ዘፀአት 14:1-9
ዘፀአት 14:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ተመልሰው በመግደሎና በባሕር መካከል፥ በብኤልሴፎን ፊት ለፊት ባለው ገላጣ መንደር አንጻር እንዲሰፍሩ ለእስራኤል ልጆች ተናገር፤ ከእርሱም አጠገብ በባሕር ዳር ትሰፍራላችሁ። ፈርዖንም ለሕዝቡ ስለ እስራኤል ልጆች፦ ‘በምድር ይቅበዘበዛሉ፤ ምድረ በዳም ዘጋቻቸው’ ይላል። እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፤ እርሱም ከኋላቸው ይከተላቸዋል፤ እኔም በፈርዖንና በሠራዊቱ ሁሉ ላይ እከብራለሁ፤ ግብፃውያንም ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” እነርሱም እንዲሁ አደረጉ። ሕዝቡም እንደ ኰበለሉ ለግብፅ ንጉሥ ነገሩት፤ የፈርዖንና የሹሞቹም ልብ በሕዝቡ ላይ ተለወጠና፥ “እንዳይገዙልን የእስራኤልን ልጆች የለቀቅነው ምን ማድረጋችን ነው?” አሉ። ፈርዖንም ሰረገላውን አሰናዳ፤ ሕዝቡንም ከእርሱ ጋር ሰበሰበ። ስድስት መቶ የተመረጡ ሰረገሎችንም፥ የግብፅንም ፈረሶች ሁሉ ወስዶ ሁሉንም ከሦስት ከፈላቸው። እግዚአብሔርም የግብፅን ንጉሥ የፈርዖንንና የሹሞቹን ልብ አጸና፤ እርሱም የእስራኤልን ልጆች አሳደደ፤ የእስራኤልም ልጆች ከፍ ባለች እጅ ወጡ። ግብፃውያንም፥ የፈርዖን ፈረሶች፥ ሰረገሎቹም፥ ፈረሰኞቹም፥ ሠራዊቱም ሁሉ አሳደዱአቸው፤ በባሕሩ ዳር በብኤልሴፎን ፊት ለፊት ባለው ገላጣ መንደር አንጻርም ሰፍረው አገኙአቸው።
ዘፀአት 14:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “እስራኤላውያን ተመልሰው በሚግዶልና በባሕሩ መካከል ባለው በፊሀሒሮት አጠገብ እንዲሰፍሩ ንገራቸው፤ በበኣልዛፎንም አንጻር በባሕሩ አጠገብ ይስፈሩ። ‘ፈርዖን እስራኤላውያን ግራ ተጋብተው በምድረ በዳ በመቅበዝበዝ ይንከራተታሉ’ ብሎ ያስባል። እኔም የፈርዖንን ልብ ስለማደነድነው ያሳድዳቸዋል፤ ነገር ግን በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ፤ ግብጻውያንም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።” እስራኤላውያንም ይህንኑ አደረጉ። የግብጽ ንጉሥ ሕዝቡ መሄዳቸው በተነገረው ጊዜ፣ ፈርዖንና ሹማምቱ ስለ እነርሱ የነበራቸውን ሐሳብ በመለወጥ፣ “ምን ማድረጋችን ነው? እስራኤላውያን እንዲሄዱ ለቀቅናቸው፤ አገልግሎታቸውንም ዐጣን” አሉ። ስለዚህ ሠረገላው እንዲዘጋጅለት አደረገ፤ ሰራዊቱንም ይዞ ተንቀሳቀሰ። ስድስት መቶ ምርጥ ሠረገላዎችን ከሌሎች የግብጽ ሠረገላዎች ጋራ ከነጦር አዛዦቻቸው አሰልፎ ተነሣ። እግዚአብሔር የንጉሡን የፈርዖንን ልብ ስለ አደነደነው በልበ ሙሉነት ከግብጽ የሚወጡትን እስራኤላውያን አሳደዳቸው። ግብጻውያን፣ ይኸውም የፈርዖን ፈረሶችና ሠረገላዎች፣ ፈረሰኞችና እግረኞች ሁሉ እስራኤላውያንን አሳደዷቸው፤ በበኣልዛፎን አንጻር በባሕሩ አጠገብ በፊሀሒሮት ሰፍረው ሳሉ ደረሱባቸው።
ዘፀአት 14:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ተመልሰው በሚግዶልና በባሕር መካከል፥ በበኣልዛፎንም ፊት ለፊት ባለው በፊሀሒሮት ፊት እንዲሰፍሩ ለእስራኤል ልጆች ተናገር፤ ከእርሱም አጠገብ በባህር ዳር ትሰፍራላችሁ። ፈርዖንም ስለ እስራኤል ልጆች፦ ‘በምድር ይቅበዘበዛሉ፤ ምድረ በዳም ዘጋቻቸው፤’ ይላል። እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፤ እርሱም ያባርራቸዋል፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ ላይ ክብር አገኛለሁ፤ ግብፃውያንም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” እነርሱም እንዲሁ አደረጉ። ሕዝቡም እንደ ኮበለሉ ለግብፅ ንጉሥ ነገሩት፤ የፈርዖንና የባሪያዎቹም ልብ በሕዝቡ ላይ ተለወጠና፦ “እንዳይገዛልን እስራኤልን የለቀቅነው ምን አድርገናል?” አሉ። ሰረገላውንም አሰናዳ፤ ሕዝቡንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ስድስት መቶ የተመረጡ ሰረገሎችንም፥ የግብፅንም ፈረሶች ሁሉ፥ በእያንዳንዱም ሰረገላ ሁሉ ላይ ሦስተኞችን ወሰደ። እግዚአብሔርም የግብፅን ንጉሥ የፈርዖንን ልብ አጸና፤ እርሱም የእስራኤልን ልጆች አሳደደ፤ የእስራኤልም ልጆች ከፍ ባለች እጅ ወጡ። ግብፃውያንም የፈርዖን ፈረሶች ሰረገሎቹም ፈረሰኞቹም ሠራዊቱም ሁሉ፥ አሳደዱአቸው፤ በባሕሩ ዳር በበኣልዛፎን ፊት ለፊት ባለው በፊሀሒሮት አጠገብ ሰፍረው አገኙአቸው።
ዘፀአት 14:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እስራኤላውያን ተመልሰው፥ በሚግዶልና በቀይ ባሕር መካከል ባለው ፒሃሒሮት ፊት ለፊት በባዓልጸፎን አጠገብ እንዲሰፍሩ ንገራቸው። እነሆ፥ ንጉሡ እስራኤላውያን በበረሓ ተዘግተው በአገሪቱ ዙሪያ የሚንከራተቱ ይመስለዋል። እኔም ልቡን ስለማደነድነው ያሳድዳችኋል፤ ስለዚህም በንጉሡና በሠራዊቱ ላይ የምጐናጸፈው ድል ለእኔ ክብር ይሆናል፤ በዚያን ጊዜ ግብጻውያን እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።” እስራኤላውያንም እንደ ተነገራቸው አደረጉ። የግብጽ ንጉሥ ሕዝቡ ማምለጣቸው በተነገረው ጊዜ እርሱና መኳንንቱ ሐሳባቸውን ለውጠው “ይህ ያደረግነው ነገር ምንድን ነው? እስራኤላውያን አምልጠው እንዲሄዱ ስንፈቅድ አገልጋዮቻችንን ሁሉ ማጣታችን አይደለምን?” አሉ። ንጉሡም ሠረገላውን አዘጋጅቶ ሠራዊቱን አንቀሳቀሰ። ስድስት መቶ ምርጥ ሠረገሎችን ጨምሮ በግብጽ ያሉትን ሠረገሎች ሁሉ አሰለፈ፤ የጦር አዛዦችንም መደበላቸው፤ እግዚአብሔር የንጉሡን ልብ ስላደነደነ በድፍረት በመውጣት ላይ የነበሩትን እስራኤላውያንን አሳደዳቸው፤ የግብጽ ሠራዊት በፈረሶችና በሠረገላዎች ከፈረሰኞች ጋር ሆኖ ተከታተላቸው፤ በቀይ ባሕር ፊት ለፊት ባሉት በፒሃሒሮት በባዓልጸፎን አጠገብ በሰፈሩበት ቦታ ደረሱባቸው።
ዘፀአት 14:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “እንዲመለሱና በሚግዶልና በባሕሩ መካከል፥ በበዓልጽፎንም ፊት ለፊት ባለው በፒሃሒሮት ፊት እንዲሰፍሩ የእስራኤልን ልጆች ንገራቸው፤ ከእርሱም አንጻር በባህሩ ትሰፍራላችሁ።” ፈርዖንም ስለ እስራኤል ልጆች፦ “በምድር ግራ በመጋባት ይቅበዘበዛሉ፥ ምድረ በዳም ዘጋቻቸው” ይላል። እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፥ እርሱም ያሳድዳቸዋል፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ ላይ ክብር አገኛለሁ፤ ግብፃውያንም እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። እነርሱም እንዲሁ አደረጉ። ሕዝቡም ማምለጣቸውን ለግብጽ ንጉሥ ነገሩት፤ የፈርዖንና የአገልጋዮቹም ልብ በሕዝቡ ላይ ተለወጠና፦ “ምንድነው ያደረግነው? እንዳያገለግለን እስራኤልን ለቀቅነው” አሉ። ሠረገላውንም አሰናዳ፥ ሕዝቡንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ስድስት መቶ የተመረጡ ሰረገሎችን፥ የግብጽንም ሰረገሎችን ሁሉ፥ የጦር አዛዦች በእያንዳንዱ ሠረገላ ላይ ነበሩ። ጌታም የግብጽን ንጉሥ የፈርዖንን ልብ አጸና፥ እርሱም የእስራኤልን ልጆች አሳደደ፤ ዳሩ ግን የእስራኤል ልጆች ከፍ ባለች እጅ ወጡ። ግብፃውያንም የፈርዖን ፈረሶችና ሰረገሎች ፈረሰኞቹም ሠራዊቱም ሁሉ፥ አሳደዱአቸው፤ በባሕሩ በበዓልጽፎን ፊት ለፊት ባለው በፒሃሒሮት ሰፍረው አገኙአቸው።