አስቴር 1:1-9
አስቴር 1:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ያሉትን አንድ መቶ ሃያ ሰባት አገሮች ይገዛ በነበረው በጠረክሲስ ዘመነ መንግሥት እንዲህ ሆነ፤ በዚያ ዘመን ንጉሡ ጠረክሲስ የገዛው በሱሳ ግንብ ባለው ንጉሣዊ ዙፋኑ ሆኖ ነበር። እርሱም በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ለመኳንንቱና ለሹማምቱ ሁሉ ታላቅ ግብዣ አደረገ። በግብዣውም የፋርስና የሜዶን የጦር አዛዦች፣ መሳፍንትና የየአውራጃው መኳንንት ተገኝተው ነበር። ለእነርሱም የመንግሥቱን ሰፊ ሀብት፣ የግርማውን ታላቅነትና ክብር አንድ መቶ ሰማንያ ቀን ሙሉ አሳያቸው። እነዚህ ቀናት ካለፉ በኋላ፣ ንጉሡ በሱሳ ግንብ ለነበሩት፣ ከትንሽ እስከ ትልቅ ላለው ሕዝብ ሁሉ፣ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ዙሪያውን በአትክልት በተከበበው አደባባይ ሰባት ቀን የፈጀ ግብዣ አደረገ። አደባባዩም ከነጭና ከሰማያዊ በፍታ የተሠሩ መጋረጃዎች ነበሩት፤ እነርሱም የብር ቀለበት በተበጀላቸው፣ ከነጭ በፍታና ከሐምራዊ ቀለም በተሠሩ ገመዶች በዕብነ በረዱ ምሰሶዎች ላይ ተንጠልጥለው ነበር። ነጭና ቀይ ቀለማት ተሰበጣጥረው በተነጠፉበት ወለል ላይ የወርቅና የብር ድንክ ዐልጋዎች ነበሩ፤ እነርሱም ከዕብነ በረድ፣ ቀስተ ደመና ከሚመስሉ ቀለሞችና ከሌሎች የከበሩ ድንጋዮች የተሠሩ ነበሩ። የወይን ጠጁም አንዱ ከሌላው ልዩ በሆነ የወርቅ ዋንጫ ይቀርብ ነበር፤ ከንጉሡም ልግስና የተነሣ የቤተ መንግሥቱ የወይን ጠጅ የተትረፈረፈ ነበር። ንጉሡ ለእያንዳንዱ ሰው የሚፈልገውን ያህል እንዲያቀርቡለት የወይን ጠጅ አሳላፊዎቹን ሁሉ አዝዞ ስለ ነበረ፣ በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት እያንዳንዱ ተስተናጋጅ እንዲጠጣ ተፈቅዶለት ነበር። ንግሥት አስጢንም በንጉሥ ጠረክሲስ ቤተ መንግሥት እንደዚሁ ለሴቶች ግብዣ አድርጋ ነበር።
አስቴር 1:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በአርጤክስስም ዘመን እንዲህ ሆነ፥ ይህም አርጤክስስ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በመቶ ሀያ ሰባት አገሮች ላይ ነገሠ። በዚያም ዘመን ንጉሡ አርጤክስስ በሱሳ ግንብ በነበረው በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ሳለ፥ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ለባለምዋሎቹና ለአገልጋዮቹ ሁሉ ግብዣ አደረገ፥ የፋርስና የሜዶን ታላላቆች ሁሉ፥ የየአገሩ አዛውንትና ሹማምት፥ በፊቱ ነበሩ፥ የከበረውንም የመንግሥቱን ሀብት፥ የታላቁንም የግርማዊነቱን ክብር መቶ ሰማንያ ቀን ያህል አሳያቸው። ይህም ቀን በተፈጸመ ጊዜ በሱሳ ግንብ ውስጥ ለተገኙት ሕዝብ ሁሉ ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ንጉሡ በንጉሡ ቤት አታክልት ውስጥ ባለው አደባባይ ሰባት ቀን ግብዣ አደረገ። ነጭ፥ አርንጓዴ፥ ሰማያዊም መጋረጆች ከጥሩ በፍታና ከሐምራዊ ግምጃ በተሠራ ገመድ፥ በብር ቀለበትና በዕብነ በረድ አዕማድ ላይ ተዘርግተው ነበር፥ አልጋዎቹም ከወርቅና ከብር ተሠርተው በቀይና በነጭ በብጫና በጥቁር ዕብነ በረድ ወለል ላይ ነበሩ። መጠጡም በልዩ ልዩ በወርቅ ዕቃ ይታደል ነበር፥ የንጉሡም የወይን ጠጅ እንደ ንጉሡ ለጋስነት መጠን እጅግ ብዙ ነበረ። ንጉሡም እንደ ሰው ሁሉ ፈቃድ ያደርጉ ዘንድ ለቤቱ አዛዦች ሁሉ አዝዞ ነበርና መጠጡ እንደ ወግ አልነበረም። ንግሥቲቱም አስጢን በንጉሡ በአርጤክስስ ቤተ መንግሥት ለሴቶች ግብዣ አደረገች።
አስቴር 1:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ንጉሥ አርጤክስስ ከሕንድ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ያሉትን መቶ ኻያ ሰባት አገሮችን ይገዛ ነበር። በዚያን ጊዜ ንጉሡ አርጤክስስ ሱሳ በምትገኘው ቤተ መንግሥቱ ይኖር ነበር። አርጤክስስ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ባለሟሎቹ ለሆኑት ባለሥልጣኖችና አስተዳዳሪዎች ሁሉ ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ በግብዣውም ላይ የፋርስና የሜዶን ጦር አዛዦች፥ አገረ ገዢዎችና የክፍላተ ሀገር አስተዳዳሪዎች ተገኝተው ነበር። ንጉሡም ለስድስት ወራት ያኽል የመንግሥቱን የሀብት ብዛትና የንጉሣዊውን ግርማ ሞገስና ክብር በይፋ እንዲታይ አደረገ። ከዚህም በኋላ ንጉሥ አርጤክስስ የመናገሻ ከተማ በሆነችው በሱሳ ለሚኖሩ ሁሉ ለሀብታሞችም፥ ለድኾችም፥ እንደገና ሌላ ግብዣ አደረገ፤ በቤተ መንግሥቱ የአትክልት ቦታ ውስጥ የተደረገውም ያ ግብዣ አንድ ሳምንት ሙሉ ቈየ። የአትክልት ቦታውም ከነጭ ጥጥ በፍታ በተሠሩ ሰማያዊ ቀለም ባላቸው መጋረጃዎች የተጌጠ ነበር፤ መጋረጃዎቹም ከሐምራዊ በፍታ በተሠሩና የብር ቀለበት በተበጀላቸው ገመዶች በዕብነ በረድ ምሰሶዎች ላይ ተንጠልጥለው ነበር፤ ከወርቅና ከብር የተሠሩ ድንክ አልጋዎችም ነጭና ቀይ፥ ቢጫና ሰማያዊ ቀለማትን በሚፈነጥቅ የዕብነ በረድ ወለል ላይ ተደርድረው ነበረ። አንዱ ከሌላው በማይመሳሰል በልዩ ልዩ የወርቅ ዋንጫ መጠጥ ይታደል ነበር፤ የንጉሡ የወይን ጠጅ ብዛት ስለ ነበረው የወይን ጠጁ በገፍ እንዲሰጥ አደረገ፤ ንጉሡም ማንኛውም ሰው እንደየባህሉ የሚፈልገውን ያኽል መጠጣት ይችል ዘንድ ለቤተ መንግሥቱ አገልጋዮች ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። ይህ በዚህ እንዳለ ንግሥት አስጢን ደግሞ በበኲልዋ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ለሴት ወይዛዝርት ግብዣ አድርጋ ነበር።