ሕዝቅኤል 43:16-19
ሕዝቅኤል 43:16-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የምድጃውም ርዝመት ዐሥራ ሁለት ክንድ፥ ወርዱም ዐሥራ ሁለት ክንድ ነው፥ አራቱም ማዕዘን ትክክል ነው። የእርከኑም ርዝመት ዐሥራ አራት ክንድ፥ ወርዱም ዐሥራ አራት ክንድ ነው፤ አራቱም መዐዝን ትክክል ነው፤ በዙሪያውም ያለው ክፈፍ የክንድ እኩሌታ ነው፤ መሠረቱም በዙሪያው አንድ ክንድ ነው፤ ደረጃዎቹም ወደ ምሥራቅ ይመለከታሉ።” እንዲህም አለኝ፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡበት ዘንድ፥ ደሙንም ይረጩበት ዘንድ በሚሠሩበት ቀን የመሠዊያው ሕግ ይህ ነው። ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ እኔ ለሚቀርቡ ከሳዶቅ ዘር ለሚሆኑ ለሌዋውያኑ ካህናት ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ከመንጋው አንድ ወይፈን ትሰጣቸዋለህ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
ሕዝቅኤል 43:16-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የመሠዊያው ምድጃ እኩል በእኩል ሲሆን፣ ርዝመቱ ዐሥራ ሁለት ክንድ፣ ወርዱም ዐሥራ ሁለት ክንድ ነው። ላይኛው ዕርከንም እንዲሁ እኩል በእኩል ሆኖ ዐሥራ አራት ክንድ ርዝመትና ዐሥራ አራት ክንድ ወርድ አለው፤ ግማሽ ክንድ ጠርዝና ዙሪያውን በሙሉ አንድ ክንድ የሆነ ቦይ ነበረው። የመሠዊያው ደረጃዎችም በምሥራቅ ትይዩ ናቸው።” ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ መሠዊያው ተሠርቶ፣ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚሠዋበትና በመሠዊያው ላይ ደም በሚረጭበት ጊዜ ሥርዐቶቹ እነዚህ ናቸው፤ በፊቴ ቀርበው ለሚያገለግሉኝ ካህናት፣ ለሌዋውያኑ ለሳዶቅ ቤተ ሰብ የኀጢአት መሥዋዕት የሚሆን አንድ ወይፈን ስጥ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
ሕዝቅኤል 43:16-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የምድጃውም ርዝመት አሥራ ሁለት ክንድ ወርዱም አሥራ ሁለት ክንድ ነው፥ አራቱም ማዕዘን ትክክል ነው። የእርከኑም ርዝመት አሥራ አራት ክንድ ወርዱም አሥራ አራት ክንድ ነው፥ አራቱም ማዕዘን ትክክል ነው፥ በዙሪያውም ያለው ክፈፍ እኩል ክንድ ነው፥ መሠረቱም በዙሪያው አንድ ክንድ ነው፥ ደረጃዎቹም ወደ ምሥራቅ ይመለከታሉ። እንዲህም አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡበት ዘንድ ደሙንም ይረጩበት ዘንድ በሚሠሩበት ቀን የመሠዊያው ሕግ ይህ ነው። ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ እኔ ለሚቀርቡ ከሳዶቅ ዘር ለሚሆኑ ለሌዋውያኑ ካህናት ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ትሰጣቸዋለህ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
ሕዝቅኤል 43:16-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እሳቱ የሚነድበት ክፍል አራት ማእዘን ሲሆን የያንዳንዱ ማእዘን ርዝመት ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበር። የላይኛው እርከን እንደ ሌሎቹ እኩል አራት ማእዘን ነበረው፤ እነርሱም ዐሥራ አራት ክንድ ርዝመትና ዐሥራ አራት ክንድ ወርድ ሲሆኑ የጠርዙ ዙሪያ ግማሽ ክንድ ስፋት ነበረው፤ የማረፊያውም ዙሪያ አንድ ክንድ ስፋት ነበረው፤ መወጣጫዎቹም በስተምሥራቅ በኩል ነበሩ። ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ‘የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለማቅረብና በእርሱ ላይ ደምን ለመርጨት ይህ መሠዊያ በተሠራ ጊዜ በመሠዊያው ላይ የሚፈጸመው ሥነ ሥርዓት እንደሚከተለው ይሆናል። በፊቴ ቆመው እኔን ለሚያገልገሉ የሌዊ ነገድ ከሆነው ከሳዶቅ ዘር ለተወለዱ የኃጢአት ሥርየት መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ ዘንድ ለእነርሱ አንድ ወይፈን ትሰጣቸዋለህ፤’ ይላል ልዑል እግዚአብሔር።
ሕዝቅኤል 43:16-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የመሠዊያው ምድጃ ርዝመት ዐሥራ ሁለት ክንድ፥ ወርዱም ዐሥራ ሁለት ክንድ ነው፥ አራቱም ማዕዘን እኩል ነው። የእርከኑም ርዝመት ዐሥራ አራት ክንድ ወርዱም ዐሥራ አራት ክንድ ነው፥ አራቱም ማዕዘን እኩል ነው፤ በዙሪያውም ያለው ጠርዝ ግማሽ ክንድ ነው፥ የመሠረቱም ዙሪያ አንድ ክንድ ነው፤ ደረጃዎቹ ወደ ምሥራቅ ይመለከታሉ። እንዲህም አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ መሠዊያው ተሰርቶ የሚቃጠለውን መሥዋዕት በላዩ በሚያቀርቡበት ደምንም በላዩ በሚረጩበት ቀን የመሠዊያው ሥርዓት ይህ ነው። ሊያገለግሉኝ ወደ እኔ ለሚቀርቡ ለካህናት፥ ከሳዶቅ ዘር ለሆኑ ለሌዋውያን ለኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ትሰጣቸዋለህ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።