ዘፀአት 24:1-4
ዘፀአት 24:1-4 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “አንተ፥ አሮንም፥ ናዳብም፥ አብዩድም፥ ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወደ እግዚአብሔር ውጡ፤ በሩቁም ለእግዚአብሔር ስገዱ፤ ሙሴም ብቻውን ወደ እግዚአብሔር ይቅረብ፤ እነርሱ ግን አይቅረቡ፤ ሕዝቡም ከእነርሱ ጋር አይውጡ።” ሙሴም ገባ፤ ለሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃሎች ሁሉ፥ ሥርዐቱንም ሁሉ ነገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ድምፅ፥ “እግዚአብሔር የተናገራቸውን ቃሎች ሁሉ እንሰማለን፤ እናደርጋለንም” ብለው መለሱ። ሙሴም የእግዚአብሔርን ቃሎች ጻፈ፤ ማለዳም ተነሣ፤ ከተራራውም በታች መሠዊያን ሠራ፤ ዐሥራ ሁለትም ድንጋዮችን ለዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ አቆመ።
ዘፀአት 24:1-4 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም ሙሴን “አንተና አሮን፣ ናዳብና አብዩድ ከሰባዎቹ የእስራኤል አለቆች ጋራ ወደ እግዚአብሔር ኑ፤ ከሩቅም ስገዱ አለው፤ ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ የሚችለው ሙሴ ብቻ ነው። ሌሎቹ መቅረብ የለባቸውም፤ ሕዝቡም ከርሱ ጋራ መምጣት የለበትም።” ሙሴ ወደ ሕዝቡ ሄዶ የእግዚአብሔርን ቃሎችና ሕጎች ሁሉ በነገራቸው ጊዜ በአንድ ድምፅ ሆነው፣ “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” አሉ። ከዚያም ሙሴ እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ ጻፈ። በማግስቱም ማልዶ ተነሥቶ፣ በተራራው ግርጌ መሠዊያን ሠራ፤ ዐሥራ ሁለቱን የእስራኤልን ነገዶች የሚወክሉ ዐሥራ ሁለት የድንጋይ ዐምዶችን አቆመ።
ዘፀአት 24:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሙሴንም፦ አንተ አሮንም ናዳብም አብዩድም ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወደ እግዚአብሔር ውጡ፥ በሩቁም ስገዱ፤ ሙሴም ብቻውን ወደ እግዚአብሔር ይቅረብ፥ እነርሱ ግን አይቅረቡ፤ ሕዝቡም ከእርሱ ጋር አይውጡ አለው። ሙሴም መጣ ለሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃሎች ሁሉ ሥርዓቱንም ሁሉ ነገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ድምፅ፦ እግዚአብሔር የተናገራቸውን ቃሎች ሁሉ እናደርጋለን ብለው መለሱ። ሙሴም የእግዚአብሔርን ቃሎች ጻፈ ማለዳም ተነሣ፥ ከተራራውም በታች መሠዊያን፥ አሥራ ሁለትም ሐውልቶች ለአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ሠራ።
ዘፀአት 24:1-4 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አንተ ራስህ፥ አሮን፥ ናዳብ፥ አቢሁና ከእስራኤል መሪዎች ሰባ የሚሆኑት ጭምር እኔ ወዳለሁበት ተራራ ውጡ፤ በሩቅ ሳላችሁም ተንበርክካችሁ ስገዱ፤ ሙሴ ብቻ ወደ እኔ ይቅረብ፤ እነርሱ ግን አይቅረቡ፤ ሕዝቡም ከአንተ ጋር አይውጣ።” ሙሴም ሄዶ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና ሥርዓት ሁሉ ለሕዝቡ ነገረ፤ ሕዝቡም በአንድነት “እግዚአብሔር የተናገረውን ሁሉ እናደርጋለን” ሲል መለሰ። ሙሴም የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ሁሉ ጻፈ፤ በማግስቱም ጠዋት በማለዳ በተራራው ሥር መሠዊያ ሠራ፤ ለእያንዳንዱም የእስራኤል ነገድ አንድ የድንጋይ ዐምድ አኖረ፤
ዘፀአት 24:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሙሴንም እንዲህ አለው፦ “አንተ፥ አሮን፥ ናዳብ፥ አቢሁና ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወደ ጌታ ውጡ፥ በሩቁም ስገዱ፤ ሙሴም ብቻውን ወደ ጌታ ይቅረብ፤ እነርሱ ግን አይቅረቡ፥ ሕዝቡም ከእርሱ ጋር አይውጡ።” ሙሴም መጣ ለሕዝቡም የጌታ ቃሎች ሁሉ ሥርዓቱንም ሁሉ ነገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ድምፅ፦ “ጌታ የተናገራቸውን ቃሎች ሁሉ እናደርጋለን” ብለው መለሱ። ሙሴም የጌታን ቃሎች ሁሉ ጻፈ፤ በማለዳ ተነሥቶ ከተራራው በታች መሠዊያንና ዐሥራ ሁለት ሐውልቶች ለዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ሠራ።