ዘፀአት 14:13-22
ዘፀአት 14:13-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሙሴም ለሕዝቡ፥ “አትፍሩ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘለዓለም አታዩአቸውምና ቁሙ፤ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተም ዝም ትላላችሁ” አላቸው። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ለምን ትጮኽብኛለህ? ከብቶቻቸውን እንዲነዱ ለእስራኤል ልጆች ንገር። አንተም በትርህን አንሣ፤ እጅህንም በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ ውስጥ በየብስ ያልፋሉ። እነሆም፥ እኔ የፈርዖንንና የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ፥ በሰረገሎቹም፥ በፈረሰኞቹም ላይ እከብራለሁ። ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ፥ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር በአገኘሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዐምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፤ በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ በዚያም ጭጋግና ጨለማ ነበረ፤ ሌሊቱም አለፈ፤ ሌሊቱንም ሁሉ እርስ በእርሳቸው አልተቃረቡም። ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የአዜብ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፤ ባሕሩንም አደረቀው፤ ውኃውም ተከፈለ። የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በየብስ ገቡ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆነላቸው።
ዘፀአት 14:13-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሙሴም ለሕዝቡ መለሰላቸው፤ “አትሸበሩ፣ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር ዛሬ የሚያደርግላችሁን መታደግ ታያላችሁ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብጻውያንን ዳግም አታዩአቸውም። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተ ያለባችሁ መታገሥ ብቻ ነው።” ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለምን ትጮኹብኛላችሁ? ይልቅስ እስራኤላውያንን ወደ ፊት እንዲጓዙ ንገራቸው፤ ውሃውን ለመክፈል በትርህን አንሣና እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ እስራኤላውያን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ይሻገራሉ። ተከትለዋቸው እንዲገቡም የግብጻውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ፣ በሠረገሎቹና በፈረሰኞቹ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ። በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ በከበርሁ ጊዜ፣ ግብጻውያን እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” ከዚያም ከእስራኤል ሰራዊት ፊት ፊት ሆኖ ሲሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ተመለሰና ወደ ኋላቸው መጣ፤ የደመናውም ዐምድ እንዲሁ ከፊት ተነሥቶ ከኋላቸው ቆመ፤ በግብጽና በእስራኤል ሰራዊት መካከል በመሆን፣ ሌሊቱን ሙሉ ደመናው በአንድ በኩል ጨለማን ሲያመጣ፣ በሌላው በኩል ብርሃን አመጣ፤ ስለዚህ ሌሊቱን በሙሉ አንዱ ወደ ሌላው ሊጠጋ አልቻለም። ሙሴ እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔር ሌሊቱን በሙሉ ብርቱ የምሥራቅ ነፋስ አስነሥቶ ባሕሩን ወደ ኋላ በማሸሽ ደረቅ ምድር አደረገው፤ ውሃውም ተከፈለ። እስራኤላውያን ውሃው በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ በየብስ በባሕሩ ውስጥ ዐለፉ።
ዘፀአት 14:13-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሙሴም ለሕዝቡ፦ “አትፍሩ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ፤ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተም ዝም ትላላችሁ፤” አላቸው። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ “ለምን ትጮኽብኛለህ? እንዲጓዙ ለእስራኤል ልጆች ንገር። አንተም በትርህን አንሣ፤ እጅህንም በባህሩ ላይ ዘርጋ፤ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባህሩ ውስጥ በየብስ ያልፋሉ። እነሆም እኔ የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ በሰረገሎቹም በፈረሰኞቹም ላይ ክብር አገኛለሁ። ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር ባገኘሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፤ በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ በዚያም ደመናና ጨለማ ነበረ፤ በዚህ በኩል ግን ሌሊቱን አበራ፤ ሌሊቱንም ሁሉ እርስ በእርሳቸው አልተቃረቡም። ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፤ ባሕሩንም አደረቀው፤ ውኃውም ተከፈለ። የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በየብስ ገቡ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆነላቸው።
ዘፀአት 14:13-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሙሴም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “አይዞአችሁ አትፍሩ! ባላችሁበት ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር እናንተን ለማዳን የሚያደርገውን ዛሬ ታያላችሁ፤ እነዚህን ዛሬ የምታዩአቸውን ግብጻውያን ዳግመኛ አታዩአቸውም። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተ ማድረግ የሚገባችሁ ጸጥ ብላችሁ ሁኔታውን መጠበቅ ብቻ ነው።” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ እኔ የምትጮኸው ለምንድን ነው? ይልቅስ ሰዎቹን ወደ ፊት እንዲጓዙ ንገራቸው፤ በትርህን አንሣ፤ በባሕሩም ላይ ዘርጋው፤ ውሃውም ከሁለት ይከፈላል፤ እስራኤላውያንም በደረቅ ምድር ባሕሩን አቋርጠው ይሄዳሉ፤ የግብጻውያንን ልብ ስለማደነድን ሕዝቡን ያሳድዳሉ፤ ንጉሡንና ሠራዊቱን፥ ሠረገሎቹንና ፈረሰኞቹን ድል በመንሣት ክብርን እጐናጸፋለሁ። እነርሱንም በማሸንፍበት ጊዜ ግብጻውያን እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።” የእስራኤልን ሠራዊት ፊት ፊት ይመራ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ኋላ ተመልሶ ደጀን ሆነ፤ የደመናውም ዐምድ አልፎ በኋላ በኩል ቆመ፤ ደመናውም በግብጻውያንና በእስራኤላውያን መካከል መጥቶ ግብጻውያንን በጨለማ ሲጋርድ ለእስራኤል ሕዝብ ግን ብርሃን ይሰጥ ነበር፤ ስለዚህ የግብጽ ሠራዊት ሌሊቱን ሙሉ ወደ እስራኤላውያን መጠጋት አልቻለም። ሙሴ እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም በብርቱ የምሥራቅ ነፋስ ባሕሩን ወደ ኋላ መለሰው፤ ነፋሱም ሌሊቱን ሙሉ በመንፈሱ፥ ባሕሩን ወደ ደረቅ ምድር ለወጠው፤ ውሃውም ከሁለት ተከፈለ፤ እስራኤላውያንም በደረቅ ምድር ባሕሩን ተሻግረው ሄዱ፤ ውሃውም በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ቆሞ ነበር።
ዘፀአት 14:13-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሙሴም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ፥ ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የጌታን ማዳን እዩ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘለዓለም አታዩአቸውምና። ጌታ ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ።” ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለምን ትጮኽብኛለህ? የእስራኤልን ልጆች ጉዞ እንዲቀጥሉ ንገራቸው። አንተም በትርህን አንሣ፥ እጅህንም በባህሩ ላይ ዘርጋ፥ ክፈለውም፤ የእስራኤልም ልጆች በባህሩ ውስጥ በደረቅ ምድር ያልፋሉ። እነሆ እኔ የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፥ ከኋላቸውም ይገባሉ፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ በሰረገሎቹም በፈረሰኞቹም ላይ ክብር አገኛለሁ። ግብፃውያንም በፈርዖንና በሰረገሎቹ በፈረሰኞቹም ላይ ክብር ባገኘሁ ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።” በእስራኤልም ሠፈር ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ከኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ ከኋላቸው ሄደ፤ በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ ደመናና ጨለማ ነበረ፥ ሌሊቱን አበራ፤ ሌሊቱን ሙሉ ማንም አልቀረበም። ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጌታም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፥ ባሕሩንም ደረቅ ምድር አደረገው፥ ውኆችም ተከፈሉ። የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በደረቅ ምድር ሄዱ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው ግድግዳ ሆነላቸው።