ሕዝቅኤል 12:1-28
ሕዝቅኤል 12:1-28 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! በዐመፀኛ ቤት መካከል ተቀምጠሃል፤ እነርሱ ያዩ ዘንድ ዐይን አላቸው ነገር ግን አያዩም፤ ይሰሙም ዘንድ ጆሮ አላቸው፤ ነገር ግን አይሰሙም፤ እነርሱ ዐመፀኛ ቤት ናቸውና። አንተም የሰው ልጅ ሆይ! የስደተኛ እክት አዘጋጅ፤ በፊታቸውም ቀን ለቀን ተማረክ፤ በፊታቸውም ከስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ተማርከህ ሂድ፤ እነርሱም ዐመፀኛ ቤት እንደ ሆኑ ምንአልባት ያስተውሉ ይሆናል። ቀን ለቀንም በፊታቸው እክትህን እንደ ስደተኛ እክት አውጣው፤ በማታም ጊዜ በዐይናቸው እያዩህ ስደተኞች እንደሚወጡ እንዲሁ ውጣ። በፊታቸውም ግንቡን ነድለህ በዚያ ውጣ። ለእስራኤልም ቤት ምልክት አድርጌሃለሁና በፊታቸው ዕቃህን በትከሻህ ላይ አንግተው፤ በጨለማም ተሸክመህ ውጣ፤ ምድሪቱንም እንዳታይ ፊትህን ሸፍን።” እንዳዘዘኝም አደረግሁ፤ ቀን ለቀንም እክቴን እንደ ስደተኛ እክት አወጣሁ፤ በማታም ጊዜ ግንቡን በእጄ ነደልሁ፤ በጨለማም አወጣሁት፤ በፊታቸውም በትከሻዬ ላይ አንግቼ ተሸከምሁት። በነጋውም የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ዐመፀኛ ቤት የእስራኤል ቤት፦ የምታደርገው ምንድር ነው? አላሉህምን? አንተም፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህ ሸክም በኢየሩሳሌም በሚኖረው አለቃ ላይ፥ በመካከላቸውም በሚኖሩት በእስራኤል ቤት ሁሉ ላይ ነው በላቸው። ደግሞም፦ እኔ ምልክታችሁ ነኝ፤ እኔ እንዳደረግሁ እንዲሁ ይደረግባቸዋል፥ እነርሱንም ማርከው ይወስዷቸዋል በል። በመካከላቸውም የሚኖረው አለቃ በትከሻው ላይ አንግቶ በጨለማ ይወጣል፤ በዚያ ያወጡ ዘንድ ግንቡን ይነድላሉ፤ በዐይኑም ምድርን እንዳያይ ፊቱን ይሸፍናል። መረቤንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ፤ በወጥመዴም ይያዛል፤ ወደ ከለዳውያንም ምድር ወደ ባቢሎን አመጣዋለሁ፤ ሆኖም አያያትም፤ በዚያም ይሞታል። የሚረዱትንም፥ በዙሪያው ያሉትን ሁሉ፥ ጭፍሮቹንም ሁሉ ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፤ በኋላቸውም ሰይፍን እመዝዛለሁ። በአሕዛብም መካከል በምበትናቸው ጊዜ፥ በሀገሮችም በምዘራቸው ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። በሚሄዱባቸውም አሕዛብ መካከል ርኵሰታቸውን ሁሉ ይናገሩ ዘንድ ከሰይፍና ከራብ፥ ከቸነፈርም ጥቂቶች ሰዎችን ከእነርሱ አስቀራለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! እንጀራህን በመታወክ ብላ፤ ውኃህንም በፍርሃትና በድንጋጤ ጠጣ፤ ለምድሪቱም ሕዝብ፦ ጌታ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ስለሚኖሩ ስለ እስራኤል ምድርም እንዲህ ይላል፦ የሚኖሩባት ሁሉ በዐመፅ ይኖራሉና ምድሪቱ በመላዋ ትጠፋ ዘንድ እንጀራቸውን በችግር ይበላሉ፤ ውኃቸውንም በድንጋጤ ይጠጣሉ። ሰዎች የሚኖሩባቸው ከተሞች ይጠፋሉ፤ ምድሪቱም ውድማ ትሆናለች፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ በላቸው።” የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! በእስራኤል ምድር፦ ዘመኑ ረዝሞአል፤ ራእዩም ሁሉ ጠፍቶአል የምትሉት ምሳሌው ምንድን ነው? ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህን ምሳሌ አስቀረዋለሁ፤ በእስራኤልም ዘንድ ደግሞ ምሳሌ አድርገው አይናገሩትም፤ አንተ ግን፦ ዘመኑና የራእዩ ሁሉ ነገር ቀርቦአል በላቸው። ከዚህም በኋላ በእስራኤል ቤት መካከል ከንቱ ራእይና ውሸተኛ ምዋርት አይሆንም። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እናገራለሁ፤ የምናገረውም ቃል ይፈጸማል፤ ደግሞም አይዘገይም፤ እናንተ ዐመፀኛ ቤት ሆይ! በዘመናችሁ ቃሌን እናገራለሁ፤ እፈጽመውማለሁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ዐመፀኛው የእስራኤል ቤት፦ ይህቺ የሚያያት ራእይ ለብዙ ዘመን ናት፤ እርሱም ለሩቅ ወራት ትንቢትን ይናገራል” ይላሉ። ስለዚህ በላቸው፥ “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የምናገረው ቃል ይፈጸማል እንጂ ከቃሌ ሁሉ ደግሞ የሚዘገይ የለም፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
ሕዝቅኤል 12:1-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ በዐመፀኛ ሕዝብ መካከል ተቀምጠሃል፤ የሚያዩበት ዐይን አላቸው፤ ነገር ግን አያዩም፤ የሚሰሙበትም ጆሮ አላቸው፤ ነገር ግን አይሰሙም፤ ዐመፀኛ ሕዝብ ናቸውና። “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፤ እነርሱ እያዩህ በቀን ጓዝህን ጠቅልለህ ለመሰደድ ተዘጋጅ፤ ካለህበትም ስፍራ ተነሥተህ ወደ ሌላ ቦታ ሂድ፤ ዐመፀኛ ቤት ቢሆኑም ምናልባት ይህን ያስተውሉታል። በቀን እያዩ ጓዝህን እንደ ስደተኛ ጓዝ አውጣው፤ በምሽትም እያዩህ ስደተኛ እንደሚወጣ ውጣ። እነርሱ እያዩ ግንቡን ነድለህ ጓዝህን በዚያ አሹልክ። በፊታቸው ጓዝህን በትከሻህ ላይ አስቀምጥ፣ በምሽትም ተሸክመህ ውጣ። ለእስራኤል ቤት ምልክት አድርጌሃለሁና ምድሪቱን እንዳታይ ፊትህን ሸፍን።” እኔም በታዘዝሁት መሠረት አደረግሁ፤ በቀን ጓዜን ጠቅልዬ እንደ ስደተኛ ጓዝ አወጣሁ፤ በምሽትም ግንቡን በእጄ ነደልሁት፤ እያዩኝም በምሽት ጓዜን በትከሻዬ ላይ ተሸክሜ አወጣሁ። በማግስቱም ጧት የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ዐመፀኛው የእስራኤል ቤት፣ ‘ይህ የምታደርገው ምንድን ነው?’ ብለው ጠይቀውህ አልነበረምን? “እንዲህ በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ይህ የትንቢት ቃል በኢየሩሳሌም ለሚኖረው መስፍንና በዚያ ለሚገኙት ለእስራኤል ቤት ሁሉ ነው።’ ‘እኔ ምልክታችሁ ነኝ’ በላቸው። “እኔ እንዳደረግሁት፤ እንዲሁ በእነርሱ ይደረግባቸዋል፤ በምርኮኛነትም ተሰድደው ይሄዳሉ። “በመካከላቸው ያለው መስፍን በምሽት ጓዙን በትከሻው ተሸክሞ ይወጣል፤ ሾልኮ እንዲሄድ ግንቡ ይነደልለታል፤ ምድሪቱንም እንዳያይ ፊቱን ይሸፍናል። መረቤን በርሱ ላይ እዘረጋለሁ፤ በወጥመዴም ይያዛል፤ ወደ ከለዳውያን ምድር ወደ ባቢሎን አመጣዋለሁ፤ ነገር ግን እርሷን ሳያያት በዚያ ይሞታል። በዙሪያው ያሉትን ረዳቶቹንና ወታደሮቹን ሁሉ ወደ ነፋስ እበትናቸዋለሁ፤ በተመዘዘም ሰይፍ አሳድዳቸዋለሁ። “በአሕዛብ መካከል ስበትናቸውና በአገሮችም መካከል ስዘራቸው፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። ነገር ግን በሄዱባቸው አሕዛብ መካከል ስለ ጸያፍ ተግባራቸው ይናገሩ ዘንድ ከእነርሱ ጥቂቶቹን ከሰይፍ ከራብና ከቸነፈር አተርፋለሁ። በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ምግብህን በድንጋጤ ብላ፤ ውሃህንም በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ ጠጣ። ለምድሪቱ ሕዝብ እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌምና በእስራኤል ምድር ስለሚኖሩት እንዲህ ይላል፤ በዚያ ከሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ዐመፅ የተነሣ ምድራቸው ስለምትራቈት፣ ምግባቸውን በጭንቀት ይመገባሉ፤ ውሃቸውንም በፍርሀት ይጠጣሉ። ሰው ይኖርባቸው የነበሩ ከተሞች ባድማ ይሆናሉ፤ ምድሪቱም ወና ትሆናለች። በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።’ ” ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ በእስራኤል ምድር፣ ‘ዘመኑ ረዝሟል፤ ራእዩ ሁሉ ከንቱ ሆኗል’ የምትሉት ይህ አባባል ምንድን ነው? እንዲህ በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ይህን አባባል እሽራለሁ፤ በእስራኤልም ምድር ዳግመኛ በንግግራቸው አይጠቀሙበትም።” እንዲህም በላቸው፤ “ራእዩ ሁሉ የሚፈጸምበት ጊዜ ቀርቧል፤ በእስራኤል ሕዝብ መካከል ከእንግዲህ ሐሰተኛ ራእይና አሳሳች ሟርት አይገኝምና። ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር እናገራለሁ፤ የምናገረውም ቃል ሳይዘገይ ይፈጸማል፤ እናንተ ዐመፀኛ ቤት ሆይ፤ የተናገርሁትን ሁሉ በዘመናችሁ እፈጽማለሁ” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ” ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የእስራኤል ቤት፣ ‘ይህ ሰው የሚያየው ራእይ ገና ለሩቅ ዘመን የሚሆን ነው፤ የሚናገረውም ትንቢት የረዥም ጊዜ ትንቢት ነው’ ይላሉ። “ስለዚህ እንዲህ በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከተናገርሁት ቃል ከእንግዲህ የሚዘገይ የለም፤ የምለው ሁሉ ይፈጸማል ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”
ሕዝቅኤል 12:1-28 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በዓመፀኛ ቤት መካከል ተቀምጠሃል፥ ያዩ ዘንድ ዓይን አላቸው እነርሱም አያዩም፥ ይሰሙም ዘንድ ጆሮ አላቸው እነርሱም አይሰሙም፥ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና። አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የስደተኛ እክት አዘጋጅ በፊታቸውም ቀን ለቀን ተማረክ፥ በፊታቸውም ከስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ተማርከህ ሂድ፥ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት እንደ ሆኑ ምናልባት ያስተውሉ ይሆናል። ቀን ለቀንም በፊታቸው እክትህን እንደ ስደተኛ እክት አውጣው፥ በማታም ጊዜ በፊታቸው ስደተኞች እንደሚወጡ እንዲሁ ውጣ። በፊታቸውም ግንቡን ንደል በእርሱም አውጣ። ለእስራኤልም ቤት ምልክት አድርጌሃለሁና በፊታቸው በጫንቃህ ላይ አንግተው፥ በጨለማም ተሸክመህ ውጣ፥ ምድሪቱንም እንዳታይ ፊትህን ሸፍን። እንዳዘዘኝም አደረግሁ፥ ቀን ለቀንም እክቱን እንደ ስደተኛ እክት አወጣሁ፥ በማታም ጊዜ ግንቡን በእጄ ነደልሁ፥ በጨለማም አወጣሁት በፊታቸውም በጫንቃዬ ላይ አንግቼ ተሸከምሁት። በነጋውም የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ዓመፀኛ ቤት የእስራኤል ቤት፦ የምታደርገው ምንድር ነው? አላሉህምን? አንተም፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህ ሸክም በኢየሩሳሌም በሚኖረው አለቃ ላይ በመካከላቸውም በሚኖሩት በእስራኤል ቤት ሁሉ ላይ ነው በላቸው። ደግሞም፦ እኔ ምልክታችሁ ነኝ፥ እኔ እንዳደረግሁ እንዲሁ ይደረግባቸዋል፥ እነርሱም በስደት ወደ ምርኮ ይሄዳሉ በል። በመካከላቸውም የሚኖረው አለቃ በጫንቃው ላይ አንግቶ በጨለማ ይወጣል፥ በዚያ ያወጡ ዘንድ ግንቡን ይነድላሉ፥ በዓይኑም ምድርን እንዳያይ ፊቱን ይሸፍናል። መረቤንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ በወጥመዴም ይያዛል፥ ወደ ከለዳውያንም ምድር ወደ ባቢሎን አመጣዋለሁ፥ ሆኖም አያያትም በዚያም ይሞታል። ሊረዱትም በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ጭፍሮቹንም ሁሉ ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፥ በኋላቸውም ሰይፍ እመዝዛለሁ። በአሕዛብም መካከል በበተንኋቸው ጊዜ፥ በአገሮችም በዘራኋቸው ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። በሚሄዱባቸውም አሕዛብ መካከል ርኵሰታቸውን ሁሉ ይናገሩ ዘንድ ከሰይፍና ከራብ ከቸነፈርም ጥቂቶች ሰዎችን ከእነርሱ አስቀራለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እንጀራህን በድንጋጤ ብላ ውኃህንም በመንቀጥቀጥና በኀዘን ጠጣ፥ ለምድሪቱም ሕዝብ፦ ጌታ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ስለሚኖሩ ስለ እስራኤልም ምድር እንዲህ ይላል፦ ስለሚኖሩባት ሁሉ ግፍ ምድሪቱ ከነሞላዋ ትጠፋ ዘንድ እንጀራቸውን በችግር ይበላሉ ወኃቸውንም በድንጋጤ ይጠጣሉ። ሰዎች የሚኖሩባቸው ከተሞች ባድማ ይሆናሉ ምድሪቱም ውድማ ትሆናለች፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ በላቸው። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ምድር፦ ዘመኑ ረዝሞአል ራእዩም ሁሉ ጠፍቶአል የምትሉት ምሳሌ ምንድር ነው? ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህን ምሳሌ አስቀረዋለሁ በእስራኤልም ዘንድ ደግሞ ምሳሌ አድርገው አይናገሩትም፥ አንተ ግን፦ ዘመኑና የራእዩ ሁሉ ነገር ቀርቦአል በላቸው። ከዚህም በኋላ በእስራኤል ቤት መካከል ከንቱ ራእይና ውሸተኛ ምዋርት አይሆንም። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ እናገራለሁ የምናገረውም ቃል ይፈጸማል፥ ደግሞም አይዘገይም፥ እናንተ ዓመፀኛ ቤት ሆይ፥ በዘመናችሁ ቃሌን እናገራለሁ እፈጽመውማለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ የእስራኤል ቤት፦ ይህች የሚያያት ራእይ ለብዙ ዘመን ናት፥ እርሱም ለሩቅ ወራት ትንቢት ይናገራል ይላሉ። ስለዚህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የምናገረው ቃል ይፈጸማል እንጂ ከቃሌ ሁሉ ደግሞ የሚዘገይ የለም፥ ይላል እግዚአብሔር።
ሕዝቅኤል 12:1-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! አንተ የምትኖረው ዐመፀኞች በሆኑ ሕዝብ መካከል ነው፤ እነርሱ ዐመፀኞች ከመሆናቸው የተነሣ ዐይን እያላቸው አያዩም፤ ጆሮም እያላቸው አይሰሙም። “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ! የስደት ዕቃህን ጠቅልለህ አዘጋጅ፤ እነርሱ እያዩም የስደት ጒዞህን በቀን ጀምር፤ እንደ ስደተኛ ከቦታህ ተነሥተህ ወደ ሌላ ቦታ ሂድ፤ ዐመፀኞች ቢሆኑም እንኳ ያስተውሉ ይሆናል። እንደ ስደተኛ እነርሱ እያዩህ የጒዞ ዕቃህን በቀን ታዘጋጃለህ፤ ስደተኞች እንደሚያደርጉትም እነርሱ እያዩህ ወደ ማታ ጊዜ ወጥተህ ሂድ። በሚመለከቱህም ጊዜ የቤትህን ግድግዳ ሸንቁረህ ቀዳዳ አብጅ፤ ዕቃህንም በዚያ ቀዳዳ አሾልከህ አውጣው፤ የምትሄድበትን ስፍራ እንዳታይ ዕቃህን በትከሻህ ተሸክመህ ፊትህን በመሸፈን በጨለማ ስትሄድ ይመልከቱህ፤ እኔም ለእስራኤላውያን ምልክት አድርጌሃለሁ።” እኔም እግዚአብሔር ያዘዘኝን ሁሉ አደረግሁ፤ በዚያኑ ቀን እንደ ስደተኛ ዕቃዬን ጠቀለልኩ፤ ቀኑም ሲመሽ ግድግዳውን በእጄ ነድዬ ቀዳዳ አበጀሁና በዚያ በኩል ዕቃዬን አወጣሁ፤ ሰዎቹም ሁሉ እያዩኝ የተጠቀለለውን ዕቃዬን በትከሻዬ ላይ አድርጌ በጨለማ ሄድኩ። በማግስቱም ጠዋት እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ! እነዚያ ዐመፀኞች እስራኤላውያን ‘እነሆ ይህ የምታደርገው ነገር ሁሉ ምንድን ነው?’ ብለው አልጠየቁህምን? ስለዚህ እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምለውን ንገራቸው፤ ይህ የትንቢት ቃል በኢየሩሳሌም ላይ ለሚያስተዳድረው መስፍንና እዚያም ለሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ የተነገረ ነው። ይህም አንተ ያደረግኸው ነገር ሁሉ በእነርሱ ላይ ሊፈጸም ለተቃረበው ነገር ምልክት መሆኑን አስታውቃቸው፤ እነርሱም ስደተኞችና ምርኮኞች ይሆናሉ ማለት ነው። እነርሱን የሚያስተዳድረው መስፍን ዕቃውን ጠቅልሎ በትከሻው በመሸከም እነርሱ ግድግዳ ነድለው በሚያወጡለት ቀዳዳ ሾልኮ በጨለማ ይሰደዳል፤ ዐይኑንም ስለሚሸፍን ምድሪቱን አያይም። ነገር ግን እኔ መረቤን ዘርግቼ አጠምደዋለሁ፤ በዐይኑ ሳያያት ወደሚሞትባት ወደ ባቢሎን ከተማ አመጣዋለሁ፤ የቅርብ አማካሪዎቹንና የክብር ዘብ ጠባቂዎቹን ሁሉ በየአቅጣጫው እበትናቸዋለሁ፤ ከኋላቸውም ሆኜ በሰይፍ አሳድዳቸዋለሁ። “በባዕዳን ሕዝቦችና አገሮች መካከል በምበትናቸው ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ፤ ነገር ግን ከእነርሱ ጥቂቶቹን ከጦርነት፥ ከራብና ከቸነፈር እንዲተርፉ አደርጋለሁ፤ በዚህም ዐይነት በሕዝቦች መካከል ሲኖሩ ሥራቸው ምን ያኽል አጸያፊ እንደ ነበር ይገነዘባሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።” እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! በምትበላበት ጊዜ በፍርሃት ብላ፤ በምትጠጣበትም ጊዜ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ ጠጣ፤ በምድሪቱ ለሚኖሩ ሕዝብ ጌታ እግዚአብሔር በእስራኤል ምድር በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሕዝብ እንዲህ ይላል ብለህ ንገራቸው፦ ‘በምድሪቱ በሚኖሩ ሰዎች ዐመፅ ምክንያት ምድሪቱ በጠቅላላ ስለምትራቈት ምግባቸውን የሚበሉት በፍርሃት ነው፤ ውሃቸውንም የሚጠጡት ተስፋ በመቊረጥ ነው። አሁን በሕዝብ ተሞልተው የሚታዩ ከተሞች ይጠፋሉ፤ አገሪቱም ምድረ በዳ ትሆናለች፤ በዚያን ጊዜ እነርሱ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።’ ” እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ራእዩ ሁሉ ተግባራዊ ሳይሆን ቀኖቹ ተራዘሙ ተብሎ ስለ እስራኤል ምድር የሚነገረው ይህ ምሳሌ ምንድን ነው? እኔ ልዑል እግዚአብሔር ስለዚህ ጉዳይ የምለውን ንገራቸው፤ ይህ ምሳሌ እዚሁ ላይ እንዲያበቃ አደርገዋለሁ፤ ዳግመኛም በእስራኤል አይነገርም፤ በዚህ ፈንታ ‘እነሆ ጊዜው ደርሶአል፤ የትንቢቱም ቃል ሁሉ ሊፈጸም ነው!’ ብለህ ንገራቸው። “በእስራኤል ሕዝብ መካከል ሐሰተኛ ራእይ ወይም ሟርት ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አይነገርም። እኔ እግዚአብሔር በቀጥታ እናገራለሁ፤ የምናገረውም ቃል ሁሉ ይፈጸማል፤ ከእንግዲህ ወዲህም ከቶ አይዘገይም፤ እናንተ ዐመፀኞች ‘በእናንተ ላይ አመጣለሁ’ ብዬ በማስጠንቀቅ የተናገርኩትን ሁሉ በሕይወታችሁ ዘመን እንዲፈጸም አደርጋለሁ፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ነኝ።” እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! እስራኤላውያን የአንተ ራእይና ትንቢት ‘ከብዙ ዘመን በኋላ የሚፈጸም ነው’ ብለው ይናገራሉ፤ ስለዚህ እኔ እግዚአብሔር የምላቸውን ንገራቸው፤ እኔ የተናገርኩት ሁሉ ይፈጸማል፤ ከቶም አይዘገይም፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ነኝ።”
ሕዝቅኤል 12:1-28 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በዓመፀኛ ቤት መካከል ተቀምጠሃል፥ እንዲያዩ ዐይን አላቸው ነገር ግን አያዩም፥ እንዲሰሙም ጆሮ አላቸው ነገር ግን አይሰሙም፥ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና። አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የስደተኛ ጓዝ ለራስህ አዘጋጅ፥ እያዩህም በቀን ወደ ምርኮ ሂድ፥ በፊታቸውም እንደ ምርኮኛ ከስፍራህ ወደ ሌላ ስፍራ ሂድ፥ ዓመፀኛ ቤት ቢሆኑም ምናልባት ያስተውሉ ይሆናል። ጓዝህን እንደ ስደተኛ ጓዝ እያዩህ በቀን አውጣው፥ በማታም እያዩህ ስደተኞች እንደሚወጡ እንዲሁ ውጣ። እያዩህም ግንቡን ቦርቡረው፥ በእርሱም አውጣው። ለእስራኤልም ቤት ምልክት አድርጌሃለሁና እያዩህ በትከሻህ ላይ ተሸከመው፥ በጨለማም ይዘኸው ውጣ፥ ምድሪቱንም እንዳታይ ፊትህን ሸፍን። እኔም እንደታዘዝኩት አደረግሁ፥ በቀንም ጓዙን እንደ ስደተኛ ጓዝ አወጣሁ፥ በምሽትም ጊዜ ግንቡን በእጄ ቦረቦርሁት፥ እያዩኝም በትከሻዬ ላይ ተሸክሜ በጨለማ አወጣሁት። በማግስቱም የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት፥ ዓመፀኛ ቤት፦ ምን እያደረግህ ነው? አላሉህምን? እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህ የትንቢት ቃል በኢየሩሳሌም ለሚኖረው መስፍንና በውስጧ ለሚኖሩ ለእስራኤል ቤት ሁሉ ነው። እንዲህም በላቸው፦ እኔ ምልክታችሁ ነኝ፥ እኔ እንዳደረግሁት እንዲሁ ይደረግባቸዋል፥ እነርሱም ወደ ስደት ወደ ምርኮ ይሄዳሉ። በመካከላቸውም ያለው ልዑል በትከሻው ላይ ተሸክሞ በጨለማ ይወጣል፥ በዚያም ሊወጡ ግንቡን ይቦረቡራሉ፥ በዓይኑም ምድሪቱን እንዳያይ ፊቱን ይሸፍናል። መረቤንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ፥ በወጥመዴም ይያዛል፥ ወደ ከለዳውያን ምድር ወደ ባቢሎን አመጣዋለሁ፥ ሆኖም አያያትም በዚያም ይሞታል። በዙሪያው ያሉ ረዳቶቹና ወታደሮቹን ሁሉ ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፥ ከኋላቸውም ሰይፍ እመዝዛለሁ። በአሕዛብ መካከል ስበትናቸው፥ በአገሮችም ስዘራቸው፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። በሚሄዱባቸው አሕዛብ መካከል ርኩሰታቸውን ሁሉ እንዲናገሩ ከእነርሱ ጥቂቶች ከሰይፍ፥ ከራብና ከቸነፈር አስቀራለሁ፥ በዚያን ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ምግብህን በድንጋጤ ብላ፥ ውኃህንም በመንቀጥቀጥና በስጋት ጠጣ፤ ለምድሪቱም ሕዝብ እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር በእስራኤልም ምድር በኢየሩሳሌም ስለሚኖሩት እንዲህ ይላል፦ በሚኖሩባት ሰዎች ሁሉ ግፍ ምድሪቱ ከነሞላዋ ስለምትጠፋ ምግባቸውን በስጋት ይበላሉ ወኃቸውንም በድንጋጤ ይጠጣሉ። ሰዎች የሚኖሩባቸው ከተሞች ይጠፋሉ፥ ምድሪቱም ውድማ ትሆናለች፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ምድር፦ “ቀኖቹ ረዝመዋል፥ ራእይም ሁሉ ጠፍቶአል” የምትሉት ይህ ምሳሌ ምንድነው? ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህን ምሳሌ አስቀረዋለሁ በእስራኤልም ዘንድ ደግሞ ምሳሌ አድርገው አይናገሩትም፥ አንተ ግን፦ ዘመኑና የራእዩ ሁሉ ነገር ቀርቧል በላቸው። ከዚህም በኋላ በእስራኤል ቤት መካከል ከንቱ ራእይና ውሸተኛ ምዋርት አይሆንም። ነገር ግን እኔ ጌታ የምናገረውን ቃል እናገራለሁ፥ ይፈጸማልም፥ ደግሞም አይዘገይም፥ እናንተ ዓመፀኛ ቤት ሆይ፥ በዘመናችሁ ቃሌን እናገራለሁ እፈጽመዋለሁም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ የእስራኤል ቤት እንዲህ ይላሉ፦ የሚያየው ራእይ ለብዙ ዘመን ነው፥ እርሱም ለሩቅ ወራት ትንቢት ይናገራል። ስለዚህም እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የምናገረው ቃል ይፈጸማል እንጂ ከቃሌ ሁሉ ደግሞ የሚዘገይ የለም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።