ሕዝቅኤል 31:4-9
ሕዝቅኤል 31:4-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ውኃም አበቀለው፥ ቀላይም አሳደገው፥ ወንዞችም በተተከለበት ዙሪያ ይጎርፉ ነበር፤ ፈሳሾቹንም ወደ ምድረ በዳ ዛፍ ሁሉ ላከ። ስለዚህ ቁመቱ ከምድረ በዳ ዛፍ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ አለ፤ ቅርንጫፎቹም በዙ፤ ጫፎቹም ከብዙ ውኆች የተነሣ ረዘሙ። የሰማይም ወፎች ሁሉ በቅርንጫፎቹ ላይ ተዋለዱ፤ የምድርም አራዊት ሁሉ ከጫፎቹ በታች ተዋለዱ፤ ከጥላውም በታች ታላላቆች አሕዛብ ሁሉ ይቀመጡ ነበር። ሥሩም በብዙ ውኃ አጠገብ ነበረና በታላቅነቱና በጫፎቹ ርዝመት የተዋበ ነበረ። በእግዚአብሔር ገነት የነበሩ ዝግባዎች አይተካከሉትም፥ ጥዶችም ቅርንጫፎቹን፥ አስታ የሚባለውም ዛፍ ጫፎቹን አይመሳሰሉትም ነበር፤ የእግዚአብሔርም ገነት ዛፍ ሁሉ በውበቱ አይመስለውም ነበር። በጫፎቹ ብዛት ውብ አደረግሁት፤ በእግዚአብሔርም ገነት በዔድን የነበሩ ዛፎች ሁሉ ቀኑበት።
ሕዝቅኤል 31:4-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ውሆች አበቀሉት፤ ጥልቅ ምንጮች አሳደጉት፤ ጅረቶቻቸው ፈሰሱ፤ የሥሮቹንም ዙሪያ ሁሉ አረሰረሱ፤ በመስኩ ላይ ወዳሉት ዛፎች ሁሉ፣ መስኖዎቻቸውን ለቀቁት። ስለዚህ በደን ካሉት ዛፎች ሁሉ፣ እጅግ ከፍ አለ፤ ቅርንጫፎቹ በዙ፤ ቀንበጦቹ ረዘሙ፤ ከውሃውም ብዛት የተነሣ ተስፋፉ። የሰማይ ወፎች ሁሉ፣ በቅርንጫፎቹ ላይ ጐጇቸውን ሠሩ፤ የምድር አራዊት ሁሉ፣ ከቅርንጫፎቹ ሥር ግልገሎቻቸውን ወለዱ። ታላላቅ መንግሥታትም ሁሉ፣ ከጥላው ሥር ኖሩ። ከተንሰራፉት ቅርንጫፎቹ ጋራ፣ ውበቱ ግሩም ነበር፤ ብዙ ውሃ ወዳለበት፣ ሥሮቹ ጠልቀው ነበርና። በእግዚአብሔርም የአትክልት ቦታ ያሉ ዝግባዎች፣ ሊወዳደሩት አልቻሉም፤ የጥድ ዛፎች፣ የርሱን ቅርንጫፎች አይተካከሉትም፤ የኤርሞን ዛፎችም፣ ከርሱ ቅርንጫፎች ጋራ አይወዳደሩም፤ በእግዚአብሔርም የአትክልት ቦታ ያለ ማንኛውም ዛፍ፣ በውበት አይደርስበትም። በብዙ ቅርንጫፎች፣ ውብ አድርጌ ሠራሁት፤ በእግዚአብሔርም የአትክልት ቦታ፣ በዔድን ያሉትን ዛፎች የሚያስቀና አደረግሁት።
ሕዝቅኤል 31:4-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ውኆችም አበቀሉት፥ ቀላይም አሳደገው፥ ወንዞችም በተተከለበት ዙሪያ ይጐርፉ ነበር፥ ፈሳሾቹንም ወደ ምድረ በዳ ዛፍ ሁሉ ሰደደ። ስለዚህ ቁመቱ ከምድረ በዳ ዛፍ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ አለ፥ ቅርንጫፎቹም በዙ፥ ጫፎቹንም ባበቀለ ጊዜ ከብዙ ውኆች የተነሣ ረዘሙ። የሰማይ ወፎች ሁሉ ጎጆቻቸውን በቅርንጫፎቹ ላይ አደረጉ፥ የምድርም አራዊት ሁሉ ከጫፎቹ በታች ተዋለዱ፥ ከጥላውም በታች ታላላቆች አሕዛብ ሁሉ ይቀመጡ ነበር። ሥሩም በብዙ ውኃ አጠገብ ነበረና በታላቅነቱና በጫፎቹ ርዝመት የተዋበ ነበረ። በእግዚአብሔር ገነት የነበሩ ዝግባዎች አላጨለሙትም፥ ጥዶችም ቅርጫፎቹን አስታ የሚባለውም ዛፍ ጫፎቹን አይመሳሰሉትም ነበር፥ የእግዚአብሔርም ገነት ዛፍ ሁሉ በውበቱ አይመሳሰለውም ነበር። በጫፎቹም ብዛት ውብ አደረግሁት በእግዚአብሔርም ገነት በዔድን የነበሩ ዛፎች ሁሉ ቀኑበት።
ሕዝቅኤል 31:4-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እዚያም ዛፉን የሚያሳድገው በቂ ውሃ ነበረው፤ በመሬት ውስጥ ያለው ጥልቅ ውሃ ዛፉን ያሳድገዋል፤ ጅረቶችም በሜዳ በተተከሉ ዛፎች ዙሪያ ይፈስሳሉ። ይህም ዛፍ ብዙ ውሃ በማግኘቱ፥ ቁመቱ ከሌሎች ዛፎች ሁሉ የረዘመ ሆነ፤ ቅርንጫፎቹም ወፍራሞችና ረጃጅሞች ሆኑ። የወፍ ዐይነቶች ሁሉ በቅርንጫፎቹ ላይ ጎጆአቸውን ሠሩ፤ የምድር አራዊትም ግልገሎቻቸውን በጥላዎቹ ሥር ወለዱ፤ ታላላቅ ሕዝቦች ሁሉ በጥላው ሥር ያርፉ ነበር። ብዙ ውሃ ወዳለበት ሥሮቹን ስለ ሰደደ፥ ታላቅነቱና የቅርንጫፎቹ መስፋፋት ውበትን ሰጥቶት ነበር። በእግዚአብሔር ገነት ውስጥ ያለው የሊባኖስ ዛፍ ሊወዳደረው አይችልም፤ የጥድ ዛፍም ቅርንጫፉን አያኽልም፤ የግራር ዛፎች ቅርንጫፍ ከእርሱ ቅርንጫፎች ጋር ሲወዳደር እንደ ኢምንት ነው። በእግዚአብሔር ገነት ውስጥ ካሉ ዛፎች መካከል አንዳቸው እንኳ እንደ እርሱ ያለ ውበት የላቸውም። እኔ እርሱን በተንሠራፉ ቅርንጫፎች የተዋበ አደረግሁት፤ እርሱ እኔ እግዚአብሔር በተከልኳት በዔደን ገነት ያለውን ዛፍ ሁሉ የሚያስቀና ነበር።’
ሕዝቅኤል 31:4-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ውኆች አበቀሉት፥ ጥልቅ ውኃ አሳደገው፥ ወንዞቹም በተተከለበት ዙሪያ ይጐርፉ ነበር፥ ፈሳሾቹንም ወደ ምድረ በዳ ዛፍ ሁሉ ሰደደ። ስለዚህ ቁመቱ ከሜዳ ዛፍ ሁሉ በላይ በለጠ፥ ቅርንጫፎቹም በዙ፥ በለቀቀላቸውም ጊዜ ከብዙ ውኆች የተነሣ ቅርንጫፎቹ ረዘሙ። የሰማይ ወፎች ሁሉ ጎጆአቸውን በቅርንጫፎቹ ላይ ሠሩ፥ የምድር አራዊት ሁሉ ከቅርጫፎቹ በታች ወለዱ፥ ታላላቅ ሕዝቦች ሁሉ ከጥላው በታች ኖሩ። ሥሩ በብዙ ውኃ አጠገብ ስለ ነበረ በታላቅነቱና በቅርጫፎቹ ርዝመት የተዋበ ነበረ። በእግዚአብሔር ገነት የነበሩ ዝግባዎች አልሸፈኑትም፥ ጥዶችም ቅርጫፎቹን አይመስሉትም አስታ የሚባለውም ዛፍ ቅርጫፎቹን አይመሳሰሉትም ነበር፤ በእግዚአብሔር ገነት የነበረ ዛፍ ሁሉ በውበቱ አይመስለውም ነበር። በቅርጫፎቹ ብዛት ውብ አደረግሁት፥ በእግዚአብሔርም ገነት በዔድን የነበሩ ዛፎች ሁሉ ቀኑበት።