ኤፌሶን 6:12-18
ኤፌሶን 6:12-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሰልፋችሁ፦ ከጨለማ ገዦች ጋርና ከሰማይ በታች ካሉ ከክፉዎች አጋንንት ጋር ነው እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ጋር አይደለምና። ስለዚህም በክፉ ቀን መቃወም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ጋሻ ያዙ፤ እንድትጸኑም በሁሉ የተዘጋጃችሁ ሁኑ። እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ ቁሙ፤ የጽድቅንም ጥሩር ልበሱ። የሰላም ወንጌል ኀይልንም ተጫምታችሁ ቁሙ። ከዚህም ሁሉ ጋር የሚንበለበሉ የክፉን ፍላፃዎች ሁሉ ማጥፋት እንድትችሉ የእምነትን ጋሻ አንሡ። የመዳንንም የራስ ቍር በራሳችሁ ላይ ጫኑ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ሰይፍ ያዙ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ቃል ነው። በጸሎትና በምልጃ ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ ከዚህም ጋር ስለ ቅዱሳን ሁሉ ለመጸለይ ሁልጊዜ ትጉ፤
ኤፌሶን 6:12-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ምክንያቱም ተጋድሏችን ከሥጋና ከደም ጋራ ሳይሆን ከዚህ ከጨለማ ዓለም ገዦች፣ ከሥልጣናትና ከኀይላት እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከርኩሳን መናፍስት ሰራዊት ጋራ ነው። ክፉው ቀን ሲመጣ መቋቋም ትችሉ ዘንድ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ፤ ሁሉን ከፈጸማችሁ በኋላ ጸንታችሁ መቆም ትችላላችሁና። እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ዝናር ታጥቃችሁ፣ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፣ በሰላም ወንጌል ዝግጁነት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ። ከእነዚህም ሁሉ ጋራ፣ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ የመዳንን ራስ ቍር አድርጉ፤ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው። በሁሉ ዐይነት ጸሎትና ልመና፣ በማንኛውም ሁኔታ በመንፈስ ጸልዩ፤ ይህንም በማሰብ ንቁ፤ ስለ ቅዱሳንም ሁሉ በትጋት ልመና አቅርቡ።
ኤፌሶን 6:12-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ። ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ። እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፤ በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው። በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ፤
ኤፌሶን 6:12-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የእኛ ውጊያ ከሰዎች ጋር ሳይሆን በዚህ በጨለማ ዘመን ከሚሠሩት ገዢዎች፥ ከባለ ሥልጣኖችና ከዚህ ዓለም ኀይሎችና ይህም ማለት በሰማይ ካሉት ከርኩሳን መናፍስት ሠራዊት ጋር ነው። ስለዚህ በክፉ ቀን የጠላትን ኀይል ለመቋቋም እንድትችሉና ሁሉንም ፈጽማችሁ ጸንታችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር መሣሪያ አንሡ! እንግዲህ እውነትን እንደ ዝናር በወገባችሁ ታጥቃችሁ፥ ጽድቅን እንደ ጥሩር ለብሳችሁ፥ የሰላምን ወንጌል እንደ ጫማ በእግሮቻችሁ ተጫምታችሁ በመዘጋጀት ቁሙ። ከዚህም ሁሉ በላይ እንደ እሳት የሚንበለበሉትን የዲያብሎስን ፍላጻዎች ሁሉ ማጥፋት የምትችሉበትን እምነት እንደ ጋሻ አንግቡ። መዳንን እንደ ራስ ቊር በራሳችሁ ላይ ድፉ፤ እንዲሁም ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኘውን ሰይፍ ይኸውም የእግዚአብሔርን ቃል ያዙ። ዘወትር በመንፈስ ቅዱስ እየተመራችሁ ጸሎትንና ልመናን አቅርቡ። በዚህም መሠረት እግዚአብሔር ለቀደሳቸው ሰዎች ነቅታችሁና ተግታችሁ ጸልዩ።
ኤፌሶን 6:12-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ተጋድሏችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለም፤ ነገር ግን ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር፥ ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር፥ በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው። ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን የጦር ትጥቅ አንሡ። እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ የሰላም ወንጌል ለማወጅ በዝግጁነት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፤ በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን የመዳንንም ራስ ቁር፥ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ። በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ እስከ መጨረሻው በጽናት ትጉ።