ኤፌሶን 4:7-16

ኤፌሶን 4:7-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከእኛ ለእ​ያ​ን​ዳ​ንዱ በክ​ር​ስ​ቶስ ስጦታ መጠን ጸጋው ተሰ​ጥ​ቶ​ናል። “ምር​ኮን ማር​ከህ ወደ ሰማይ ወጣህ፤ ጸጋ​ህ​ንም ለሰው ልጅ ሰጠህ” ይላ​ልና። ከም​ድር በታች ካል​ወ​ረደ መው​ጣቱ ምን​ድን ነው? የወ​ረ​ደው እርሱ ነው፤ ሁሉ​ንም ይመላ ዘንድ ከሰ​ማ​ያት ሁሉ በላይ የወ​ጣው ደግሞ እርሱ ነው። እር​ሱም ጸጋን ሰጠ፤ ከቤተ ሰቦ​ቹም ሐዋ​ር​ያ​ትን፥ ከእ​ነ​ር​ሱም ነቢ​ያ​ት​ንና የወ​ን​ጌል ሰባ​ኪ​ዎ​ችን፥ ጠባ​ቂ​ዎ​ች​ንና መም​ህ​ራ​ንን ሾመ። ቅዱ​ሳን ለአ​ገ​ል​ግ​ሎቱ ሥራና ለክ​ር​ስ​ቶስ አካል ሕንጻ እን​ዲ​ጸኑ፤ ሁላ​ችን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ልጅ በማ​መ​ንና በማ​ወቅ አንድ እስ​ክ​ን​ሆን ድረስ በክ​ር​ስ​ቶስ ምል​ዐት መጠን፥ አካለ መጠን እንደ አደ​ረሰ እንደ አንድ ሙሉ ሰው እስ​ክ​ን​ሆን ድረስ፥ እን​ግ​ዲህ በሽ​ን​ገ​ላ​ቸው ያስቱ ዘንድ በሚ​ተ​ና​ኰሉ ሰዎች ተን​ኰል ምክ​ን​ያት በት​ም​ህ​ርት ነፋስ ሁሉ ወዲ​ያና ወዲህ እየ​ተ​ፍ​ገ​መ​ገ​ም​ንና እየ​ተ​ን​ሳ​ፈ​ፍን ሕፃ​ናት አን​ሁን። ነገር ግን በፍ​ቅር እው​ነ​ተ​ኞች እን​ሆን ዘንድ ራስ ወደ ሆነው ወደ እርሱ ወደ ክር​ስ​ቶስ እን​ደግ። ከእ​ርሱ የተ​ነሣ አካል ሁሉ እያ​ን​ዳ​ንዱ ክፍል በልክ እን​ደ​ሚ​ሠራ፥ በተ​ሰ​ጠው በሥር ሁሉ እየ​ተ​ጋ​ጠ​መና እየ​ተ​ያ​ያዘ፥ ራሱን በፍ​ቅር ለማ​ነጽ አካ​ሉን ያሳ​ድ​ጋል።

ኤፌሶን 4:7-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ነገር ግን ክርስቶስ በወሰነው መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጥቶናል። ስለዚህም እንዲህ ይላል፤ “ወደ ላይ በወጣ ጊዜ፣ ምርኮን ማረከ፤ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ።” ታዲያ፣ “ወደ ላይ ወጣ” ማለት ደግሞ ወደ ምድር ታችኛው ክፍል ወረደ ማለት ካልሆነ በቀር ምን ማለት ነው? ወደ ታች የወረደውም፣ መላውን ፍጥረተ ዓለም ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው እርሱ ራሱ ነው። አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ አንዳንዶቹ ነቢያት፣ አንዳንዶቹም ወንጌል ሰባኪዎች፣ ሌሎቹ ደግሞ እረኞችና አስተማሪዎች ይሆኑ ዘንድ የሰጠ እርሱ ነው፤ ይኸውም የክርስቶስ አካል ይገነባ ዘንድ፣ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት ሲሆን፣ ይህም የሚሆነው፣ ሁላችንም የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኘው አንድነት በመምጣትና ሙሉ ሰው በመሆን፣ በክርስቶስ ወዳለው ፍጹምነት ደረጃ እስከምንደርስ ነው። ከእንግዲህ በማዕበል ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየተነዳን፣ በልዩ ልዩ ዐይነት የትምህርት ነፋስ፣ በሰዎችም ረቂቅ ተንኰልና ማታለል ወዲያና ወዲህ እየተንገዋለልን ሕፃናት አንሆንም። ይልቁንም እውነትን በፍቅር እየተናገርን፣ ራስ ወደ ሆነው ወደ እርሱ በነገር ሁሉ እናድጋለን፤ እርሱም ክርስቶስ ነው። ከርሱም የተነሣ፣ አካል ሁሉ በሚያገናኘው ጅማት እየተያያዘና እየተጋጠመ፣ እያንዳንዱ ክፍል የራሱን ሥራ እያከናወነ በፍቅር ያድጋል፤ ራሱንም ያንጻል።

ኤፌሶን 4:7-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን። ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል። ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው። እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም፥ ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፤ ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል።

ኤፌሶን 4:7-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ነገር ግን ክርስቶስ ለመስጠት በወሰነው መጠን ለእያንዳንዳችን የጸጋው ስጦታ ተሰጥቶናል። ይህም፦ “ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ብዙ ምርኮኞችን ይዞ ሄደ፤ ለሰዎችም ስጦታዎችን ሰጠ” እንደ ተባለው ነው። ታዲያ፥ ይህ “ወደ ላይ ወጣ” የሚለው ቃል አስቀድሞ ወደዚህች ምድር፥ ከምድሪቱም ወደ ዝቅተኛው ቦታ መውረዱ ካልሆነ በቀር ሌላ ምንን ያመለክታል? ይህ ወደ ታች የወረደው ደግሞ ያ ሁሉን ለመሙላት ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ነው። እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ አንዳንዶቹ ነቢያት፥ አንዳንዶቹ የወንጌል ሰባኪዎች፥ አንዳንዶቹ የምእመናን እረኞች፥ አንዳንዶቹ አስተማሪዎች እንዲሆኑ ስጦታዎችን ሰጣቸው። ይህንንም ያደረገው የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን እንድትታነጽ፥ ምእመናንን ለክርስቲያናዊ አገልግሎት ለማዘጋጀት ነው። እንዲሁም የእግዚአብሔርን ልጅ በማወቅ በእምነት ወደሚገኘው አንድነት ደርሰን፥ ክርስቶስ ፍጹምና ሙሉ እንደሆነው ዐይነት እኛም ሙሉ ሰው እንድንሆን ነው። ከእንግዲህ ወዲህ በሰዎች የተንኰል ሽንገላና አታላይነት በተዘጋጀ በአሳሳች የትምህርት ነፋስና ሞገድ ወዲያና ወዲህ ተገፍትረው እንደሚወሰዱ ሕፃናት አንሆንም። ይልቁንም እውነትን በፍቅር እየተናገርን በሁሉም ነገር ራስ ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ እናድጋለን። የተለያዩት የሰውነት ክፍሎች የሚገጣጠሙት በክርስቶስ ነው፤ አካልም በሙሉ የተያያዘው በመገጣጠሚያዎቹ ነው፤ ስለዚህ እያንዳንዱ የአካል ክፍል የተመደበለትን ተግባር በሚገባ ሲያከናውን አካል በሙሉ ያድጋል፤ በፍቅርም ይታነጻል።

ኤፌሶን 4:7-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን። ስለዚህ “ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ፤ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ፤” ይላል። ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? ይህ የወረደው ሁሉን ለመሙላት ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው እርሱ ራሱ ነው። አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ የሰጠ እርሱ ነው፤ ይህም የክርስቶስ አካል ለመገንባት፥ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት ነው፤ ይህም ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ፍጽምናው እስክንደርስ ድረስ ነው። ከእንግዲህ እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል፥ በሰዎችም ማታለል ምክንያት፥ በነፈሰው የትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን፥ ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን፥ ሕፃናት መሆን አይገባንም። ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየተናገርን፥ በነገር ሁሉ ራስ ወደሚሆን ወደ እርሱ ወደ ክርስቶስ እንደግ፤ ከእርሱም የተነሣ መላው አካል በሚያገናኘው ጅማት እየተያያዘና እየተጋጠመ፥ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል።