ዘፀአት 27:1-8
ዘፀአት 27:1-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱም አምስት ክንድ መሠዊያን ከማይነቅዝ ዕንጨት አድርግ፤ አራት ማዕዘንም ይሁን፤ ከፍታውም ሦስት ክንድ ይሁን። በአራቱም ማዕዘን ቀንዶችን ታደርጋለህ፤ ቀንዶቹ ሥረ-ወጥ ይሁኑ፤ በናስም ለብጣቸው። ለመሠዊያው ክዳን ሥራለት፤ መሸፈኛውን፥ ጽዋዎቹን፥ የሥጋ ሜንጦዎቹን፥ የእሳት መጫሪያዎቹንም አድርግ። ዕቃውንም ሁሉ ከናስ አድርግ። ለመሠዊያውም እንደ መረብ ሆኖ የተሠራ የናስ መከታ አድርግለት፤ ለመከታውም አራት የናስ ቀለበት በአራት ማዕዘኑ አድርግለት። መከታውም እስከ መሠዊያው እኩሌታ ይደርስ ዘንድ ከመሠዊያው እርከን በታች አኑረው። ለመሠዊያውም ከማይነቅዝ ዕንጨት መሎጊያዎችን ሠርተህ በናስ ለብጣቸው፤ መሎጊያዎቹም በቀለበቶች ውስጥ ይግቡ፤ መሠዊያውንም ስትሸከሙ መሎጊያዎቹ በመሠዊያው በሁለት ወገን ይሁኑ። ሰሌዳውም ፍልፍል ይሁን፤ በተራራው እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንዲሁ አድርግ።
ዘፀአት 27:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ከፍታው ሦስት ክንድ የሆነ መሠዊያ ከግራር ዕንጨት ሥራ፤ ርዝመቱ ዐምስት፣ ወርዱም ዐምስት ክንድ ሆኖ ባለአራት ማእዘን ይሁን። ቀንዶቹና መሠዊያው አንድ ወጥ ይሆኑ ዘንድ በአራቱም ማእዘኖች ላይ ቀንድ አድርግለት፤ መሠዊያውንም በንሓስ ለብጠው። ዕቃዎቹን ሁሉ ይኸውም የዐመድ ማስወገጃ ምንቸቶችን፣ መጫሪያዎችን፣ ጐድጓዳ ሳሕኖችን፣ ሜንጦዎችንና የፍም መያዣዎችን ከንሓስ አብጃቸው። ዐመድ ማውረጃ የሚሆን እንደ መረብ የሆነ የንሓስ ፍርግርግ አድርግለት በአራቱም የመረብ ማእዘኖች ላይ የንሓስ ቀለበቶች አብጅ። እስከ መሠዊያው ወገብ እንዲደርስ በመሠዊያው ዙሪያ ባለው እርከን ሥር አድርገው። የግራር ዕንጨት መሎጊያዎችን ለመሠዊያው ሠርተህ በንሓስ ለብጣቸው። በሸክም ጊዜ በመሠዊያው ሁለቱም ጐኖች እንዲሆኑ፣ መሎጊያዎቹ በቀለበቶቹ ውስጥ ይግቡ። መሠዊያውን ውስጡን ባዶ ከሆኑ ሳንቃዎች አብጀው፤ ልክ በተራራው ላይ ባየኸው መሠረት ይበጅ።
ዘፀአት 27:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱም አምስት ክንድ መሠዊያ ከግራር እንጨት አድርግ፤ አራት ማዕዘንም ይሁን፤ ከፍታውም ሦስት ክንድ ይሁን። በአራቱም ማዕዘን ቀንዶችን ታደርጋለህ፥ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድ የተሠሩ ይሁኑ፤ በናስም ለብጠው። አመድ የሚሆንባቸውን ምንቸቶች፥ መጫሪያዎቹንም፥ ድስቶቹንም፥ ሜንጦቹንም፥ ማንደጃዎቹንም አድርግ፤ ዕቃውንም ሁሉ ከናስ አድርግ። እንደ መረብ ሆኖ የተሠራ የናስ መከታ አድርግለት፤ ለመከታውም አራት የናስ ቀለበት በአራት ማዕዘኑ አድርግለት። መከታውም እስከ መሠዊያው እኵሌታ ይደርስ ዘንድ መሰዊያው በሚዞረው በእርከኑ ታች አድርገው። ለመሠዊያውም ከግራር እንጨት መሎጊያዎችን ሠርተህ በናስ ለብጣቸው። መሎጊያዎቹም በቀለበቶች ውስጥ ይግቡ፤ መሠዊያውንም ስትሸከሙ መሎጊያዎቹ በሁለቱ ወገኖች ይሁኑ። ከሳንቆች ሠርተህ ባዶ አድርገው፤ በተራራው እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንዲሁ ያድርጉት።
ዘፀአት 27:1-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ከግራር እንጨት መሠዊያ ሥራ፤ ርዝመቱ ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር የጐኑ ስፋት ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ቁመቱም አንድ ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር ይሁን። በአራቱም ማእዘን ጫፍ ላይ ጠርበህ ቀንድ መሳይ ጒጦች አውጣ፤ ይህም ከመሠዊያው ጋር አብሮ የተሠራ ይሁን፤ እርሱም በነሐስ የተለበጠ ይሁን። ዐመድ የሚጠራቀምባቸውን ድስቶችን፥ የእሳት መጫሪያዎችን፥ ጐድጓዳ ሳሕኖችን፥ ሜንጦዎችንና ማንደጃዎችን አዘጋጅ፤ ሁሉም ከነሐስ የተሠሩ ይሁኑ። እንደ መረብ ሆኖ የተሠራ የነሐስ መከላከያ አብጅለት፤ ለመከላከያውም አራት የነሐስ ቀለበቶች በአራቱም ማእዘን አድርግለት። መከላከያም እስከ መሠዊያው እኩሌታ እንዲደርስ ከመሠዊያው ክፈፍ በታች አድርገው፤ ለመሠዊያው መሸከሚያ የሚሆኑ መሎጊያዎችንም ከግራር እንጨት ሠርተህ በነሐስ ለብጣቸው። መሠዊያውን መሸከም በሚያስፈልግበትም ጊዜ መሎጊያዎቹን ከመሠዊያው በእያንዳንዱ ጐን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ አግባ። በተራራው ላይ ባሳየሁህ ዕቅድ መሠረት መሠዊያውን ከሳንቃዎች ሥራ፤ ውስጡም ባዶ ይሁን።
ዘፀአት 27:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱ አምስት ክንድ የሆነ መሠዊያ ከግራር እንጨት ሥራ፤ መሠዊያው አራት ማዕዘን ይሁን፤ ከፍታው ሦስት ክንድ ይሁን። በአራቱም ማዕዘን ቀንዶችን አድርግለት፥ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር ወጥ ሆነው የተሠሩ ይሁኑ፤ በነሐስም ለብጠው። አመድ የሚጠራቀምባቸውን ምንቸቶች፥ መጫሪያዎቹን፥ ድስቶቹን፥ ሜንጦቹንና ማንደጃዎቹን ታደርጋለህ፤ ዕቃዎቹ ሁሉ ከነሐስ ሥራ። እንደ መረብ ሆኖ የተሠራ የነሐስ መከታ አድርግለት፤ ለመከታውም አራት የነሐስ ቀለበት በአራቱም ማዕዘን አድርግለት። መከታውም እስከ መሠዊያው እኩሌታ እንዲደርስ ከመሠዊያው እርከን በታች አድርገው። ለመሠዊያው ከግራር እንጨት መሎጊያዎችን ሥራ፥ በነሐስም ለብጣቸው። መሎጊያዎቹ በቀለበቶቹ ውስጥ ይግቡ፥ መሠዊያውን ለመሸከም መሎጊያዎቹ በሁለቱ ጎኖች ይሁኑ። ከሳንቃዎች ሠርተህ ባዶ አድርገው፤ በተራራው እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንዲሁ ይሥሩት።