አስቴር 8:4-8

አስቴር 8:4-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚያም ንጉሡ የወርቅ ዘንጉን ለአስቴር ዘረጋላት፤ እርሷም ተነሥታ በፊቱ ቆመች። እንዲህም አለች፤ “ንጉሡን ደስ የሚያሠኘውና እኔም በፊቱ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ጕዳዩም በንጉሡ ዘንድ ተገቢ ሆኖ ከተገኘና በእኔም ደስ ከተሠኘ፣ የአጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ ሐማ በንጉሡ አውራጃዎች ሁሉ የሚገኙትን አይሁድ ለማጥፋት የሸረበውን ሤራና የጻፈውን ደብዳቤ የሚሽር ትእዛዝ ይጻፍ። በሕዝቤ ላይ መዓት ሲወርድ እያየሁ እንዴት ልታገሥ እችላለሁ? የዘመዶቼንስ መጥፋት እያየሁ እንዴት መቋቋም እችላለሁ?” ንጉሥ ጠረክሲስም ለንግሥት አስቴርና ለአይሁዳዊው ለመርዶክዮስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እነሆ ሐማ አይሁድን ለማጥፋት ስላቀደ፣ ቤት ንብረቱን ለአስቴር ሰጥቻለሁ፤ እርሱንም በዕንጨት ላይ ሰቅለውታል። በንጉሥ ስም የተጻፈና በቀለበቱ የታተመ ደብዳቤ ሊሻር ስለማይችል፣ እናንተ ደግሞ አይሁድን በተመለከተ መልካም መስሎ የታያችሁን ሌላ ዐዋጅ በንጉሡ ስም ጽፋችሁ በንጉሡ የቀለበት ማኅተም ዐትሙት።”

አስቴር 8:4-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ንጉሡም የወርቁን በትር ዘረጋላት፤ እርስዋም ተነሥታ በፊቱ በመቆም እንዲህ አለች፤ “የግርማዊነትዎ መልካም ፈቃድ ቢሆንና ስለ እኔም የሚያስብልኝ ከሆነ፥ እንዲሁም ጉዳዩ በእርስዎ ፊት ትክክል ሆኖ ከተገኘ፥ በንጉሠ ነገሥት ግዛትዎ ሁሉ ውስጥ የሚገኙ አይሁድ ሁሉ ይደመሰሱ ዘንድ የአጋግ ዘር የነበረው የሃመዳታ ልጅ ሃማን ሰጥቶት የነበረውን ትእዛዝ ሁሉ የሚሽር ዐዋጅ እንዲያስተላልፉልኝ እለምንሃለሁ። ይህ ሁሉ ጥፋት በሕዝቤ ላይ ሲደርስና የገዛ ዘመዶቼም ሲገደሉ እንዴት መታገሥ እችላለሁ?” ከዚህም በኋላ ንጉሥ አርጤክስስ ንግሥት አስቴርንና አይሁዳዊውን መርዶክዮስን እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ ሃማን በአይሁድ ላይ ስለ ፈጸመው ሤራ በእንጨት ላይ እንዳሰቀልኩትና ሀብቱንም ሁሉ ለአስቴር እንደ ሰጠሁ የሚታወስ ነው፤ ይሁን እንጂ የቤተ መንግሥቱ ማኅተም ያለበትና በንጉሡ ስም የተላለፈ ዐዋጅ ሊለወጥ አይችልም፤ ሆኖም እናንተ በበኩላችሁ የፈለጋችሁትን ነገር ለአይሁድ ጻፉላቸው፤ በእኔም ስም ከጻፋችሁ በኋላ የቤተ መንግሥቱን ማኅተም አትሙበት።”