ዘፀአት 20:18-26
ዘፀአት 20:18-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሕዝቡም ሁሉ ነጐድጓዱንና መብረቁን፥ የቀንደ መለከቱን ድምፅ፥ ተራራውንም ሲጤስ አዩ፤ ሕዝቡም ሁሉ ፈርተው ርቀው ቆሙ። ሙሴንም፥ “አንተ ከእኛ ጋር ተናገር፤ ነገር ግን እንዳንሞት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር አይናገር” አሉት። ሙሴም ለሕዝቡ፥ “እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ፥ ኀጢአትንም እንዳትሠሩ እርሱን መፍራት በእናንተ ያድር ዘንድ መጥቶአልና አትፍሩ” አላቸው። ሕዝቡም ርቀው ቆሙ፤ ሙሴም እግዚአብሔር ወዳለበት ወደ ጨለማው ቀረበ። እግዚአብሔር ሙሴን አለው፥ “ለያዕቆብ ቤት ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ በል፦ እኔ ከሰማይ እንደ ተናገርኋችሁ እናንተ አይታችኋል። የብር አማልክትን አታምልኩ፤ የወርቅ አማልክትንም አታምልኩ። የዕንጨትና የድንጋይ አምላክንም አታምልኩ፤ እንዲህ ያለ አምላክን ለእናንተ አታድርጉ። ከአፈርም መሠዊያ ሥራልኝ፤ የሚቃጠለውንና የደኅንነት መሥዋዕትህን፥ በጎችህንም፥ በሬዎችህንም ሠዋበት፤ ስሜን ባስጠራሁበት ስፍራ ሁሉ ወደ አንተ መጥቼ እባርክሃለሁ። የድንጋይም መሠዊያ ብታደርግልኝ ጠርበህ አትሥራው፤ በመሣሪያ ብትነካው ታረክሰዋለህና። ኀፍረተ ሥጋህ በእርሱ እንዳይገለጥ ወደ መሠዊያዬ በደረጃ አትውጣ።
ዘፀአት 20:18-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሕዝቡም መብረቁንና ነጐድጓዱን የተራራውን መጤስና የመለከቱን ድምፅ ባዩና በሰሙ ጊዜ በፍርሀት ተንቀጠቀጡ፤ በርቀትም ቆሙ፤ ሙሴን፣ “አንተ ራስህ ተናገረን፤ እኛም እናደምጥሃለን፤ እግዚአብሔር እንዲናገረን አታድርግ፤ አለዚያ መሞታችን ነው” አሉት። ሙሴም ለሕዝቡ፣ “አትፍሩ፤ ኀጢአት እንዳትሠሩ የእግዚአብሔር ፍርሀት ከእናንተ ጋራ ይሆን ዘንድ፣ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ መጥቷል” አላቸው። እግዚአብሔር ወዳለበት ጥቅጥቅ ወደ ሆነው ጨለማ ሙሴ ቀርቦ ሳለ፣ ሕዝቡ በርቀት ቆመው ነበር። ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “ለእስራኤላውያን ይህን ንገራቸው፤ ‘ከሰማይ ሆኜ እንደ ተናገርኋችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል፤ ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሯችሁ፤ ከብር ወይም ከወርቅ ለእናንተ አማልክትን አታብጁ። “ ‘የጭቃ መሠዊያን ሥራልኝ፤ በርሱም ላይ የሚቃጠልና የኅብረት መሥዋዕትን ከበጎችህ፣ ከፍየሎችህና ከቀንድ ከብቶችህ ሠዋልኝ፤ ስሜ እንዲከበር በማደርግበት ቦታ ሁሉ ወደ አንተ እመጣና እባርክሃለሁ። ከድንጋይ መሠዊያ የምትሠራልኝ ከሆነ፣ ከጥርብ ድንጋይ አትሥራ፤ መሣሪያ የነካው ከሆነ ታረክሰዋለህና። ወደ መሠዊያዬም በደረጃ አትውጣ፤ አለዚያ ኀፍረተ ሥጋህ ይገለጣል።’
ዘፀአት 20:18-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሕዝቡም ሁሉ ነጎድጓዱንና መብረቁን፥ የቀንደ መለከቱን ድምፅ፥ ተራራውንም ሲጤስ አዩ፤ ሕዝቡም ባዩ ጊዜ ተርበደበዱ፥ ርቀውም ቆሙ። ሙሴንም፦ አንተ ተናገረን እኛም እንሰማለን፤ እንዳንሞት ግን እግዚአብሔር አይናገረን አሉት። ሙሴም ለሕዝቡ፦ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ፥ ኃጢያትንም እንዳትሠሩ እርሱን መፍራት በልባችሁ ይሆን ዘንድ መጥአልና አትፍሩ አለ። ሕዝቡም ርቀው ቆሙ፥ ሙሴም እግዚአብሔር ወዳለበት ወደ ጨለማው ቀረበ። እግዚአብሔር ሙሴን አለው፦ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በል፦ እኔ ከሰማይ እንደ ተናገርኋችሁ እናንተ አይታችኋል። በአጠገቤ ምንም አታድርጉ፤ የብር አማልክት የወርቅም አማልክት ለእናንተ አታድርጉ። የጭቃ መሰዊያ ሥራልኝ፥ የሚቃጠለውንና የደኅንነት መሥዋዕትህን በጎችህንም በሬዎችህንም ሠዋበት፤ ስሜን በማሳስብበት ስፍራ ሁሉ ወደ አንተ መጥቼ እባርክሃለሁ። የድንጋይም መሠዊያ ብታደርግልኝ ብረት በነካው ድንጋይ አትሥራው፤ በመሣሪያ ብትነካው ታረክሰዋለህና። ኃፍረተ ሥጋህ በእርሱ እንዳይገለጥ ወደ መሠዊያዬ በደረጃ አትውጣ።
ዘፀአት 20:18-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሕዝቡም የነጐድጓዱንና የእምቢልታውን ድምፅ በሰሙ ጊዜ፥ እንዲሁም መብረቁ ሲብለጨለጭና ተራራው ሲጤስ ባዩ ጊዜ በፍርሃት በመንቀጥቀጥ ርቀው ቆሙ፤ እነርሱም ሙሴን “አንተ ተናገረን፤ እናዳምጥሃለን፤ እግዚአብሔር ቢናገረን ግን እንሞታለን ብለን እንፈራለን” አሉት። ሙሴም “አይዞአችሁ፥ አትፍሩ፤ እግዚአብሔር በዚህ ሁኔታ ወደ እናንተ የመጣው ሊፈትናችሁና እርሱን በመፍራት ኃጢአት ከመሥራት ርቃችሁ እንድትኖሩ ነው” ሲል መለሰላቸው። ሕዝቡ ግን ርቀው ቆሙ፤ ሙሴ ብቻውን እግዚአብሔር ወዳለበት ጥቅጥቅ ወደ ሆነው ደመና ተጠጋ። እግዚአብሔር ሙሴን ለእስራኤላውያን እንዲነግር እንዲህ ሲል አዘዘው፥ “እኔ እግዚአብሔር ከሰማይ እንዴት እንደ ተናገርኳችሁ አይታችኋል፤ እኔን ብቻ አምልኩ እንጂ፥ ከብርና ከወርቅ ጣዖቶች ሠርታችሁ አታምልኩ፤ ለእኔ ከጭቃ የተሠራ መሠዊያ አብጁልኝ፤ በእርሱም ላይ ከበጎቻችሁ፥ ከፍየሎቻችሁና ከከብቶቻችሁ መርጣችሁ የሚቃጠልና የአንድነት መሥዋዕት አድርጋችሁ ሠዉበት፤ ስሜ እንዲታሰብበት በወሰንኩት ስፍራ ሁሉ ወደ እናንተ መጥቼ እባርካችኋለሁ፤ ለእኔ የድንጋይ መሠዊያ ማበጀት ብትፈልጉ ከጥርብ ድንጋይ የተሠራ አይሁን፤ የብረት መሣሪያ ቢነካው ታረክሱታላችሁ፤ ኀፍረተ ሥጋችሁ በእርሱ ላይ እንዳይገለጥ በመወጣጫ መሰላል አትውጡ።
ዘፀአት 20:18-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሕዝቡም ሁሉ ነጎድጓዱንና መብረቁን፥ የቀንደ መለከቱን ድምፅ፥ ተራራውንም ሲጤስ አዩ፤ ሕዝቡም ፈሩ ተንቀጠቀጡም፥ ርቀውም ቆሙ። ሙሴንም እንዲህ አሉት፦ “አንተ ተናገረን እኛም እንሰማለን፤ ነገር ግን እንዳንሞት እግዚአብሔር አይናገረን።” ሙሴም ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ ሊፈትናችሁ፥ ኃጢአትንም እንዳትሠሩ እርሱን መፍራት በልባችሁ እንዲሆን እግዚአብሔር መጥቷልና።” ሙሴ እግዚአብሔር ወዳለበት ወደ ጨለማው ሲቀርብ ሕዝቡ ግን ርቀው ቆሙ። ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፥ ‘እኔ ከሰማይ ከእናንተ ጋር እንደተነጋገርሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል። ከእኔ ጋር የብር አማልክትን አትሥሩ፥ የወርቅ አማልክትንም ለእናንተ አትሥሩ። ከአፈርም መሠዊያ ሥራልኝ፥ የሚቃጠለውንና የሰላም መሥዋዕትህን በጎችህንም በሬዎችህንም ሠዋበት፤ ስሜን በማሳስብበት ስፍራ ሁሉ ወደ አንተ መጥቼ እባርክሃለሁ። የድንጋይም መሠዊያ ብታደርግልኝ በተጠረበ ድንጋይ አትሥራው፤ በመሣሪያ ብትነካው ታረክሰዋለህና። ኃፍረተ ሥጋህ በእርሱ ላይ እንዳይገለጥ ወደ መሠዊያዬ በደረጃ አትውጣ።’”