ዘፀአት 33:19-23
ዘፀአት 33:19-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም፥ “እኔ በክብሬ በፊትህ አልፋለሁ፤ የእግዚአብሔርንም ስም በፊትህ እጠራለሁ፤ ይቅርም የምለውን ይቅር እላለሁ፤ የምምረውንም እምራለሁ” አለ። እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም” አለ። እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “እነሆ፥ ስፍራ በእኔ ዘንድ አለ፥ በዐለቱም ላይ ትቆማለህ፤ ክብሬም በአለፈ ጊዜ በአለቱ ስንጥቅ ውስጥ አኖርሃለሁ፤ እስከ አልፍም ድረስ እጄን በላይህ እጋርዳለሁ፤ እጄንም ፈቀቅ አደርጋለሁ፤ በዚያ ጊዜ ጀርባዬን ታያለህ፤ ፊቴ ግን ለአንተ አይታይም።”
ዘፀአት 33:19-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “መልካምነቴ ሁሉ በፊትህ እንዲያልፍ አደርጋለሁ፤ በፊትህም ስሜን እግዚአብሔርን ዐውጃለሁ፤ የምምረውን እምረዋለሁ፤ የምራራለትንም ራራለታለሁ፤ ነገር ግን፣ ማንም እኔን አይቶ መኖር ስለማይችል፣ ፊቴን ማየት አትችልም።” ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “በአጠገቤ ስፍራ አለ፤ አንተም በዐለት ላይ ትቆማለህ፤ ክብሬ በዚያ ሲያልፍ በዐለቱ ስንጥቅ ውስጥ አደርግሃለሁ፤ በዚያም እስከማልፍ ድረስ በእጄ እጋርድሃለሁ፤ ከዚያም እጄን አነሣለሁ፤ ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን መታየት የለበትም።”
ዘፀአት 33:19-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም፦ እኔ መልካምነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ፤ የእግዚአብሔርንም ስም በፊትህ አውጃለሁ፤ ይቅርም የምለውን ይቅር እላለሁ፥ የምምረውንም እምራለሁ አለ። ደግሞም፦ ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም አለ። እግዚአብሔርም አለ፦ እነሆ ስፍራ በእኔ ዘንድ አለ፥ በዓለቱም ላይ ትቆማለህ፤ ክብሬም ባለፈ ጊዜ በሰንጣቃው ዓለት አኖርሃለሁ፥ እስካልፍ ድረስ እጄን በላይህ እጋርዳለሁ፤ እጄንም ፈቀቅ አደርጋለሁ፥ ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም።
ዘፀአት 33:19-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ደግነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ስሜን በፊትህ ዐውጃለሁ፤ የምምረውን እምራለሁ፤ የምራራለትንም እራራለታለሁ፤ ፊቴን አይቶ ለመኖር የሚችል ሰው ስለሌለ ፊቴን ለማየት አትችልም። ነገር ግን እዚህ በአጠገቤ በአለት ላይ የምትቆምበት ስፍራ አለ። የእኔ ክብር በዚያ ሲያልፍ በአለቱ ስንጣቂ አቈይሃለሁ፤ እስካልፍ ድረስ በእጄ እጋርድሃለሁ፤ ከዚያም በኋላ እጄን አነሣለሁ፤ አንተም ፊቴን ሳይሆን ጀርባዬን ታያለህ።”
ዘፀአት 33:19-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እርሱም እንዲህ አለው፦ “እኔ መልካምነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ የጌታንም ስም በፊትህ አውጃለሁ፤ ይቅር የምለውን ይቅር እላለሁ፥ የምምረውን እምራለሁ።” ደግሞም “ሰው አይቶኝ መኖር አይችልምና ፊቴን ማየት አትችልም” አለ። ጌታ እንዲህ አለው፦ “እነሆ የምትቆምበት ስፍራ በአጠገቤ አለ፥ በዓለቱ ላይ ትቆማለህ፤ ክብሬ ሲያልፍ ዓለቱ ስንጥቅ ውስጥ አስቀምጥሃለሁ፥ እስካልፍ ድረስ በመዳፌ እጋርዳለሁ፤ መዳፌን አነሣለሁ፥ ጀርባዬን ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም።”