ዘፀአት 2:10-15
ዘፀአት 2:10-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሕፃኑም በአደገ ጊዜ ወደ ፈርዖን ልጅ ወሰደችው፤ ለእርስዋም ልጅ ሆነላት። እኔ ከውኃ አውጥቼዋለሁና ስትልም ስሙን ሙሴ ብላ ጠራችው ። ከብዙ ቀን በኋላ እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ አደገ፤ ወደ ወንድሞቹም ወጣ፤ መከራቸውንም ተመለከተ፤ የግብፅም ሰው ከወንድሞቹ ከእስራኤል ልጆች አንዱን ዕብራዊ ሰው ሲመታ አየ። ወዲህና ወዲያ ተመለከተ፤ ማንንም አላየም፤ ግብፃዊውንም ገደለው፤ በአሸዋ ውስጥም ቀበረው። በሁለተኛውም ቀን ወጣ፤ ሁለቱም የዕብራውያን ሰዎች ሲጣሉ አየ፤ ሙሴም በዳዩን፥ “ለምን ባልንጀራህን ትመታዋለህ?” አለው። ወንድሙን የሚበድለው ያም ሰው፥ “በእኛ ላይ አንተን አለቃ ወይስ ዳኛ ማን አደረገህ? ወይስ ግብፃዊውን ትናንት እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትሻለህን?” አለው። ሙሴም፥ “በእውነት ይህ ነገር ታውቆአልን?” ብሎ ፈራ። ፈርዖንም ይህን ነገር ሰማ፤ ሙሴንም ሊገድለው ፈለገ። ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኰበለለ፤ በምድያምም ምድር ተቀመጠ፤ ወደ ምድያም ምድር በደረሰ ጊዜም በውኃው ጕድጓድ አጠገብ ዐረፈ።
ዘፀአት 2:10-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሕፃኑም ባደገ ጊዜ ወደ ፈርዖን ልጅ አመጣችው፤ ልጇም ሆነ፤ እርሷም፣ “ከውሃ አውጥቼዋለሁና” ስትል ስሙን ሙሴ ብላ ጠራችው። ሙሴ ካደገ በኋላ አንድ ቀን ወገኖቹ ወደሚገኙበት ስፍራ ወጣ፤ በዚያም ተገድደው ከባድ ሥራ ሲሠሩ ተመለከተ፤ ዕብራዊ ወገኑንም አንድ ግብጻዊ ሲደበድበው አየ። ሙሴም አካባቢውን ቃኝቶ ማንም አለመኖሩን ካረጋገጠ በኋላ፣ ግብጻዊውን ገድሎ አሸዋ ውስጥ ደበቀው። በማግስቱም በወጣ ጊዜ ሁለት ዕብራውያን እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አየ፤ ጥፋተኛውንም፣ “የገዛ ወገንህን የምትመታው ለምንድን ነው?” አለው። ሰውየውም፣ “አንተን በእኛ ላይ ገዥና ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማን ነው? ግብጻዊውን እንደ ገደልኸው እኔንም ልትገድለኝ ትፈልጋለህን?” አለው። ሙሴም፣ “ለካስ ያደረግሁት ነገር ታውቋል!” በማለት ፈራ። ፈርዖንም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ፤ ሙሴ ግን ከፈርዖን ሸሽቶ ወደ ምድያም ሄደ፤ እዚያም እንደ ደረሰ በአንድ የውሃ ጕድጓድ አጠገብ ተቀመጠ።
ዘፀአት 2:10-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሕፃኑም አደገ፤ ወደ ፈርዖንም ልጅ ዘንድ አመጣችው፤ ለእርስዋም ልጅ ሆነላት። “እኔ ከውኃ አውጥቼዋለሁና” ስትልም ስሙን ሙሴ ብላ ጠራችው። በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ ጎበዝ በሆነ ጊዜ ወደ ወንድሞቹ ወጣ፤ የሥራቸውንም መከራ ተመለከተ፤ የግብፅም ሰው የወንድሞቹን የዕብራውያንን ሰው ሲመታ አየ። ወዲህና ወዲያም ተመለከተ፤ ማንንም አላየም፤ ግብፃዊውንም ገደለ፤ በአሸዋም ውስጥ ሸሸገው። በሁለተኛውም ቀን ወጣ፤ ሁለቱም የዕብራውያን ሰዎች ሲጣሉ አየ፤ በዳዩንም፦ “ለምን ባልንጀራህን ትመታዋለህ?” አለው። ያም፦ “በእኛ ላይ አንተን አለቃ ወይስ ዳኛ ማን አደረገህ? ወይስ ግብፃዊውን እንደገደልኸው ልትገድለኝ ትሻለህን?” አለው። ሙሴም፦ “በእውነት ይህ ነገር ታውቆአል” ብሎ ፈራ። ፈርዖንም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ። ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኰበለለ፤ በምድያምም ምድር ተቀመጠ፤ በውኃም ጉድጓድ አጠገብ ዐረፈ።
ዘፀአት 2:10-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሕፃኑም ባደገ ጊዜ ወደ ንጉሡ ልጅ አመጣችው፤ የእርስዋም ልጅ ተባለ። እርስዋም “ከውሃ ያወጣሁት ስለ ሆነ ስሙ ሙሴ ተብሎ ይጠራ” አለች። ሙሴ ባደገ ጊዜ ወገኖቹን ለመጐብኘት ሄደ፤ ከባድ ሥራ መሥራታቸውን ተመለከተ፤ እንዲያውም አንድ ግብጻዊ ከወገኖቹ አንዱ የሆነውን ዕብራዊ ሲደበድብ አየ። ሙሴ ዙሪያውን ተመልክቶ ማንም እንደማያየው ከተረዳ በኋላ ግብጻዊውን ገድሎ በአሸዋ ውስጥ ደበቀው። በማግስቱም ወደዚያው ስፍራ ተመልሶ ሲሄድ ሁለት ዕብራውያን እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አየ፤ በደል የሠራውንም ሰው ተመልክቶ “ወገንህ የሆነውን ዕብራዊ ለምን ትመታዋለህ?” ሲል ጠየቀው። ሰውየውም “አንተን በእኛ ላይ ገዢና ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማን ነው? ወይስ ያንን ግብጻዊ እንደ ገደልክ እኔንም መግደል ትፈልጋለህን?” አለው፤ ሙሴም እጅግ ፈርቶ “ያደረግኹት ነገር ታውቋል ማለት ነው” ብሎ አሰበ። ንጉሡም የሆነውን ነገር ሁሉ በሰማ ጊዜ ሙሴን ለማስገደል ፈለገ፤ ሙሴ ግን ኰብልሎ በዚያው ለመኖር ወደ ምድያም አገር ሄደ። እዚያም እንደ ደረሰ በውሃ ጒድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፤
ዘፀአት 2:10-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሕፃኑም አደገ፥ ወደ ፈርዖንም ልጅ አመጣችው፥ ለእርሷም ልጅ ሆነላት። እኔ ከውኃ አውጥቼዋለሁና ስትልም ስሙን ሙሴ ብላ ጠራችው። በነዚያም ቀኖች፥ ሙሴ ባደገ ጊዜ ወደ ወንድሞቹ ወጣ፥ የሥራቸውንም መከራ ተመለከተ፤ የግብጽም ሰው ከወንድሞቹ አንድ የሆነውን ዕብራዊ ሰው ሲመታ አየ። ወዲህና ወዲያም ተመለከተ፥ ማንንም አላየም፥ ግብፃዊውንም ገደለው፥ በአሸዋም ውስጥ ደበቀው። በሁለተኛውም ቀን ወጣ፥ ሁለት ዕብራውያን ሰዎች ሲጣሉ አየ፥ በዳዩንም፦ “ለምን ባልንጀራህን ትመታዋለህ?” አለው። እሱም፦ “አንተን በእኛ ላይ አለቃና ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማን ነው? ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትፈልጋለህን?” አለው። ሙሴም፦ “በእውነት ይህ ነገር ታውቆአል” ብሎ ፈራ። ፈርዖንም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ። ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኮበለለ፥ በምድያምም ምድር ተቀመጠ፥ በውኃም ጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ።