ዘፀአት 6:1-12
ዘፀአት 6:1-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “በጸናች እጅ ይለቅቃቸዋልና፥ በተዘረጋችም ክንድ ከምድሩ አስወጥቶ ይሰድዳቸዋልና አሁን በፈርዖን የማደርገውን ታያለህ።” እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው አለውም፥ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ። ለአብርሃምም፥ ለይስሐቅም፥ ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ፤ ነገር ግን ስሜ እግዚአብሔር አልታወቀላቸውም ነበር። የነበሩባትንም የከነዓንን ምድር እሰጣቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳኔን አቆምሁ። ደግሞ እኔ ግብፃውያን የገዙአቸውን የእስራኤልን ልጆች ልቅሶ ሰማሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አሰብሁ።” ስለዚህም ፈጥነህ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፥ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከግብፃውያንም ተገዥነት አወጣችኋለሁ፤ ከባርነታቸውም አድናችኋለሁ፤ በተዘረጋ ክንድ፤ በታላቅ ፍርድም እታደጋችኋለሁ፤ ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ፤ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብፃውያን ባርነት ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። ለአብርሃምና ለይስሐቅ፥ ለያዕቆብም እሰጣት ዘንድ እጄን ወደ ዘረጋሁባት ምድር አገባችኋለሁ፤ እርስዋንም ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” ሙሴም ይህን ለእስራኤል ልጆች ተናገረ፤ እነርሱ ግን ከሰውነታቸው መጨነቅ፥ ከሥራቸውም ክብደት የተነሣ ቃሉን አልሰሙትም። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ግባ፤ የእስራኤልን ልጆች ከሀገሩ ይለቅቅ ዘንድ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን ንገረው።” ሙሴም በእግዚአብሔር ፊት፥ “እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች አልሰሙኝም፤ እንዴትስ ፈርዖን ይሰማኛል? እኔም አንደበተ ርቱዕ አይደለሁም” ብሎ ተናገረ።
ዘፀአት 6:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “አሁን በፈርዖን ላይ የማደርገውን ታያለህ፤ ከኀያሉ እጄ የተነሣ እንዲሄዱ ይለቅቃቸዋል፤ ከኀያሉም እጄ የተነሣ ከአገሩ ያስወጣቸዋል” አለው። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ። ሁሉን ቻይ አምላክ ሆኜ ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅ፣ ለያዕቆብ ተገለጥሁላቸው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በተባለው ስሜ ራሴን አልገለጥሁላቸውም። በእንግድነት የሚኖሩባትን የከነዓንን ምድር እንድሰጣቸው ከእነርሱ ጋራ ቃል ኪዳን ገብቻለሁ። ደግሞም በግብጻውያን ሥር በባርነት ሆነው ያሰሙትን የእስራኤላውያንን የሥቃይ ድምፅ ሰምቻለሁ ኪዳኔንም አስታውሻለሁ። “ስለዚህ ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከግብጻውያን ቀንበር አወጣችኋለሁ። ለእነርሱ ባሪያ ከመሆን ነጻ አወጣችኋለሁ፤ በተዘረጋች ክንድና በታላቅ ፍርድ እቤዣችኋለሁ። የራሴ ሕዝብ አደርጋችኋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ ከግብጻውያን ቀንበር ያላቀቅኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላክ መሆኔንም ታውቃላችሁ። ከዚያም ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅ፣ ለያዕቆብ እሰጣችኋለሁ ብዬ ወደ ማልሁላቸው ምድር አመጣችኋለሁ፤ ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ” ሙሴ ይህን ለእስራኤላውያን ነገራቸው፤ ተስፋ ከመቍረጣቸውና ከአስከፊ እስራታቸው የተነሣ ግን አላደመጡትም። ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ሂድና ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖን እስራኤላውያን ከአገሩ እንዲወጡ ይፈቅድላቸው ዘንድ ንገረው።” ሙሴ ግን እግዚአብሔርን፣ “እስራኤላውያን ያልሰሙኝ፣ ፈርዖን እንዴት ይሰማኛል፤ እኔ ለራሴ ተብታባ ሰው ነኝ” አለው።
ዘፀአት 6:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ “በጸናች እጅ ይለቅቃቸዋልና፥ በጸናችም እጅ ከምድሩ አስወጥቶ ይሰድዳቸዋልና አሁን በፈርዖን የማደርገውን ታያለህ።” እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው፤ አለውም፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ለአብርሃምም ለይስሐቅም ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ፤ ነገር ግን ስሜ እግዚአብሔር አልታወቀላቸውም ነበር። የተሰደዱባትንም ምድር፥ የእንግድነታቸውን የከነዓንን ምድር፥ እሰጣቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳኔን አቆምሁ። ደግሞ እኔ ግብፃውያን የገዙአቸውን የእስራኤልን ልጆች ልቅሶ ሰማሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አሰብሁ። ስለዚህም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፦ ‘እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከግብፃውያን ባርነት አወጣችኋለሁ፥ ከተገዥነታችሁም አድናችኋለሁ፤ በተዘረጋ ክንድ በታላቅ ፍርድም እታደጋችኋለሁ፤ ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ፤ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብፃውያን ባርነት ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እሰጣት ዘንድ ወደ ማልሁባት ምድር አገባችኋለሁ፤ እርስዋንም ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ’”። ሙሴም ይህን ለእስራኤል ልጆች ተናገረ፤ እነርሱ ግን ከሰውነታቸው መጨነቅ ከከባዱም ሥራ የተነሣ ቃሉን አልሰሙትም። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፤ “ግባ፤ የእስራኤልንም ልጆች ከአገሩ ይለቅቅ ዘንድ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን ንገር”። ሙሴም በእግዚአብሔር ፊት፥ “እነሆ የእስራኤል ልጆች አልሰሙኝም፤ እንዴትስ ፈርዖን ይሰማኛል? ይልቁንም እኔ ከንፈረ ቈላፍ ነኝ” ብሎ ተናገረ።
ዘፀአት 6:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔርም ሙሴን “በንጉሡ በፈርዖን ላይ የማደርገውን አሁን ታያለህ፤ በኀይሌ ተገዶ ሕዝቤን ይለቃል፤ በኀያል ክንዴም ተሸንፎ ያባርራቸዋል።” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ሁሉን የምችል አምላክ (ኤልሻዳይ) መሆኔን በማስረዳት ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ተገልጬላቸዋለሁ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) በተሰኘው ቅዱስ ስሜ አማካይነት ግን አልተገለጥኩላቸውም። እንደ ስደተኞች ሆነው የሚኖሩባትን የከነዓንን ምድር ላወርሳቸው ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ። እነሆ፥ አሁንም ግብጻውያን ባርያዎች አድርገው የሚያስጨንቁአቸውን የእስራኤላውያንን መራራ ጩኸት ሰምቼአለሁ፤ የገባሁትንም ቃል ኪዳን አስታውሼአለሁ። ስለዚህም ለእስራኤላውያን የምለውን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ግብጻውያን ከሚያደርሱባችሁ የባርነት ጭቈና በማዳን ነጻ አወጣችኋለሁ፤ አሠቃቂ ቅጣት አመጣባቸው ዘንድ የኀይል ክንዴን በእነርሱ ላይ አነሣለሁ፤ እናንተንም እታደጋችኋለሁ፤ የእኔ ሕዝብ አደርጋችኋለሁ፤ እኔም አምላካችሁ እሆናለሁ፤ ከግብጽ ባርነትም ነጻ በማወጣችሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ መሆኔን ታውቃላችሁ፤ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ አወርሳቸው ዘንድ በመሐላ ቃል ኪዳን ወደገባሁባት ምድር አመጣችኋለሁ፤ ርስትም አድርጌ አወርሳችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ” ሙሴም ይህን ሁሉ ለእስራኤላውያን ነገረ፤ እነርሱ ግን በወደቀባቸው ጨካኝ ጭቈና ምክንያት መንፈሳቸው ተሰብሮ ስለ ነበረ ሊያዳምጡት አልፈለጉም። እንደገናም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ወደ ግብጽ ንጉሥ ሄደህ እስራኤላውያንን ከአገርህ እንዲወጡ ልቀቃቸው ብለህ ንገረው።” ነገር ግን ሙሴ “ወገኖቼ እስራኤላውያን እንኳ አልሰሙኝም፤ ታዲያ፥ ንጉሡ እንዴት ሊሰማኝ ይችላል? እንደምታየኝ እኔ ኰልታፋ ነኝ” ሲል መለሰ።
ዘፀአት 6:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም ሙሴን አለው፦ “አሁን ፈርዖንን ምን እንደማደርገው ታያለህ በጸናች እጅ ይለቅቃቸዋል፥ በጸናችም እጅ ከምድሩ አስወጥቶ ይሰድዳቸዋል።” እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው አለውም፦ “እኔ ጌታ ነኝ፤ ለአብርሃም ለይስሐቅ ለያዕቆብም ሁሉን የሚችል አምላክ ሆኜ ተገለጥኩላቸው፤ ጌታ የሚለውን ስሜን ግን አላስታወቅኳቸውም። ደግሞም የከነዓንን ምድር፥ በእንግድነት ተቀምጠውበት የነበረውን የእንግድነታቸው ምድር እሰጣቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳኔን መሰረትኩ። ደግሞም እኔ ግብፃውያን እንዲሰሩ የሚያስገድዷቸውን የእስራኤልን ልጆች ጩኸት ሰማሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አሰብሁ። ስለዚህም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፦ ‘እኔ ጌታ ነኝ፥ ከግብፃውያን ጭቆና አወጣችኋለሁ፥ ከተገዥነታችሁም አላቅቃችኋለሁ፤ በተዘረጋች ክንድ በታላቅ የፍርድ ሥራም አድናችኋለሁ፤ ለእኔ ሕዝብ አድርጌ እቀበላችኋለሁ፥ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብጽ ጭቆና ያወጣኋችሁ ጌታ አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። ለአብርሃም ለይስሐቅና ለያዕቆብ እሰጣታለሁ ብዬ እጄን ወደ አነሳሁባት ምድር አመጣችኋለሁ፤ እርሷንም ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ ጌታ ነኝ።’” ሙሴም ይህን ለእስራኤል ልጆች ተናገረ፤ እነርሱ ግን ከመንፈሳቸው መሰበር ከከባዱም ሥራ የተነሣ ሙሴን አልሰሙትም። ጌታም ሙሴን አለው፦ “ግባ፥ የግብጽን ንጉሥ ፈርዖንን የእስራኤልን ልጆች ከምድሩ እንዲለቅ ንገረው።” ሙሴም በጌታ ፊት፦ “እነሆ የእስራኤል ልጆች አልሰሙኝም፤ ታድያ እንዴት ፈርዖን ይሰማኛል? እኔ ደግሞ ከንፈሬ ያልተገረዘ ሰው ነኝ” ብሎ ተናገረ።