ዘፀአት 12:1-20
ዘፀአት 12:1-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም በግብፅ ሀገር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁናችሁ፤ የዓመቱም መጀመሪያ ወር ይሁናችሁ። ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ተናገሩ፤ በሉአቸውም፦ በዚህ ወር በዐሥረኛው ቀን ሰው ሁሉ ለአባቱ ቤተ ሰቦች ቤቶች አንድ አንድ ጠቦት፥ እያንዳንዱ ሰውም ለራሱ ቤተ ሰብእ አንድ ጠቦት ይውሰድ። በቤት ያሉት ሰዎች ጥቂት ቢሆኑ፥ አንድ በግም የማይጨርሱ ቢሆኑ በጉን ሊጨርሱ በሚበቁ በሰዎች ቍጥር እያንዳንዱ በአጠገቡ የሚኖረውን ጎረቤቱን ይውሰድ። ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለእናንተ ይሁን፤ ከበጎች ወይም ከፍየሎች ውሰዱ። በዚህም ወር እስከ ዐሥራ አራተኛ ቀን ድረስ ጠብቁት፤ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ሲመሽ ይረዱት። ከደሙም ወስደው በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጉበኑን ይቅቡት። በእሳትም የተጠበሰውን ሥጋውን በዚያች ሌሊት ይብሉ፤ ቂጣውን እንጀራም ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት። ጥሬውንም፥ በውኃም የበሰለውን አትብሉ፤ ነገር ግን በእሳት የተጠበሰውን ራሱን፥ እግሩንና ሆድ ዕቃውን ብሉት። ከእርሱም እስከ ጥዋት አንዳች አታስቀሩ፤ አጥንቱንም ከእርሱ አትስበሩ፤ ከእርሱም እስከ ጥዋት የተረፈ ቢኖር በእሳት አቃጥሉት። ወገቦቻችሁን ታጥቃችሁ፥ ጫማችሁን በእግራችሁ ተጫምታችሁ፥ በትራችሁንም በእጃችሁ ይዛችሁ እንዲህ ብሉት፦ እየቸኰላችሁም ትበሉታላችሁ፤ እርሱ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነውና። እኔም በዚያች ሌሊት በግብፅ ሀገር አልፋለሁ፤ በግብፅም ሀገር ከሰው እስከ እንስሳ ድረስ በኵርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብፅም አማልክት ሁሉ ላይ በቀልን አደርግባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። ደሙም ባላችሁባቸው ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል፤ ደሙንም አያለሁ፤ እናንተንም እሰውራችኋለሁ፤ እኔም የግብፅን ሀገር በመታሁ ጊዜ የጥፋት መቅሠፍት አይመጣባችሁም። ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁናችሁ፤ ለእግዚአብሔርም በዓል ታደርጉታላችሁ፤ ለልጅ ልጃችሁም ሥርዐት ሆኖ ለዘለዓለም ታደርጉታላችሁ። “ሰባት ቀን ቂጣ ትበላላችሁ፤ በመጀመሪያም ቀን እርሾውን ከቤታችሁ ታወጣላችሁ፤ ከመጀመሪያውም ቀን አንሥቶ እስከ ሰባተኛው ቀን እርሾ ያለበትን እንጀራ የሚበላ ነፍስ ከእስራኤል ተለይቶ ይጥፋ። የመጀመሪያዪቱ ቀን ቅድስት ትባላላች፤ እንዲሁም ሰባተኛዋ ቀን ቅድስት ትሁንላችሁ፤ ለነፍስ ከሚሠራው ሥራ ሁሉ በቀር ማናቸውንም ሥራ ሁሉ አትሥሩ በዚህም ቀን ሠራዊታችሁን ከግብፅ ሀገር አወጣዋለሁና ይህን ትእዛዝ ጠብቁት፤ እንግዲህ ይህን ቀን ለልጅ ልጃችሁ ለዘለዓለም ሥርዐት አድርጋችሁ ትጠብቃላችሁ። ከመጀመሪያውም ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን ሠርክ ጀምራችሁ እስከዚሁ ወር ሃያ አንደኛ ቀን ሠርክ ድረስ ቂጣ ትበላላችሁ። ሰባት ቀን በቤታችሁ እርሾ አይገኝ፤ እርሾ ያለበትንም እንጀራ የሚበላ ሁሉ ያ ሰው ከመጻተኛው ጀምሮ እስከ ሀገር ልጁ ድረስ፥ ከእስራኤል ማኅበር ተለይቶ ይጥፋ። እርሾ ያለበትን ምንም አትብሉ፤ በቤቶቻችሁም ሁሉ ውስጥ ቂጣ ብሉ።”
ዘፀአት 12:1-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን በግብጽ እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ወር ለእናንተ የወር መጀመሪያ፣ የዓመቱም መጀመሪያ ይሁንላችሁ። ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ይህን ንገሩ፤ ይህ ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው አንዳንድ ጠቦት ለቤተ ሰቡ፣ አንዳንድ ጠቦት ለአባቱ ቤት ያዘጋጅ። ማንኛውም ቤተ ሰብ ለአንድ ሙሉ ጠቦት ቍጥሩ አነስተኛ ከሆነ፣ በጎረቤት ያሉትን ሰዎች ቍጥር እስከ ቅርብ ከሆነው ጋራ መካፈል ይኖርበታል፤ እያንዳንዱ ሰው በሚበላው መጠንም ምን ያህል ጠቦት እንደሚያስፈልግ መወሰን ይኖርባችኋል። የምትመርጡት ጠቦት በግ ወይም ፍየል ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ምንም ነቀፋ የሌለበትና አንድ ዓመት የሞላው ተባዕት መሆን አለበት። ወሩ በገባ እስከ ዐሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቋቸው። በዚያ ምሽት ጀምበር ስትጠልቅ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ይረዷቸው። ከዚያም ከደሙ ወስደው የጠቦቶቹ ሥጋ የሚበላበትን የእያንዳንዱን ቤት ደጃፍ መቃንና ጕበን ይቀቡ። ሥጋውንም በዚያችው ሌሊት በእሳት ላይ ጠብሰው ከመራራ ቅጠልና ከቂጣ ጋራ ይብሉት። ጥሬውን ሥጋ ወይም ቅቅሉን አትብሉ፤ ነገር ግን ጭንቅላቱን፣ እግሮቹንና ሆድ ዕቃውን በእሳት ላይ ጠብሳችሁ ብሉት። ከሥጋው ተርፎ አይደር፤ ያደረ ቢኖር ግን በእሳት ይቃጠል። ስትበሉም ልብሳችሁን ለብሳችሁ፣ በዐጭር ታጥቃችሁ፣ ጫማችሁን አድርጋችሁ በትራችሁን ይዛችሁ በጥድፊያ ብሉት፤ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው። “እኔም በዚያች ሌሊት በግብጽ ምድር ላይ ዐልፋለሁ፤ ከሰውም ከእንስሳም የተወለደውን የበኵር ልጅ ሁሉ እገድላለሁ፤ የግብጽን አማልክት ሁሉ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። ደሙም ያላችሁበትን ቤት ለይቶ የሚያሳይ ምልክት ይሆንላችኋል፤ እኔ ደሙን በማይበት ጊዜ እናንተን ዐልፋለሁ፤ ግብጽን ስቀጣ መቅሠፍቱ አይደርስባችሁም። “ይህን ቀን መታሰቢያ ታደርጉታላችሁ፤ በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ ቋሚ ሥርዐት ሆኖ የእግዚአብሔር በዓል አድርጋችሁ አክብሩት። ለሰባት ቀናት እርሾ የሌለበት ቂጣ ብሉ። በመጀመሪያው ቀን እርሾን ሁሉ ከቤታችሁ አስወግዱ፤ በእነዚህ ሰባት ቀናት እርሾ ያለበትን ቂጣ የበላ ማንኛውም ሰው ከእስራኤል ይወገድ። በመጀመሪያውና በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ። በእነዚህ ቀናት ምንም ዐይነት ሥራ አትሥሩ፤ የምትሠሩት ሥራ ቢኖር ለእያንዳንዱ ምግብ ማዘጋጀት ብቻ ይሆናል። “የቂጣን በዓል አክብሩ፤ ሰራዊታችሁን ከግብጽ ምድር ያወጣሁት በዚች ዕለት ነውና። ይህን ዕለት ለሚቀጥለው ትውልድ ቋሚ ሥርዐት በማድረግ አክብሩት። ከመጀመሪያው ወር ከዐሥራ አራተኛው ቀን ምሽት እስከ ሃያ አንደኛው ቀን ምሽት ድረስ ቂጣ ትበላላችሁ። ለሰባት ቀን እርሾ በቤታችሁ አይኑር፤ መጻተኛም ሆነ የአገር ተወላጅ እርሾ ያለበትን ቂጣ የበላ ከእስራኤል ማኅበር ይወገድ። እርሾ ያለበትን ምንም ነገር አትብሉ፤ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ቂጣ ነው መብላት ያለባችሁ።”
ዘፀአት 12:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም በግብፅ አገር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። “ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁናችሁ፤ የዓመቱም መጀመሪያ ወር ይሁናችሁ። ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ተናገሩ፥ በሉአቸውም፥ በዚህ ወር በአሥረኛው ቀን ሰው ሁሉ ለአባቱ ቤት አንድ ጠቦት፥ ለአንድ ቤትም አንድ ጠቦት ይውሰድ። የቤቱ ሰዎች ቁጥርም ጠቦቱን ለመጨረስ የማይበቃ ቢሆን እርሱና ለቤቱ የቀረበው ጎረቤቱ እንደ ነፍሶቻቸው ቁጥር አንድ ጠቦት ይውሰድ፤ እያንዳንዱም እንደሚበላው መጠን ከጠቦቱ ይካፈሉ። የእናንተ ጠቦት ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ይሁን፤ ከበጎች ወይም ከፍየሎች ውሰድ። በዚህም ወር እስከ አሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቁት፤ የእስራኤልም ማኅበር ጉባኤ ሁሉ ሲመሽ ይረዱት። ከደሙም ወስደው በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃን ጉበኑን ይቀቡት። በእሳት የተጠበሰውን ሥጋውንና ቂጣውን እንጀራ በዚያች ሌሊት ይብሉ፤ ከመራራ ቅጠል ጋር ይበሉታል። ጥሬውን በውኃም የበሰለውን አትብሉ፤ ነገር ግን ከራሱ ከጭኑ ከሆድ ዕቃው ጋር በእሳት የተጠበሰውን ብሉት፤ ከእርሱም እስከ ጥዋት አንዳች አታስቀሩ፤ እስከ ጥዋት የቀረውን በእሳት አቃጥሉት። ወገቦቻችሁን ታጥቃችሁ፥ ጫማችሁን በእግራችሁ፥ በትራችሁንም በእጃችሁ አድርጋችሁ እንዲህ ብሉት፥ ፈጥናችሁም ትበሉታላችህ፤ እርሱ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው። እኔም በዚያች ሌሊት በግብፅ አገር አልፋለሁ፤ በግብፅም አገር ከሰው እስከ እንስሳ ድረስ በኵርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብፅም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። ደሙም ባላችሁበት ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል፤ ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ፤ እኔም የግብፅን አገር በመታሁ ጊዜ መቅሰፍቱ ለጥፋት አይመጣባችሁም። ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁናችሁ፤ ለእግዚአብሔርም በዓል ታደርጉታላችሁ፤ ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ሆኖ ለዘላለም ታደርጉታላችሁ። “ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ፤ በመጀመሪያም ቀን እርሾውን ከቤታችሁ ታወጣላችሁ፤ ከመጀመሪያውም ቀን አንሥቶ እስከ ሰባተኛው ቀን እርሾ ያለበትን እንጀራ የሚበላ ነፍስ ከእስራኤል ተለይቶ ይጥፋ። በመጀመሪያውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ እንዲሁም በሰባተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንላችኋል። ከሚበላ በቀር በእነርሱም ምንም አትሠሩም፤ ይህንም ብቻ ታደርጉታላችሁ። በዚህም ቀን ሠራዊታችሁን ከግብፅ አገር አውጥቼአለሁና የቂጣውንም በዓል ጠብቁት፤ እንግዲህ ይህን ቀን ለልጅ ልጃችሁ ለዘላለም ሥርዓት ትጠብቃላችሁ። በመጀመሪያውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ ከወሩም እስከ ሀያ አንድ ቀን በመሸ ጊዜ የቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ። ሰባት ቀን በቤታችሁ እርሾ አይገኝ፤ እርሾ ያለበትንም እንጀራ የሚበላ ነፍስ፥ ከመጻተኛው ጀምሮ እስከ አገር ልጁ ድረስ፥ ከእስራኤል ማኅበር ተለይቶ ይጥፋ። እርሾ ያለበትን ምንም አትብሉ፤ በቤቶቻችሁም ሁሉ ውስጥ ቂጣ እንጀራ ብሉ”።
ዘፀአት 12:1-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን በግብጽ ምድር እንዲህ ሲል ተናገራቸው፤ “ይህ ወር ለእናንተ የዓመቱ መጀመሪያ ወር ይሁንላችሁ፤ ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ይህን ሥርዓት አስተምሩ፤ ይህ ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው በቤተሰቡ ደረጃ አንድ ጠቦት ይምረጥ። ቤተሰቡ አነስተኛ ከመሆኑ የተነሣ እንስሳውን በልቶ ለመጨረስ የማይችል ከሆነ ግን እርሱና የቅርብ ጐረቤቱ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ሊመገበው የሚችለውን ያኽል ተመጥኖ እንስሳውን በአንድነት አብረው ይብሉት። የምትመርጡት እንስሳ በግ ወይም ፍየል መሆን ይችላል፤ ነገር ግን ምንም ነውር የሌለበትና አንድ ዓመት የሞላው ተባዕት ይሁን። እነዚህንም እስከ ዐሥራ አራተኛው ቀን ጠብቁአቸው። በዐሥራ አራተኛው ቀን ምሽት ላይ የእስራኤል ኅብረተሰብ ሁሉ እንስሶቹን ይረዱ። ሕዝቡም ከደሙ ወስደው የእንስሶቹ ሥጋ የሚበላበትንም እያንዳንዱን ቤት ደጃፍ መቃኑንና ጉበኑን ሁሉ ይቀቡት፤ ሥጋውንም በዚያኑ ሌሊት እየጠበሱ ከመራር ቅጠልና ካልቦካ ቂጣ ጋር ይብሉት። ከሥጋውም ጥሬውን ወይም ቅቅሉን አትብሉ፤ ራሱን፥ እግሮቹን የሆድ ዕቃውንም ጭምር በሙሉ ጠብሳችሁ ሥጋውን ብሉት። እስከሚነጋም ድረስ ከሥጋው ምንም ነገር አታስተርፉ፤ የተረፈ ነገር ቢኖር ሁሉንም በእሳት አቃጥሉት። ለጒዞ እንደ ተዘጋጀ ሰው ሆናችሁ ወገባችሁን በመታጠቅ ጫማችሁን አድርጋችሁ፥ በትራችሁን በእጃችሁ ይዛችሁ በችኰላ ብሉት፤ እርሱም እኔን እግዚአብሔርን የምታከብሩበት የፋሲካ በዓል ይሁንላችሁ። “በዚያችም ሌሊት እኔ በግብጽ ምድር ሁሉ እየተላለፍኩ እያንዳንዱን የሰውም ሆነ የእንስሳ ዘር የሆነውን የበኲር ልጅ ሁሉ እገድላለሁ፤ የግብጽንም አማልክት ሁሉ እቀጣለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። በደጃፎቻችሁ መቃኖች ላይ የሚታየው ደም እናንተ የምትኖሩባቸውን ቤቶች ለይቶ የሚያሳይ ምልክት ይሆናል፤ እኔም ደሙን በማይበት ጊዜ አልፌአችሁ እሄዳለሁ፤ በዚህም ዐይነት ግብጻውያንን በመቅሠፍት በምመታበት ጊዜ፥ በእናንተ ላይ ምንም ዐይነት መቅሠፍት አይደርስባችሁም። እኔ እግዚአብሔር ያደረግኹላችሁን ሁሉ በማስታወስ ይህ ቀን መንፈሳዊ ክብረ በዓል ይሁንላችሁ፤ እርሱንም በሚመጡት ዘመናት ሁሉ እንድታከብሩት ቋሚ ሥርዓት ይሁንላችሁ።” እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “ሰባት ቀን ሙሉ እርሾ ያልነካውና ፈጽሞ ያልቦካ ቂጣ ብቻ ትበላላችሁ፤ በመጀመሪያው ቀን እርሾውን ሁሉ ከየቤታችሁ ታስወግዳላችሁ፤ ማንም ሰው በነዚያ ሰባት ቀኖች እርሾ ያለበትን እንጀራ ቢበላ ከእስራኤል ሕዝብ መካከል ይወገዳል። ከዚያም ሰባት ቀኖች በመጀመሪያውና በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ታደርጋላችሁ፤ በነዚያም ቀኖች ምግባችሁን ከማዘጋጀት በቀር ምንም ሥራ አትሠሩም። መላውን የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር መርቼ ያወጣሁት በዚህ ቀን ስለ ሆነ ይህን የቂጣ በዓል ትጠብቃላችሁ፤ በሚመጡትም ዘመናት ሁሉ ይህን በዓል ማክበር ቋሚ ሥርዓት ይሁንላችሁ። ከመጀመሪያው ወር ከዐሥራ አራተኛው ቀን ዋዜማ ምሽት ጀምሮ እስከ ኻያ አንደኛው ቀን ምሽት ድረስ ያልቦካ እንጀራ ትበላላችሁ። እስከ ሰባት ቀን ምንም እርሾ በቤታችሁ መገኘት የለበትም፤ የአገር ተወላጅም ሆነ ወይም መጻተኛ ማንኛውም ሰው የቦካ እንጀራ ቢበላ፥ ከእስራኤል ሕዝብ መካከል ይወገዳል፤ በማንኛውም ስፍራ ብትሆኑ እርሾ የሌለበት ቂጣ ብሉ እንጂ እርሾ ያለበት ምንም ነገር አትብሉ።”
ዘፀአት 12:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም በግብጽ ምድር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ “ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁናችሁ፤ ከዓመቱ ወሮችም የመጀመሪያ ይሁናችሁ። ለእስራኤል ልጆች ማህበር ሁሉ እንዲህ ብላችሁ ንገሩ። በዚህ ወር በአሥረኛው ቀን ሰው ሁሉ ለአባቱ ቤት አንድ ጠቦት፥ ለአንድ ቤትም አንድ ጠቦት ይውሰድ። የቤተሰቡ ቍጥር ም ለጠቦቱ የሚያንስ ከሆነ እርሱና ለቤቱ የቀረበው ጎረቤቱ በእያንዳንዱ ሰው ቍጥር አንድ ጠቦት ይውሰድ፤ እያንዳንዱም እንደሚበላው መጠን ከጠቦቱ ይካፈሉ። የእናንተ ጠቦት ነውር የሌለበት፥ ተባዕት፥ የአንድ ዓመት ይሁን፤ ከበጎች ወይም ከፍየሎች ውሰድ። በዚህም ወር እስከ ዐሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቁት፤ የእስራኤልም ማኅበር ጉባኤ ሁሉ ሲመሽ ይረዱት። ከደሙም ጥቂት ወስደው በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጉበኑን ይቀቡት። ሥጋውን በዚያች ሌሊት ይብሉ፤ በእሳት የተጠበሰውን ካልቦካ ቂጣና ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት። ጥሬውን ወይም በውኃ የበሰለውን አትብሉ፥ ነገር ግን ራሱ፥ ከእግሮቹና ከሆድ ዕቃው ጋር በእሳት የተጠበሰውን ብሉት። ከእርሱም እስከ ጥዋት አንዳች አታስቀሩ፤ እስከ ጥዋት የቀረውንም በእሳት አቃጥሉት። እንግዲህ ወገቦቻችሁን ታጥቃችሁ፥ ጫማችሁን በእግራችሁ፥ በትራችሁንም በእጃችሁ አድርጋችሁ ብሉት፥ ፈጥናችሁም ብሉት፤ ለጌታ ፋሲካ ነው። እኔም በዚያች ሌሊት በግብጽ ምድር አልፋለሁ፥ በግብጽም ምድር ከሰው እስከ ከብት ድረስ በኩርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብጽም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ ጌታ ነኝ። ደሙም በምትኖሩባቸው ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል፤ ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ፤ እኔም የግብጽን ምድር በመታሁ ጊዜ መቅሰፍቱ ለጥፋት አይመጣባችሁም። ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁናችሁ፥ በዓል አድርጋችሁ ጠብቁት፥ ለጌታ በዓል ነው፤ ለትውልዳችሁ ለዘለዓለም ሥርዓት አድርጋችሁ ትጠብቁታላችሁ። ሰባት ቀን ያልቦካ ቂጣ ትበላላችሁ፤ በመጀመሪያው ቀን ከቤቶቻችሁ እርሾ ታስወግዳላችሁ፤ ከመጀመሪያውም ቀን አንሥቶ እስከ ሰባተኛው ቀን የቦካ የሚበላ ያቺ ነፍስ ከእስራኤል ተለይታ ትጥፋ። በመጀመሪያውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ እንዲሁም በሰባተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንላችኋል። ለሁሉም ሰው የሚሆን የሚበላ ካልሆነ በቀር በእነርሱ ቀናት ምንም አትሥሩ፥ ይህንም ብቻ ታደርጋላችሁ። በዚህም ቀን ሠራዊታችሁን ከግብጽ ምድር አውጥቼአለሁና የቂጣውን በዓል ጠብቁት፤ እንግዲህ ይህን ቀን በትውልዳችሁ ለዘለዓለም ሥርዓት ትጠብቃላችሁ። በመጀመሪያው ወር ከወሩም በዓሥራ አራተኛው ቀን ምሽት እስከ ከወሩ ሀያ አንድ ቀን ምሽት ድረስ ያልቦካ ቂጣ ትበላላችሁ። ሰባት ቀን በቤታችሁ እርሾ አይገኝ፤ እርሾ ያለበትንም እንጀራ የሚበላ ነፍስ፥ ከመጻተኛው ጀምሮ እስከ አገሩ ተወላጅ ድረስ፥ ከእስራኤል ማኅበር ተለይቶ ይወገድ። እርሾ ያለበትን ምንም አትብሉ፥ በምትኖሩበትም ቦታ ሁሉ ያልቦካ ቂጣ ብሉ።”