ዘፀአት 20:1-6
ዘፀአት 20:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ይህን ቃል ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ “ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ፤ “ከእኔ በቀር ሌሎችን አማልክት አታምልክ። “በላይ በሰማይ ከአለው፥ በታችም በምድር ከአለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ከአለው ነገር የማናቸውንም ምስል ለአንተ አምላክ አታድርግ። አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና። በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኀጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፤ ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ አምላክ ነኝና።
ዘፀአት 20:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር እነዚህን ቃሎች ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ፤ “ከግብጽ ከባርነት ምድር ያወጣሁህ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ። “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ። በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም ከምድር በታች ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩ ነገሮች በማናቸውም ዐይነት ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ። አትስገድላቸው ወይም አታምልካቸውም፤ እኔ አምላክህ እግዚአብሔር የሚጠሉኝን ስለ አባቶቻቸው ኀጢአት እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ ልጆቻቸውን የምቀጣ ቀናተኛ አምላክ ነኝ፤ ለሚወድዱኝና ትእዛዞቼን ለሚጠብቁ ግን እስከ ሺሕ ትውልድ ፍቅርን የማሳይ ነኝ።
ዘፀአት 20:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ይህን ቃል ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ። ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም፤ በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢያት በልጆች ላይ የማመጣ ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና።
ዘፀአት 20:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ ለሕዝቡ ተናገረ፥ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በባርነት ከምትኖርባት ከግብጽ ምድር ያወጣሁህ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ፤ “ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አታምልክ፤ “በሰማይም ሆነ በምድር ወይም ከምድር በታች ባለው ውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ነገሮች የማንኛውንም ዐይነት ምስል ጣዖት አድርገህ አትሥራ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ እጅግ ቀናተኛ ስለ ሆንኩ ተቀርጾ የተሠራውን ማንኛውም ጣዖት አታምልክ፤ አትስገድለትም፤ እኔ የሚጠሉኝን ሁሉ እቀጣለሁ፤ ዘራቸውንም ሁሉ እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ድረስ እበቀላለሁ። ለሚወዱኝና ትእዛዞቼን ለሚጠብቁ ሁሉ ግን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ዘለዓለማዊ ፍቅሬን አሳያቸዋለሁ።
ዘፀአት 20:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እግዚአብሔርም እነዚህን ቃሎች ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “ከግብጽ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ ጌታ አምላክህ እኔ ነኝ። “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ። በላይ በሰማያት ካለው፥ በታች በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም አምሳል፥ የተቀረጸ ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውም፤ እኔ ጌታ አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፥ ለሚወድዱኝ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ ነኝ።