አስቴር 1:19-22

አስቴር 1:19-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ንጉሥ ሆይ! እንግዲህ መልካም ፈቃድህ ቢሆን፥ ንግሥት አስጢን ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አንተ ፊት መቅረብ ከቶ እንዳይፈቀድላት የሚገልጥ ውሳኔህን በዐዋጅ አስተላልፍ፤ ይህም ውሳኔ ከቶ የማይለወጥ ሆኖ ለዘለዓለም ይጸና ዘንድ በፋርስና በሜዶን ሕግ ውስጥ እንዲመዘገብ ትእዛዝ አስተላልፍ፤ የአስጢንንም የንግሥትነት ማዕርግ ከእርስዋ ለተሻለች ለሌላ ሴት ስጥ። አንተ የምታስተላልፈውም ዐዋጅ እጅግ ታላቅ በሆነው በዚህ በንጉሠ ነገሥት መንግሥትህ ግዛት ሁሉ በይፋ በሚነገርበት ጊዜ እያንዳንድዋ ሴት ባለጸጋም ይሁን ወይም ድኻ ባልዋን በአክብሮት ትመለከታለች።” ንጉሡና ባለሟሎቹ የሆኑ ባለሥልጣኖች ሁሉ ይህን ሐሳብ በደስታ ተቀበሉት፤ ንጉሡም መሙካን ያቀረበውን ምክር በሥራ ላይ አዋለ። ስለዚህም ንጉሡ “እያንዳንዱ ባል የቤቱ አባወራ ሆኖ በአዛዥነት የመናገር መብቱ የተጠበቀ ይሁን!” የሚል ትእዛዝ በየቋንቋውና በየአጻጻፍ ሥርዓቱ ተዘጋጅቶ ወደያንዳንዱ አገር እንዲተላለፍ አደረገ።