ዘፀአት 2:1-25

ዘፀአት 2:1-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከሌዊ ወገን እን​በ​ረም የሚ​ባል አንድ ሰው ነበረ፤ እር​ሱም ከሌዊ ሴቶች ልጆች ሚስ​ትን አገባ። ሴቲ​ቱም ፀነ​ሰች፤ ወንድ ልጅም ወለ​ደች፤ መል​ካ​ምም እን​ደ​ሆነ በአዩ ጊዜ ሦስት ወር ሸሸ​ጉት። ደግ​ሞም ሊሸ​ሽ​ጉት በአ​ል​ቻሉ ጊዜ እናቱ የደ​ን​ገል ሣጥን ለእ​ርሱ ወስዳ ዝፍ​ትና ቅጥ​ራን ለቀ​ለ​ቀ​ችው፤ ሕፃ​ኑ​ንም አኖ​ረ​ች​በት፤ በወ​ን​ዝም ዳር ባለ በቄ​ጠማ ውስጥ አስ​ቀ​መ​ጠ​ችው። እኅ​ቱም ምን እን​ደ​ሚ​ደ​ር​ስ​በት ታውቅ ዘንድ በሩቅ ቆማ ትጐ​በ​ኘው ነበር። የፈ​ር​ዖ​ንም ሴት ልጅ ልት​ታ​ጠብ ወደ ወንዝ ወረ​ደች፤ ደን​ገ​ጥ​ሮ​ች​ዋም በወ​ንዝ ዳር ይሄዱ ነበር፤ ሣጥ​ኑ​ንም በቄ​ጠማ ውስጥ አየች፤ ደን​ገ​ጥ​ር​ዋ​ንም ልካ አስ​መ​ጣ​ችው። ሣጥ​ኑን በከ​ፈ​ተ​ችም ጊዜ ሕፃ​ኑን አየች፤ እነ​ሆም፥ ሕፃኑ በሣ​ጥኑ ውስጥ ያለ​ቅስ ነበር፤ የፈ​ር​ዖ​ንም ልጅ አዘ​ነ​ች​ለት፥ “ይህ ሕፃን ከዕ​ብ​ራ​ው​ያን ልጆች አንዱ ነው” አለች። የዚ​ያም ሕፃን እኅት ለፈ​ር​ዖን ልጅ፥ “ሕፃ​ኑን ታጠ​ባ​ልሽ ዘንድ ሄጄ የም​ታ​ጠባ ሴት ከዕ​ብ​ራ​ው​ያን ሴቶች ልጥ​ራ​ል​ሽን?” አለ​ቻት። የፈ​ር​ዖ​ንም ልጅ፥ “ሂጂና ጥሪ​ልኝ” አለ​ቻት፤ ብላ​ቴ​ና​ዪ​ቱም ሄዳ የሕ​ፃ​ኑን እናት ጠራች። የፈ​ር​ዖ​ንም ልጅ፥ “ይህን ሕፃን ተን​ከ​ባ​ክ​በሽ አጥ​ቢ​ልኝ፤ ዋጋ​ሽ​ንም እሰ​ጥ​ሻ​ለሁ” አለ​ቻት። ሴቲ​ቱም ሕፃ​ኑን ወስዳ አጠ​ባ​ችው። ሕፃ​ኑም በአ​ደገ ጊዜ ወደ ፈር​ዖን ልጅ ወሰ​ደ​ችው፤ ለእ​ር​ስ​ዋም ልጅ ሆነ​ላት። እኔ ከውኃ አው​ጥ​ቼ​ዋ​ለ​ሁና ስት​ልም ስሙን ሙሴ ብላ ጠራ​ችው ። ከብዙ ቀን በኋላ እን​ዲህ ሆነ፤ ሙሴ አደገ፤ ወደ ወን​ድ​ሞ​ቹም ወጣ፤ መከ​ራ​ቸ​ው​ንም ተመ​ለ​ከተ፤ የግ​ብ​ፅም ሰው ከወ​ን​ድ​ሞቹ ከእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች አን​ዱን ዕብ​ራዊ ሰው ሲመታ አየ። ወዲ​ህና ወዲያ ተመ​ለ​ከተ፤ ማን​ንም አላ​የም፤ ግብ​ፃ​ዊ​ው​ንም ገደ​ለው፤ በአ​ሸዋ ውስ​ጥም ቀበ​ረው። በሁ​ለ​ተ​ኛ​ውም ቀን ወጣ፤ ሁለ​ቱም የዕ​ብ​ራ​ው​ያን ሰዎች ሲጣሉ አየ፤ ሙሴም በዳ​ዩን፥ “ለምን ባል​ን​ጀ​ራ​ህን ትመ​ታ​ዋ​ለህ?” አለው። ወን​ድ​ሙን የሚ​በ​ድ​ለው ያም ሰው፥ “በእኛ ላይ አን​ተን አለቃ ወይስ ዳኛ ማን አደ​ረ​ገህ? ወይስ ግብ​ፃ​ዊ​ውን ትና​ንት እንደ ገደ​ል​ኸው ልት​ገ​ድ​ለኝ ትሻ​ለ​ህን?” አለው። ሙሴም፥ “በእ​ው​ነት ይህ ነገር ታው​ቆ​አ​ልን?” ብሎ ፈራ። ፈር​ዖ​ንም ይህን ነገር ሰማ፤ ሙሴ​ንም ሊገ​ድ​ለው ፈለገ። ሙሴ ግን ከፈ​ር​ዖን ፊት ኰበ​ለለ፤ በም​ድ​ያ​ምም ምድር ተቀ​መጠ፤ ወደ ምድ​ያም ምድር በደ​ረሰ ጊዜም በው​ኃው ጕድ​ጓድ አጠ​ገብ ዐረፈ። ለም​ድ​ያ​ምም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበ​ሩት፤ የአ​ባ​ታ​ቸ​ው​ንም የዮ​ቶ​ርን በጎች ይጠ​ብቁ ነበር፤ እነ​ር​ሱም መጥ​ተው ውኃ ቀዱ፤ የአ​ባ​ታ​ቸ​ው​ንም የዮ​ቶ​ርን በጎች ሊያ​ጠጡ የው​ኃ​ዉን ገንዳ ሞሉ። እረ​ኞ​ችም መጥ​ተው ገፉ​አ​ቸው፤ ሙሴ ግን ተነ​ሥቶ አዳ​ና​ቸው፤ እየ​ቀ​ዳም በጎ​ቻ​ቸ​ዉን አጠ​ጣ​ላ​ቸው። ወደ አባ​ታ​ቸ​ውም ወደ ራጉ​ኤል መጡ እር​ሱም፥ “ዛሬስ እን​ዴት ፈጥ​ና​ችሁ መጣ​ችሁ?” አላ​ቸው። እነ​ር​ሱም፥ “አንድ የግ​ብፅ ሰው ከእ​ረ​ኞች እጅ አዳ​ነን፤ ደግ​ሞም ቀዳ​ልን፤ በጎ​ቻ​ች​ን​ንም አጠ​ጣ​ልን” አሉት። ልጆ​ቹ​ንም፥ “ሰው​ዬው ወዴት ነው? ለም​ንስ ያን ሰው ተዋ​ች​ሁት? ጥሩት፤ እን​ጀ​ራም ይብላ” አላ​ቸው። ሙሴም ከዚያ ሰው ጋር ሊቀ​መጥ ወደደ፤ ልጁ​ንም ሲፓ​ራን ለሙሴ ሚስት ትሆ​ነው ዘንድ ሰጠው። ያችም ሴት ፀነ​ሰች፤ ወንድ ልጅም ወለ​ደች፤ ሙሴም፥ “በሌላ ምድር መጻ​ተኛ ነኝ” ሲል ስሙን ጌር​ሳም ብሎ ጠራው። ዳግ​መ​ኛም ፀነ​ሰች፤ ወንድ ልጅም ወለ​ደች፤ ስሙ​ንም ኤል​ኤ​ዜር አለው፤ የአ​ባቴ ፈጣሪ ረዳቴ ነው ሲል። ከዚ​ያም ከብዙ ቀን በኋላ እን​ዲህ ሆነ፤ የግ​ብፅ ንጉሥ ሞተ፤ የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ልጆች ከባ​ር​ነት የተ​ነሣ አለ​ቀሱ፤ ጮኹም፤ ስለ ባር​ነ​ታ​ቸ​ውም ጩኸ​ታ​ቸው ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ወጣ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ጩኸ​ታ​ቸ​ውን ሰማ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ከአ​ብ​ር​ሃ​ምና ከይ​ስ​ሐቅ፥ ከያ​ዕ​ቆ​ብም ጋር ያደ​ረ​ገ​ውን ቃል ኪዳን ዐሰበ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም የእ​ስ​ራ​ኤ​ልን ልጆች ጐበ​ኛ​ቸው፤ ታወ​ቀ​ላ​ቸ​ውም።

ዘፀአት 2:1-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በዚያ ጊዜ ከሌዊ ነገድ የሆነ አንድ ሰው አንዲት ሌዋዊት ሴት አገባ። እርሷም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ሕፃኑ መልከ መልካም መሆኑን ባየች ጊዜ ሦስት ወር ሸሸገችው። ከዚያ በላይ ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ ግን የደንገል ቅርጫት ወስዳ፣ በዝፍትና በቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም በውስጡ አስተኝታ ቅርጫቱን አባይ ወንዝ ዳር ቄጠማ መካከል አስቀመጠችው። የሕፃኑም እኅት የሚደርስበትን ነገር ለማወቅ ራቅ ብላ ቆማ ታይ ነበር። በዚህ ጊዜ የፈርዖን ልጅ ልትታጠብ ወደ አባይ ወንዝ ወረደች፤ በምትታጠብበትም ጊዜ ደንገጥሮቿ በወንዙ ዳር ወዲያና ወዲህ ይሉ ነበር፤ በቄጠማውም መካከል የተቀመጠ ቅርጫት አይታ ከደንገጥሮቿ አንዷን እንድታመጣው ላከቻት። ቅርጫቱን ስትከፍተው ሕፃኑን በውስጡ አየች፤ ያለቅስ ስለ ነበርም ዐዘነችለትና፣ “ከዕብራውያን ሕፃናት አንዱ መሆን አለበት” አለች። የሕፃኑ እኅት ለፈርዖን ልጅ፣ “ሕፃኑን እያጠባች የምታሳድግልሽ ከዕብራውያን ሴቶች መካከል ሞግዚት ላምጣልሽን?” አለቻት። የፈርዖንም ልጅ፣ “መልካም፣ ሂጂ” አለቻት። ልጅቱም ሄዳ የሕፃኑን እናት ይዛ መጣች። የፈርዖንም ልጅ ሴቲቱን፣ “ይህን ሕፃን ወስደሽ እያጠባሽ አሳድጊልኝ፤ ደመወዝ እከፍልሻለሁ” አለቻት። ሴትዮዋም ሕፃኑን ወስዳ አሳደገችው። ሕፃኑም ባደገ ጊዜ ወደ ፈርዖን ልጅ አመጣችው፤ ልጇም ሆነ፤ እርሷም፣ “ከውሃ አውጥቼዋለሁና” ስትል ስሙን ሙሴ ብላ ጠራችው። ሙሴ ካደገ በኋላ አንድ ቀን ወገኖቹ ወደሚገኙበት ስፍራ ወጣ፤ በዚያም ተገድደው ከባድ ሥራ ሲሠሩ ተመለከተ፤ ዕብራዊ ወገኑንም አንድ ግብጻዊ ሲደበድበው አየ። ሙሴም አካባቢውን ቃኝቶ ማንም አለመኖሩን ካረጋገጠ በኋላ፣ ግብጻዊውን ገድሎ አሸዋ ውስጥ ደበቀው። በማግስቱም በወጣ ጊዜ ሁለት ዕብራውያን እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አየ፤ ጥፋተኛውንም፣ “የገዛ ወገንህን የምትመታው ለምንድን ነው?” አለው። ሰውየውም፣ “አንተን በእኛ ላይ ገዥና ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማን ነው? ግብጻዊውን እንደ ገደልኸው እኔንም ልትገድለኝ ትፈልጋለህን?” አለው። ሙሴም፣ “ለካስ ያደረግሁት ነገር ታውቋል!” በማለት ፈራ። ፈርዖንም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ፤ ሙሴ ግን ከፈርዖን ሸሽቶ ወደ ምድያም ሄደ፤ እዚያም እንደ ደረሰ በአንድ የውሃ ጕድጓድ አጠገብ ተቀመጠ። የምድያም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም ወደ ውሃው ጕድጓድ መጥተው የአባታቸውን በጎች ውሃ ለማጠጣት ገንዳውን ሞሉት። እረኞችም መጥተው ሴቶቹን ሲያባርሯቸው ሙሴ ከተቀመጠበት ተነሥቶ ተከላከለላቸው፤ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው። ሴቶቹም ወደ አባታቸው ወደ ራጉኤል በተመለሱ ጊዜ፣ “ዛሬስ ያለወትሯችሁ እንዴት ፈጥናችሁ ተመለሳችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “አንድ ግብጻዊ ከእረኞች እጅ አዳነን፤ እንዲያውም ውሃ ቀድቶ በጎቻችንን አጠጣልን” አሉት። አባታቸውም፣ ሴቶች ልጆቹን “የት አለ? ለምን ትታችሁት መጣችሁ? ጥሩትና ዐብሮን እንጀራ ይብላ” አላቸው። ሙሴም ከሰውየው ጋራ ለመኖር ተስማማ፤ ራጉኤልም ልጁን ሲፓራን ዳረለት። ሲፓራም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ሙሴም፣ “በባዕድ አገር መጻተኛ ነኝ” ሲል የልጁን ስም ጌርሳም ብሎ ጠራው። ከብዙ ዓመት በኋላ የግብጽ ንጉሥ ሞተ፤ እስራኤላውያንም በባርነት ከደረሰባቸው ግፍ የተነሣ ይጮኹ ነበር፤ ከባርነት ቀንበር ለመላቀቅ ያሰሙትም ጩኸት ወደ እግዚአብሔር ደረሰ። እግዚአብሔርም የጩኸታቸውን ሲቃ ሰማ፤ ከአብርሃም፣ ከይሥሐቅና ከያዕቆብ ጋራ የገባውንም ቃል ኪዳን ዐሰበ። እግዚአብሔርም እስራኤላውያንን ተመለከተ፤ ስለ እነርሱም ገደደው።

ዘፀአት 2:1-25 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከሌዊ ወገንም አንድ ሰው ሄዶ የሌዊን ልጅ አገባ። ሴቲቱም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ መልካምም እንደሆነ ባየች ጊዜ ሦስት ወር ሸሸገችው። ደግሞም ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ፥ የደንገል ሣጥን ለእርሱ ወስዳ ዝፍትና ቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም አኖረችበት፤ በወንዝም ዳር ባለ በቄጠማ ውስጥ አስቀመጠችው። እኅቱም የሚደርስበትን ታውቅ ዘንድ በሩቅ ቆማ ትመለከት ነበር። የፈርዖንም ልጅ ልትታጠብ ወደ ወንዝ ወረደች፤ ደንገጥሮችዋም በወንዝ ዳር ይሄዱ ነበር፤ ሣጥኑንም በቄጠማ ውስጥ አየች፤ ደንገጥሩዋንም ልካ አስመጣችው። በከፈተችውም ጊዜ ሕፃኑን አየች፤ እነሆም ሕፃኑ ያለቅስ ነበር፤ አዘነችለትም፤ “ይህ ከዕብራውያን ልጆች አንድ ነው፤” አለች። እኅቱም ለፈርዖን ልጅ፦ “ሕፃኑን ታጠባልሽ ዘንድ ሄጄ የምታጠባት ሴት ከዕብራውያን ሴቶች ልጥራልሽን?” አለቻት፤ የፈርዖንም ልጅ፦ “ሂጂ” አለቻት፤ ብላቴናይቱም ሄዳ የሕፃኑን እናት ጠራች። የፈርዖንም ልጅ፦ “ይህን ሕፃን ወስደሽ አጥቢልኝ፤ ዋጋሽንም እሰጥሻለሁ፤” አለቻት። ሴቲቱም ሕፃኑን ወስዳ አጠባችው። ሕፃኑም አደገ፤ ወደ ፈርዖንም ልጅ ዘንድ አመጣችው፤ ለእርስዋም ልጅ ሆነላት። “እኔ ከውኃ አውጥቼዋለሁና” ስትልም ስሙን ሙሴ ብላ ጠራችው። በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ ጎበዝ በሆነ ጊዜ ወደ ወንድሞቹ ወጣ፤ የሥራቸውንም መከራ ተመለከተ፤ የግብፅም ሰው የወንድሞቹን የዕብራውያንን ሰው ሲመታ አየ። ወዲህና ወዲያም ተመለከተ፤ ማንንም አላየም፤ ግብፃዊውንም ገደለ፤ በአሸዋም ውስጥ ሸሸገው። በሁለተኛውም ቀን ወጣ፤ ሁለቱም የዕብራውያን ሰዎች ሲጣሉ አየ፤ በዳዩንም፦ “ለምን ባልንጀራህን ትመታዋለህ?” አለው። ያም፦ “በእኛ ላይ አንተን አለቃ ወይስ ዳኛ ማን አደረገህ? ወይስ ግብፃዊውን እንደገደልኸው ልትገድለኝ ትሻለህን?” አለው። ሙሴም፦ “በእውነት ይህ ነገር ታውቆአል” ብሎ ፈራ። ፈርዖንም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ። ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኰበለለ፤ በምድያምም ምድር ተቀመጠ፤ በውኃም ጉድጓድ አጠገብ ዐረፈ። ለምድያምም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም መጥተው ውኃ ቀዱ፤ የአባታቸውንም በጎች ሊያጠጡ የውኃውንም ገንዳ ሞሉ። እረኞችም መጥተው ገፉአቸው፤ ሙሴ ግን ተነሥቶ ረዳቸው፤ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው። ወደ አባታቸው ወደ ራጉኤልም በመጡ ጊዜ፦ “ስለ ምን ዛሬ ፈጥናችሁ መጣችሁ?” አላቸው። እነርሱም፦ “አንድ የግብፅ ሰው ከእረኞች እጅ አዳነን፤ ደግሞም ቀዳልን፤ በጎቻችንንም አጠጣ፤” አሉ። ልጆቹንም፦ “እርሱ ወዴት ነው? ለምንስ ያንን ሰው ተዋችሁት? ጥሩት፤ እንጀራም ይብላ፤” አላቸው። ሙሴም ከዚያ ሰው ጋር ሊቀመጥ ወደደ፤ ልጁንም ሲፓራን ለሙሴ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠው። ወንድ ልጅም ወለደች፤ “በሌላ ምድር መጻተኛ ነኝ” ሲል ስሙን ጌርሳም ብሎ ጠራው። ከዚያም ከብዙ ቀን በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የግብፅ ንጉሥ ሞተ፤ የእስራኤልም ልጆች ከባርነት የተነሣ አለቀሱ፤ ጮኹም፤ ስለባርነታቸውም ጩኸታቸው ወደ እግዚአብሔር ወጣ። እግዚአብሔርም የለቅሶአቸውን ድምፅ ሰማ፤ እግዚአብሔርም ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አሰበ። እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች አየ፤ እግዚአብሔርም በእነርሱ ያለውን ነገር አወቀ።

ዘፀአት 2:1-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በዚያን ጊዜ ከሌዊ ነገድ የሆነ አንድ ሰው አንዲት ሌዋዊት ሴት አገባ፤ እርስዋም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ሕፃኑ መልከ መልካም መሆኑን አይታ ሦስት ወር ሸሸገችው። ሆኖም ከዚያ በላይ ልትሸሽገው አለመቻልዋን በተረዳች ጊዜ፥ በሣጥን መልክ ከደንገል የተሠራ ቅርጫት አዘጋጀች፤ ውሃም እንዳያስገባ በቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም አስገብታ ቅርጫቱን በወንዝ ዳር በሚገኝ ቀጤማ መካከል አስቀመጠችው። የሕፃኑም እኅት የሚደርስበትን ነገር ለማየት ራቅ ብላ ትጠባበቀው ነበር። በዚህ ጊዜ የንጉሡ ሴት ልጅ ልትታጠብ ወደ ወንዝ ወረደች፤ ሴቶች አገልጋዮችዋም በወንዙ ዳር ይሄዱ ነበር፤ እርስዋም በቀጤማ መካከል የተቀመጠ አንድ ቅርጫት አየች፤ አገልጋይዋንም ልካ አስመጣችው። በከፈተችውም ጊዜ አንድ ሕፃን በውስጡ አገኘች፤ ሕፃኑም ያለቅስ ስለ ነበር አዘነችለትና “ይህ ከዕብራውያን ሕፃናት አንዱ ነው” አለች። በዚያን ጊዜ የሕፃኑ እኅት የንጉሡን ልጅ “ይህን ሕፃን እያጠባች የምታሳድግልሽ ከዕብራውያን ሴቶች አንዲት ሞግዚት ልጥራልሽን?” ስትል ጠየቀቻት። “አዎ፥ ሄደሽ ጥሪልኝ” ስላለቻት ልጅቱ ሄደች፤ የሕፃኑንም እናት ጠርታ አመጣች። የንጉሡ ልጅም ሴትዮይቱን “ይህን ሕፃን ወስደሽ እያጠባሽ አሳድጊልኝ፤ ደመወዝሽንም እከፍልሻለሁ” አለቻት፤ ስለዚህ ሴቲቱ ሕፃኑን ወስዳ ታጠባው ጀመር። ሕፃኑም ባደገ ጊዜ ወደ ንጉሡ ልጅ አመጣችው፤ የእርስዋም ልጅ ተባለ። እርስዋም “ከውሃ ያወጣሁት ስለ ሆነ ስሙ ሙሴ ተብሎ ይጠራ” አለች። ሙሴ ባደገ ጊዜ ወገኖቹን ለመጐብኘት ሄደ፤ ከባድ ሥራ መሥራታቸውን ተመለከተ፤ እንዲያውም አንድ ግብጻዊ ከወገኖቹ አንዱ የሆነውን ዕብራዊ ሲደበድብ አየ። ሙሴ ዙሪያውን ተመልክቶ ማንም እንደማያየው ከተረዳ በኋላ ግብጻዊውን ገድሎ በአሸዋ ውስጥ ደበቀው። በማግስቱም ወደዚያው ስፍራ ተመልሶ ሲሄድ ሁለት ዕብራውያን እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አየ፤ በደል የሠራውንም ሰው ተመልክቶ “ወገንህ የሆነውን ዕብራዊ ለምን ትመታዋለህ?” ሲል ጠየቀው። ሰውየውም “አንተን በእኛ ላይ ገዢና ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማን ነው? ወይስ ያንን ግብጻዊ እንደ ገደልክ እኔንም መግደል ትፈልጋለህን?” አለው፤ ሙሴም እጅግ ፈርቶ “ያደረግኹት ነገር ታውቋል ማለት ነው” ብሎ አሰበ። ንጉሡም የሆነውን ነገር ሁሉ በሰማ ጊዜ ሙሴን ለማስገደል ፈለገ፤ ሙሴ ግን ኰብልሎ በዚያው ለመኖር ወደ ምድያም አገር ሄደ። እዚያም እንደ ደረሰ በውሃ ጒድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፤ አንድ የምድያም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም ውሃ ለመቅዳትና በገንዳ እየሞሉ የአባታቸውን በጎችና ፍየሎች ለማጠጣት ወደዚያ መጡ። እረኞችም መጥተው እነዚያን ሴቶች አባረሩአቸው፤ ሙሴም ሴቶቹን ከእረኞቹ እጅ በማዳን መንጋቸውን ውሃ አጠጣላቸው። እነዚያም ሴቶች ልጆች ወደ አባታቸው ወደ ራጉኤል በተመለሱ ጊዜ “ዛሬ እንዴት በፍጥነት ተመለሳችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “አንድ ግብጻዊ ከእረኞች እጅ አዳነን፤ እንዲያውም ውሃ እየቀዳ መንጋችንን አጠጣልን” ብለው መለሱለት። አባታቸውም “ታዲያ፥ አሁን ሰውየው የት ነው? ለምንስ ተዋችሁት? ሂዱ ጥሩትና መጥቶ እህል ይቅመስ” አላቸው። ሙሴም ከዚያ ሰው ጋር ለመኖር ፈቃደኛ ሆነ፤ ያም ሰው ልጁን ጺጳራን ሚስት ትሆነው ዘንድ ለሙሴ ሰጠው። እርስዋም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ሙሴም “እኔ በዚህ ምድር መጻተኛ ነኝ” ሲል ልጁን ጌርሾም ብሎ ጠራው። ከብዙ ዓመቶች በኋላ የግብጽ ንጉሥ ሞተ፤ እስራኤላውያን ግን አሁንም በባርነት ቀንበር ሥር በመጨነቅ ርዳታ ለማግኘት በመጮኽ ላይ ነበሩ፤ ጩኸታቸውም ወደ እግዚአብሔር ደረሰ። ጭንቀት የተሞላበትን ጩኸታቸውንም ሰምቶ እግዚአብሔር ከአብርሃም፥ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን አስታወሰ። እግዚአብሔር እስራኤላውያን በባርነት መጨነቃቸውን አይቶ ስለ እነርሱ አሰበ።

ዘፀአት 2:1-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከሌዊ ወገን የሆነ አንድ ሰው ሄዶ የሌዊን ልጅ አገባ። ሴቲቱም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅም ወለደች፤ መልካምም እንደሆነ ባየች ጊዜ ሦስት ወር ሸሸገችው። ደግሞም ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ፥ የደንገል ሣጥን ለእርሱ ወስዳ ዝፍትና ቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም እዚያ ውስጥ አስገባችው፥ በወንዝም ዳር ባለ በቄጠማ ውስጥ አስቀመጠችው። እኅቱም ምን እንደሚደርስበት ለማየት በሩቅ ቆማ ትከታተለው ነበር። የፈርዖንም ልጅ ልትታጠብ ወደ ወንዝ ወረደች፤ ደንገጥሮችዋም በወንዝ ዳር ይሄዱ ነበር፤ ሣጥኑንም በቄጠማ ውስጥ አየች፥ ደንገጥሩዋንም ልካ አስመጣችው። በከፈተችውም ጊዜ ሕፃኑን አየች፥ እነሆም ሕፃኑ ያለቅስ ነበር፤ አዘነችለትም፦ “ይህ ከዕብራውያን ልጆች አንዱ ነው” አለች። እኅቱም ለፈርዖን ልጅ፦ “ሕፃኑን እንድታጠባልሽ ሄጄ የምታጠባ ሴት ከዕብራውያን ሴቶች ልጥራልሽን?” አለቻት፤ የፈርዖንም ልጅ፦ “ሂጂ” አለቻት፤ ብላቴናይቱም ሄዳ የሕፃኑን እናት ጠራች። የፈርዖንም ልጅ፦ “ይህን ሕፃን ወስደሽ አጥቢልኝ፥ ዋጋሽንም እከፍልሻለሁ” አለቻት። ሴቲቱም ሕፃኑን ወስዳ አጠባችው። ሕፃኑም አደገ፥ ወደ ፈርዖንም ልጅ አመጣችው፥ ለእርሷም ልጅ ሆነላት። እኔ ከውኃ አውጥቼዋለሁና ስትልም ስሙን ሙሴ ብላ ጠራችው። በነዚያም ቀኖች፥ ሙሴ ባደገ ጊዜ ወደ ወንድሞቹ ወጣ፥ የሥራቸውንም መከራ ተመለከተ፤ የግብጽም ሰው ከወንድሞቹ አንድ የሆነውን ዕብራዊ ሰው ሲመታ አየ። ወዲህና ወዲያም ተመለከተ፥ ማንንም አላየም፥ ግብፃዊውንም ገደለው፥ በአሸዋም ውስጥ ደበቀው። በሁለተኛውም ቀን ወጣ፥ ሁለት ዕብራውያን ሰዎች ሲጣሉ አየ፥ በዳዩንም፦ “ለምን ባልንጀራህን ትመታዋለህ?” አለው። እሱም፦ “አንተን በእኛ ላይ አለቃና ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማን ነው? ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትፈልጋለህን?” አለው። ሙሴም፦ “በእውነት ይህ ነገር ታውቆአል” ብሎ ፈራ። ፈርዖንም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ። ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኮበለለ፥ በምድያምም ምድር ተቀመጠ፥ በውኃም ጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ። የምድያምም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም መጥተው ውኃ ቀዱ፥ የአባታቸውንም በጎች ሊያጠጡ የውሀውን ገንዳ ሞሉ። እረኞችም መጥተው ገፉአቸው፤ ሙሴ ግን ተነሥቶ ረዳቸው፥ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው። ወደ አባታቸው ወደ ሩኤልም ሄዱ እርሱም፦ “ለምን ዛሬ ፈጥናችሁ መጣችሁ?” አላቸው። እነርሱም፦ “አንድ ግብፃዊ ሰው ከእረኞች እጅ አዳነን፥ ደግሞም ቀዳልን፥ በጎቻችንንም አጠጣ” አሉት። ልጆቹንም፦ “ሰውዬው የት ነው? ለምንስ ይህንን ሰው ተዋችሁት? ጥሩት ምግብም ይብላ” አላቸው። ሙሴም ከዚያ ሰው ጋር ሊቀመጥ ፈቀደ፤ ልጁንም ጺጶራን ለሙሴ ሰጠው። ወንድ ልጅም ወለደች፦ “በሌላ ምድር መጻተኛ ነኝ” ሲል ስሙን “ጌርሾም” ብሎ ጠራው። ከብዙ ቀኖች በኋላ የግብጽ ንጉሥ ሞተ፤ የእስራኤልም ሕዝቦች ከባርነት የተነሣ አለቀሱ፥ ጮኹም፥ ስለባርነታቸውም የልመና ጩኸታቸው ወደ እግዚአብሔር ወጣ። እግዚአብሔርም የለቅሶአቸውን ድምፅ ሰማ፥ እግዚአብሔርም ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አስታወሰ። እግዚአብሔርም የእስራኤልን ሕዝቦች አየ፥ እግዚአብሔርም የደረሰባቸውን ነገር አወቀ።