ አንድ የጋድ በር አንዱም የአሴር በር አንዱም የንፍታሌም በር ነው። ዙሪያዋም አሥራ ስምንት ሺህ ክንድ ይሆናል፥ ከዚያም ቀን ጀምሮ የከተማይቱ ስም፦ እግዚአብሔር በዚያ አለ ተብሎ ይጠራል።
ሕዝቅኤል 48:1-35 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ምድሪቱን ለመካፈል የተመዘገቡት ነገዶች እነዚህ ናቸው፤ የዳን ነገድ በምድሪቱ ሰሜናዊ ወሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ እርሱም ከሔትሎን ወደ ሐማት መግቢያ የሚወስደውን ጐዳና ተከትሎ ከዚያም ሐጻርዔኖንና የደማስቆ ሰሜናዊ ክፍል ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የዳን ድንበር ይሆናል። አሴርም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከዳን ይዞታ ጋር የሚዋሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ንፍታሌም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከአሴር ይዞታ ጋር የሚዋሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ምናሴ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከንፍታሌም ይዞታ ጋር የሚዋሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ኤፍሬም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከምናሴ ይዞታ ጋር የሚዋሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ሮቤል ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከኤፍሬም ይዞታ ጋር የሚዋሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይሁዳ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከሮቤል ይዞታ ጋር የሚዋሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል። ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከይሁዳ ነገድ ድንበር ጋር የተያያዘ ቦታ ለይታችሁ ትመደባላችሁ፤ ይህም ቦታ ወርዱ ኻያ አምስት ሺህ ክንድ ርዝመት ከሌሎች ነገዶች ድርሻ ጋር ከምሥራቅ ጐን እስከ ምዕራብ ጐን ድረስ እኩል ይሆናል፤ ቤተ መቅደሱም የሚገኘው በዚህ ቦታ መካከል ነው። በዚህም ክልል መካከል ርዝመቱ ኻያ አምስት ሺህ ክንድ፥ ወርዱም ኻያ ሺህ ክንድ የሆነ ቦታ ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናል። ካህናቱም ከዚህ ከተቀደሰው ቦታ የተወሰነ ድርሻ ይኖራቸዋል፤ እርሱም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ኻያ አምስት ሺህ ክንድ ርዝመትና ከሰሜን እስከ ደቡብ ዐሥር ሺህ ክንድ ወርድ ይኖረዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም በመካከሉ ይኖራል። ይህም ቦታ የሳዶቅ ተወላጆች ለሆኑት የተቀደሱ ካህናት የተለየ ይሆናል። እስራኤላውያን ሁሉና ሌሎቹ ሌዋውያን እኔን ትተው በባዘኑ ጊዜ የሳዶቅ ልጆች ከትእዛዞቼ ፈቀቅ ሳይሉ ጠብቀው የኖሩ ናቸው። ከተቀደሰው ቦታ ይህ የእነርሱ ድርሻ ነው፤ እርሱም በጣም የተቀደሰ ሲሆን ከሌዋውያን ድንበር ጋር የተያያዘ ነው። ከካህናቱ ቦታ ጐን ኻያ አምስት ሺህ ክንድ ርዝመትና ዐሥር ሺህ ክንድ ወርድ የሆነ የሌዋውያን ድርሻ አለ፤ ጠቅላላውም ከካህናቱ ድርሻ ጋር ኻያ አምስት ሺህ ክንድ ርዝመትና ኻያ ሺህ ክንድ ወርድ ነው። ለእግዚአብሔር የሚከለለው ስፍራ በምድሪቱ ከሚገኘው ሁሉ የተሻለ ምርጥ ቦታ ነው፤ ከእርሱም ተከፍሎ የሚሸጥና የሚለወጥ ወይም ለማንም በውርስ የሚተላለፍ አይሆንም፤ እርሱ ለእግዚአብሔር ተለይቶ የተቀደሰ ስፍራ ነው። ልዩ ከሆነው ክልል ተከፍሎ የሚቀረው ስፍራ ኻያ አምስት ሺህ ክንድ ርዝመት አምስት ሺህ ክንድ ወርድ ነው፤ እርሱም በአጠቃላይ ለሕዝቡ የጋራ መጠቀሚያ ይሆናል፤ ለቤት ሥራና ለከብት ማሰማሪያም ይሆናል፤ ከተማይቱም በመካከሉ ትሆናለች። እርስዋም አራት ማእዘን እኩል ርዝመት ያላት ሆና የእያንዳንዱ ማእዘን ርዝመት አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ይሆናል። ከተማዋ በአራቱም ማእዘን የመሰማሪያ ቦታ ይኖራታል፤ በየማእዘኑ ያለው የመሰማሪያ ቦታ ስፋት ሁለት መቶ ኀምሳ ክንድ ነው። ከተቀደሰው ክልል በምሥራቅ ዐሥር ሺህ ክንድ በምዕራብ ዐሥር ሺህ ክንድ ተነሥቶለት ከተማይቱ ከተሠራች በኋላ የሚቀረው ትርፍ ቦታ በከተማይቱ ለሚኖሩት ሕዝብ የእርሻ መሬት ይሆናል። በከተማይቱ የሚኖር ከየትኛውም ነገድ የተወለደ ሰው ሁሉ ያን መሬት ማረስ ይችላል። ስለዚህም በምድሪቱ መኻል የተለየው ቅዱስ ድርሻ በጠቅላላው የእያንዳንዱ ማእዘን ርዝመት ኻያ አምስት ሺህ ክንድ ሲሆን እርሱም ከተማይቱ የተሠራችበትን ቦታ ያጠቃልላል። በተቀደሰው ቦታና በከተማውም ይዞታ በሁለቱም በኩል የተረፈው ክፍል የመስፍኑ ድርሻ ነው። ይኸውም በምሥራቅ በኩል የተቀደሰውን ቦታ ከሚያዋስነው ኻያ አምስት ሺህ ክንድ ተነሥቶ እስከ ምድሪቱ ወሰን ድረስ ነው። በምዕራብም በኩል የተቀደሰውን ቦታ ከሚያዋስነው ከኻያ አምስት ሺህ ክንድ ተነሥቶ እስከ ምድሪቱ ወሰን ድረስ ነው። የመሪውም ድርሻ ርዝመቱ ከሌሎቹ ነገዶች ድርሻ እኩል ነው። በዚህ ዐይነት የተቀደሰው ቦታና ቤተ መቅደሱ በመካከል ይሆናሉ ማለት ነው። እንደዚሁም የሌዋውያኑና የከተማው ይዞታ በምሥራቅና በምዕራብ የመሪው ይዞታ ከሆኑት ቦታዎች መካከል ናቸው ማለት ነው፤ እንዲሁም በሰሜን ከይሁዳ ዕጣ፥ በደቡብም ከብንያም ዕጣ ጋር ይዋሰናል። ስለቀሩትም ነገዶች የምድሪቱ አከፋፈል እንደሚከተለው ነው፤ ብንያም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የሚደርስ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ስምዖን ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከብንያም ይዞታ ጋር የሚዋሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይሳኮር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከስምዖን ይዞታ ጋር የሚዋሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ዛብሎን ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከይሳኮር ይዞታ ጋር የሚዋሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ጋድ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከዛብሎን ይዞታ ጋር የሚዋሰን አንድ ድርሻ ይኖረዋል። የጋድ ደቡባዊ ድንበር ከታማር ከተማ ደቡብ ተነሥቶ በመሪባ ቃዴስ እስከምትገኘው የውሃ ምንጭ ይዘልቃል፤ ከዚያም የግብጽ ወሰን የሆነውን ወንዝ ተከትሎ እስከ ሜዲቴራኒያን ባሕር ይደርሳል። ልዑል እግዚአብሔር “በዚህ ዐይነት ለእስራኤል ነገዶች ሁሉ በርስትነት የምታከፋፍሉአቸው ምድር ይህች ናት” ሲል ተናገረ። የከተማይቱ መውጫ በሮች አራት ማእዘኖች የሚከተሉት ናቸው፦ በየማእዘኑ ሦስት በሮች ሲኖሩ ለያንዳንዱ በር የአንድ ነገድ ስም ተሰጥቶታል። በሰሜን በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ርዝመት አለው። በዚህ ማእዘን ያሉት ሦስት በሮች በሮቤል፥ በይሁዳና በሌዊ ስም ተሰይመዋል። በምሥራቅ በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ርዝመት አለው። በዚህ ማእዘን ያሉት ሦስት በሮች በዮሴፍ፥ በብንያምና በዳን ስም ተሰይመዋል። በደቡብ በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ርዝመት አለው። በዚህም ማእዘን ያሉት ሦስት በሮች በስምዖን፥ በይሳኮርና በዛብሎን ስም ተሰይመዋል። በምዕራብ በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ርዝመት አለው። በዚህም ማእዘን ያሉት ሦስት በሮች በጋድ፥ በአሴርና በንፍታሌም ስም ተሰይመዋል። በአራቱም አቅጣጫ ያሉት የከተማይቱ የቅጽር ግንቦች ጠቅላላ ርዝመት ዐሥራ ስምንት ሺህ ክንድ ይሆናል፤ ከአሁን በኋላ የከተማይቱ መጠሪያ ስም “እግዚአብሔር በዚያ አለ!” የሚል ይሆናል።
ሕዝቅኤል 48:1-35 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የነገዶቹ ስም ይህ ነው። ከሰሜን ወሰን በሔትሎን መንገድ አጠገብ ወደ ሐማት መግቢያ በደማስቆም ድንበር ባለው በሐጸርዔናን በሐማትም አጠገብ በሰሜን በኩል ካለው ከሰሜን ድንበር ይጀምራል። ወርዳቸውም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ይሆናል። ለዳን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከዳን ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ አሴር አንድ ድርሻ ይኖረዋል። ከአሴር ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ንፍታሌም አንድ ድርሻ ይኖረዋል። ከንፍታሌም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ምናሴ አንድ ድርሻ ይኖረዋል። ከምናሴ ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ኤፍሬም አንድ ድርሻ ይኖረዋል። ከኤፍሬም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ሮቤል አንድ ድርሻ ይኖረዋል። ከሮቤል ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ይሁዳ አንድ ድርሻ ይኖረዋል። ከይሁዳ ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለምታቀርቡት መባ የሚሆን ድርሻ ይሆናል፤ ወርዱ ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል፥ ርዝመቱም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ይሆናል፥ ከድርሻዎቹ እንደ አንዱ ይሆናል፥ መቅደሱም በመካከሉ ይሆናል። ለጌታ የምታቀርቡት መባ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ወርዱ ደግሞ አስር ሺህ ክንድ ይሆናል። ይህም ለካህናቱ የተቀደሰ መባ ይሆናል፤ በሰሜን በኩል ሀያ አምስት ሺህ፥ በምዕራብ በኩል ወርዱ ዐሥር ሺህ፥ በምሥራቅ በኩል ወርዱ ዐሥር ሺህ፥ በደቡብ በኩል ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል። የጌታ መቅደስም በመካከሉ ይሆናል። ሌዋውያን በሳቱ ጊዜ፥ እንደ ሳቱት እንደ እስራኤል ልጆች ላልሳቱት ሥርዓቴን ለጠበቁት ከሳዶቅ ልጆች ለተቀደሱት ካህናት ይሆናል። ከምድሪቱ መባ የተቀደሰው መባ ለእነርሱ ይሆናል፥ እጅግ የተቀደሰ ይሆናል፤ በሌዋውያን ድንበር አጠገብ ይሆናል። ለሌዋውያኑ በካህናቱ ድንበር አጠገብ ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም ዐሥር ሺህ ይሆናል፥ ርዝመቱ ሁሉ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም ዐሥር ሺህ ክንድ ይሆናል። ለጌታ የተቀደሰ ስለሆነ ከእርሱ ምንም አይሸጡም አይለውጡም፥ የምድሪቱንም በኵራት ወደ ሌላ አይተላለፍም። በሀያ አምስቱ ሺህ ፊት ለፊት አምስት ሺህ ወርድ ያለው የቀረ ስፍራ ለከተማይቱ ለጋራ ጉዳይዋ፥ ለመኖሪያና ለማሰማርያ ይሆናል፤ ከተማይቱም በመካከሉ ትሆናለች። ልክዋም ይህ ነው፤ በሰሜን በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በደቡብ በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በምሥራቅ በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በምዕራብም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ይሆናል። ከተማይቱ ማሰማርያ ይኖራታል፤ በሰሜን በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በደቡብ በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በምሥራቅ በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በምዕራብም በኩል ሁለት መቶ አምሳ ክንድ ይሆናል። በተቀደሰው መባ አጠገብ የተረፈው ርዝመቱ ወደ ምሥራቅ ዐሥር ሺህ ወደ ምዕራብም ዐሥር ሺህ ክንድ ይሆናል። ይህም በተቀደሰው መባ አጠገብ ይሆናል። ምርቷም ከተማይቱን ለሚያገለግሉ ለመብል ይሆናል። ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከተማይቱን የሚያገለግሉ ያርሱታል። መባው ሁሉ ርዝመቱ ሀያ አምስት ሺህ ወርዱም ሀያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል፤ የተቀደሰውን መባ ከከተማይቱ ድርሻ ጋር አራት ማዕዘን አድርጋችሁ ትሰጣላችሁ። በተቀደሰው መባና በከተማይቱ ይዞታ በዚህና በዚያ ወገን የቀረው ለአለቃው ይሆናል፤ በመባው በሃያ አምስቱ ሺህ ፊት ወደ ምሥራቁ ድንበር፥ በምዕራብም በኩል በሀያ አምስቱ ሺህ ፊት ወደ ምዕራቡ ድንበር፥ እንደ ዕጣ ክፍሎች ሁሉ መጠን፥ ለአለቃው ይሆናል፤ የተቀደሰውም መባና ቤተ መቅደሱ በመካከሉ ይሆናል። የሌዋውያንም ርስት የከተማይቱም ይዞታ ለአለቃው በሆነው መካከል ይሆናል፤ በይሁዳ ድንበርና በብንያም ድንበር መካከል የአለቃ ዕጣ ክፍል ይሆናል። ለቀሩትም ነገዶች እንዲህ ይሆናል፤ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለብንያም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከብንያምም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለስምዖን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከስምዖንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለይሳኮር አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከይሳኮርም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለዛብሎን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከዛብሎንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለጋድ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። ከጋድ ድንበር ቀጥሎ በደቡብ በኩል ድንበሩ ከታማር ጀምሮ እስከ ሜሪባ ቃዴስ ውኃ እስከ ግብጽ ወንዝ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሆናል። ለእስራኤል ነገዶች ርስት አድርጋችሁ የምታካፍሉአት ምድር ይህች ናት፥ የእያንዳንዱም ዕጣ እንደዚህ ነው፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የከተማይቱ መውጫዎች እነዚህ ናቸው። በሰሜን ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ነው። የከተማይቱ በሮች በእስራኤል ነገዶች ስም ይጠራሉ፤ በሰሜን በኩል ሦስት በሮች አሉ፥ አንዱ የሮቤል በር፥ አንዱ የይሁዳ በር፥ አንዱ ደግሞ የሌዊ በር ነው። በምሥራቅ በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ነው፥ ሦስት በሮችም አሉ፤ አንዱ የዮሴፍ በር፥ አንዱ የብንያም በር፥ አንዱ ደግሞ የዳን በር ነው። በደቡብ በኩል ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ነው፥ ሦስት በሮችም አሉ፤ አንዱ የስምዖን በር፥ አንዱ የይሳኮር በር አንዱ ደግሞ የዛብሎን በር ነው። በምዕራቡም በኩል ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ነው፥ ሦስት በሮችም አሉ፤ አንዱ የጋድ በር፥ አንዱ የአሴር በር፥ አንዱ ደግሞ የንፍታሌም በር ነው። ዙሪያዋ ዐሥራ ስምንት ሺህ ክንድ ይሆናል፥ ከዚያም ቀን ጀምሮ የከተማይቱ ስም፦ “ጌታ በዚያ አለ” ተብሎ ይጠራል።