ዘፀአት 3:16-17
ዘፀአት 3:16-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሂድ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች ሰብስብ፤ እንዲህም በላቸው፦ የአባቶቻችሁ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተገለጠልኝ፦ መጐብኘትን ጐበኘኋችሁ፤ በግብፅም የሚደረግባችሁን አየሁ፤ እንዲህም አልሁ፦ ከግብፅ መከራ ወደ ከነዓናውያን፥ ወደ ኬጤዎናውያን፥ ወደ አሞሬዎናውያን፥ ወደ ፌርዜዎናውያን፥ ወደ ጌርጌሴዎናውያን፥ ወደ ኤዌዎናውያን፥ ወደ ኢያቡሴዎናውያን ሀገር፥ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ሀገር አወጣችኋለሁ፤
ዘፀአት 3:16-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ሂድና የእስራኤልን አለቆች ሰብስበህ፣ ‘የአባቶቻችሁ የአብርሃም፣ የይሥሐቅና የያዕቆብ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ተገለጠልኝና እንዲህ አለኝ፤ ጐብኝቻችኋለሁ፤ በግብጽ የደረሰባችሁንም አይቻለሁ። ስለዚህም በግብጽ ከምትቀበሉት መከራ አውጥቼ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ አሞራውያን፣ ወደ ፌርዛውያን፣ ወደ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር አገባችኋለሁ’ ብሏል ብለህ ንገራቸው” አለኝ።
ዘፀአት 3:16-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሂድ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች ሰብስብ፦ ‘እግዚአብሔር የአባቶቻችሁ አምላክ የአብርሃም የይስሐቅም የያዕቆብም አምላክ፦ መጎብኘትን ጎበኘኋችሁ፤ በግብፅም የሚደረግባችሁን አየሁ፤ ከግብፅም መከራ ወደ ከነዓናውያን ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ያቡሳውያንም አገር ወተትና ማር ወደምታፈስስ አገር አወጣችኋለሁ፤ አልሁ ብሎ ተገለጠልኝ፤’ በላቸው።
ዘፀአት 3:16-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንግዲህ ሂድና የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች ሁሉ በአንድነት ሰብስብ፤ የቀድሞ አባቶቻቸው የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ እኔ እግዚአብሔር የተገለጥኩልህ መሆኔንም ንገራቸው፤ ወደ እነርሱ ወርጄ ግብጻውያን በእነርሱ ላይ ያደረሱባቸውን ግፍና ጭቈና መመልከቴን ንገራቸው። በግፍ ጭቈና ከሚሠቃዩባት ከግብጽ ምድር አውጥቼ እነሆ ዛሬ፥ ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን የሚኖሩባትን፥ በማርና በወተት የበለጸገች ሰፊና ለም የሆነች ምድር ልሰጣቸው ቃል ገብቻለሁ።
ዘፀአት 3:16-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሂድ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች ትሰበስባለህ እንዲህም ትላቸዋለህ፦ “ጌታ የአባቶቻችሁ አምላክ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅ፥ የያዕቆብም ተገለጠልኝ፤ እንዲህም አለኝ ‘ጎበኘኋችሁ፥ በግብጽም የሚደረግባችሁን አየሁ፤ ከግብጽም መከራ ወደ ከነዓናውያን ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም አገር ወተትና ማር ወደምታፈስስ አገር አወጣችኋለሁ።’